ኢሳይያስ 54:13 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም “ልጆችሽ ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፤ የልጆችሽም ሰላም የተሟላ ይሆናል። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ልጆችሽ ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፤ የልጆችሽም ሰላም ታላቅ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ልጆችሽም ሁሉ ከጌታ የተማሩ ይሆናሉ፥ የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፤ ልጆችሽም በብዙ ሰላም ይኖራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፥ የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል። |
በእግዚአብሔር ቅዱስ ተራራ ላይ ምንም ጒዳት አይደርስም፤ ባሕር በውሃ እንደሚሞላ ምድርም እግዚአብሔርን በሚያውቁና በሚያከብሩ ሰዎች ትሞላለች።
ስለዚህ ብዙ ሕዝቦች እንዲህ ይላሉ፦ “ሕግ ከጽዮን፥ የእግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም ስለሚገኝ ኑ ወደ እግዚአብሔር ተራራ እንውጣ፤ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤተ መቅደስም እንሂድ፤ እርሱ ፈቃዱን እንድናደርግ ያስተምረናል፤ እኛም በእርሱ መንገድ እንሄዳለን።”
“ትእዛዞቼን በጥንቃቄ ሰምታችሁ ቢሆንማ ኖሮ፥ በረከታችሁ እንደማይደርቅ የወንዝ ውሃ፥ ጽድቃችሁም እንደ ባሕር ሞገድ በብዛት በመጣላችሁ ነበር!
ደካሞችን በቃል ማጽናትን ዐውቅ ዘንድ ጌታ እግዚአብሔር የምሁርን አንደበት ሰጥቶኛል፤ በየማለዳው ከእንቅልፍ ያነቃኛል፤ እንደ ተማሪም አዳምጥ ዘንድ ጆሮዬን ይከፍታል።
“እናንተም ከባቢሎን በደስታ ወጥታችሁ፥ በሰላም ወደ ሀገራችሁ እንድትመለሱ ትደረጋላችሁ፤ ተራራዎችና ኰረብቶች በፊታችሁ በመዘመር ይፈነድቃሉ፤ የሜዳ ዛፎችም በእጆቻቸው ያጨበጭባሉ።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሀብትዋን እንደ ወንዝ ውሃ አበዛዋለሁ፤ የሕዝቦችንም ሀብት እንደ ወንዝ ጅረት አደርገዋለሁ፤ በክንድዋም ተይዛችሁ ትጠባላችሁ፤ በጭንዋም ላይ አድርጋ ትንከባከባችኋለች።
ከእንግዲህ ወዲህ ‘እግዚአብሔርን ዕወቅ’ ብሎ ባልንጀራውንም ሆነ ወንድሙን የሚያስተምር ማንም አይኖርም፤ ከትልቁ ጀምሮ እስከ ትንሹ ሁሉም ያውቁኛል፤ በደላቸውን ይቅር እልላቸዋለሁ፤ ኃጢአታቸውንም አላስታውስባቸውም፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
ነገር ግን ይህችን ከተማና ሕዝብዋን እንደገና እፈውሳለሁ፤ ጤንነታቸውንም እመልስላቸዋለሁ፤ በሁሉም ቦታ ሰላምንና የሕይወት ዋስትናን አበዛላቸዋለሁ፤
የሰላም ዋስትና የሚያገኙበትን ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር እገባለሁ፤ አደገኞች የሆኑትን አራዊት ከምድሪቱ አስወግዳለሁ፤ ስለዚህ በጎቼ በየመስኩ በሰላም ተሰማርተው ሊኖሩና በየጫካውም ሊያድሩ ይችላሉ።
ከእነርሱ ጋር የሰላም ቃል ኪዳን እገባለሁ፤ ያም ቃል ኪዳን ዘለዓለማዊ ነው፤ እነርሱንም እንደገና መሥርቼ የሕዝቡን ቊጥር አበዛለሁ፤ ቤተ መቅደሴንም ለዘለዓለም ጸንቶ በሚቈይበት ስፍራ በምድራቸው አኖራለሁ።
በዚያን ጊዜ ስለ እናንተ ከአራዊት፥ ከሰማይ ወፎችና በደረታቸው በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጥረቶች ጋር ቃል ኪዳን እገባለሁ፤ ከምድሪቱም ላይ ቀስትን፥ ሰይፍንና ጦርነትን አስወግዳለሁ፤ እናንተንም በሰላም እንድታርፉ አደርጋለሁ።
ስለዚህ ብዙ ሕዝቦች እንዲህ ይላሉ፥ “ሕግ ከጽዮን፥ የእግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም ስለሚገኝ፥ ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር ተራራ እንውጣ፤ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤተ መቅደስም እንሂድ፤ እርሱ ፈቃዱን እንድናደርግ ያስተምረናል፤ እኛም በእርሱ መንገድ እንሄዳለን።”
የእስራኤል ሕዝብ እንደ ብርቱ ጦረኞች ይሆናሉ፤ የወይን ጠጅ እንደ ጠጣ ሰውም ደስተኞች ይሆናሉ፤ ልጆቻቸውም ይህን ድል በማስታወስ ደስ ይላቸዋል፤ በእግዚአብሔርም ሐሤት ያደርጋሉ።
ይህን ለእናንተ መናገሬ በእኔ ሆናችሁ ሰላም እንዲኖራችሁ ብዬ ነው፤ በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፥ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።”
ለእኛ ግን እግዚአብሔር በመንፈሱ አማካይነት ምሥጢሩን ገልጦልናል፤ የእግዚአብሔር መንፈስ ጥልቅ የሆነውን የእግዚአብሔርን ምሥጢር እንኳ ሳይቀር ሁሉን ነገር ይመረምራል።
“እነሆ፥ ከዚህ ጊዜ በኋላ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር የምገባው ቃል ኪዳን የሚከተለው ነው ይላል ጌታ፤ እኔ ሕጌን በአእምሮአቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ አምላካቸውም እሆናለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።
ከክርስቶስ የተቀበላችሁት መንፈስ በውስጣችሁ ስለሚኖር ሌላ አስተማሪ አያስፈልጋችሁም፤ እርሱ ሁሉን ነገር ያስተምራችኋል፤ የሚያስተምራችሁም እውነትን ነው እንጂ ሐሰትን አይደለም። ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንዳስተማራችሁ በክርስቶስ ኑሩ።