ኢሳይያስ 44:3 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም “ለተጠማው ምድር ውሃን እሰጣለሁ፤ በደረቀውም ምድር ጅረቶች እንዲፈስሱ አደርጋለሁ፤ መንፈሴን በልጆችህ ላይ አፈሳለሁ፤ በረከትንም ለልጅ ልጆችህ እሰጣለሁ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም በተጠማ ምድር ላይ ውሃ፤ በደረቅ መሬት ላይ ወንዞችን አፈስሳለሁና፤ መንፈሴን በዘርህ፣ በረከቴንም በልጅ ልጅህ ላይ አወርዳለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በተጠማ ላይ ውኃን በደረቅም መሬት ላይ ፈሳሾችን አፈሳለሁና፤ መንፈሴን በዘርህ ላይ በረከቴንም በልጆችህ ላይ አፈሳለሁ፥ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በደረቅ መሬት ላይ ለሚሄድና ለተጠማ ውኃን እሰጣለሁ፤ መንፈሴን በዘርህ ላይ፥ በረከቴንም በልጆችህ ላይ አኖራለሁ፤ መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በተጠማ ላይ ውኃን በደረቅም መሬት ላይ ፈሳሾችን አፈስሳለሁና፥ መንፈሴን በዘርህ ላይ በረከቴንም በልጆችህ ላይ አፈስሳለሁ፥ |
እግዚአብሔር ሆይ! አንተ አምላኬ ነህ፤ አንተን ለማግኘት በብርቱ እናፍቃለሁ፤ ሁለንተናዬ አንተን ይመኛል፤ ውሃ በማጣት ደርቆ እንደ ተሰነጣጠቀ መሬት ነፍሴ አንተን ተጠማች።
ነገር ግን እግዚአብሔር መንፈሱን በእኛ ላይ የሚያፈስበት ጊዜ ይመጣል፤ በዚያን ጊዜ ምድረ በዳው ለም ይሆናል፤ ለሙም መሬት ብዙ ፍሬ ይሰጣል።
ከእነርሱ እያንዳንዱ ከነፋስ እንደሚከለሉበትና ከወጀብ እንደሚሰወሩበት መጠጊያ ይሆናል፤ በበረሓ እንደሚፈስሱ ጅረቶችና በምድረ በዳ እንደሚገኝ እንደ ትልቅ አለት መጠለያ ይሆናሉ።
“ድኾችና ችግረኞች ውሃ ይፈልጋሉ፤ አያገኙም፤ ጒሮሮአቸው ከጥማት የተነሣ ሲደርቅ፥ እኔ እግዚአብሔር ጸሎታቸውን እሰማለሁ፤ እኔም የእስራኤል አምላክ ከቶ አልተዋቸውም።
እግዚአብሔር በምድረ በዳ በመራቸው ጊዜ ውሃ አልጠማቸውም፤ ይልቁንስ ውሃ ከአለት እንዲፈልቅላቸው አደረገ። አለቱን ከፍሎ ውሃ አጐረፈላቸው።
መራብና መጠማትም አይደርስባቸውም፤ የሚያቃጥል ነፋስ ወይም ፀሐይ አይጐዳቸውም፤ ይህም የሚሆነው የሚራራላቸው እርሱ የውሃ ምንጭ ወደሚገኝበት ቦታ ስለሚመራቸው ነው።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ ወደ ውሃው ኑ! የምትገዙበት ገንዘብ የሌላችሁ ኑና ገዝታችሁ ብሉ! ኑና ያለ ገንዘብና ያለ ዋጋ ወተትና የወይን ጠጅን ግዙ።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ከእነርሱ ጋር የሚኖረኝ ቃል ኪዳን ይህ ነው፦ ከአሁን ጀምሮ እስከ ዘለዓለም በእናንተ ላይ ያለው መንፈሴና በአንደበታችሁ ያኖርኩትን ቃሌን ለልጆቻችሁና ለልጅ ልጆቻችሁ አስተምሩ ይላል እግዚአብሔር።”
ልጆቻቸው በወገኖች ዘንድ፥ የልጅ ልጆቻቸውም በሕዝቦች ዘንድ የታወቁ ይሆናሉ። የሚያዩአቸው ሁሉ በእኔ በእግዚአብሔር የተባረኩ ዘሮች መሆናቸውን ያውቃሉ።
ሥራቸው ከንቱ አይሆንም፤ የወለዱአቸው ልጆችና የልጅ ልጆቻቸው በእግዚአብሔር የተባረኩ ስለሚሆኑ ልጆቹን የሚወልዱት ጥፋት እንዲደርስባቸው አይደለም።
እርሱም እንዲህ አለኝ፦ “ይህ ውሃ በምድሪቱ ውስጥ ወደ ምሥራቅ፥ ወደ ዮርዳኖስ ሸለቆና ወደ ሙት ባሕር ይፈስሳል፤ ወደ ሙት ባሕር በሚፈስበት ጊዜ የጨዉ ባሕር ታድሶ ጥሩ ውሃ ይሆናል።
እኔም ‘እንግዲህ ዕዳሪውን መሬት ዕረሱ፤ ጽድቅን ለራሳችሁ ዝሩ፤ የማይለዋወጥ ፍቅርን ሰብስቡ፤ እነሆ ወደ እኔ ወደ አምላካችሁ የምትመለሱበት ጊዜ አሁን ነው! እኔም መጥቼ ፍትሕን አሰፍንላችኋለሁ’ አልኩ።
ሕዝቤ ሆይ! እኔ በመካከላችሁ እንዳለሁ፥ አምላካችሁም እኔ ብቻ እንደ ሆንኩና ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ ታውቃላችሁ፤ ሕዝቤ ከእንግዲህ ወዲህ ኀፍረት አይደርስባቸውም።”
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ከዚህ በኋላ መንፈሴን በሰው ሁሉ ላይ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልምን ያልማሉ፤ ወጣቶቻችሁም ራእይ ያያሉ።
“በዚያን ጊዜ ተራራዎችም ሁሉ በወይን ተክል ይሸፈናሉ፤ በኰረብቶችም ላይ ብዙ ወተት የሚሰጡ ከብቶች ይሰማራሉ፤ በይሁዳ ምድር የሚገኙ ወንዞች ሁሉ በውሃ የተሞሉ ይሆናሉ፤ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ምንጭ ይፈልቃል፤ የሺጢምንም ሸለቆ ያጠጣል።
ከሞት የተረፉትም የእስራኤል ሕዝብ በብዙ ሕዝቦች መካከል እግዚአብሔር እንደሚልከው ጠልና በሣር እንደሚወርድ ካፊያ ይሆናሉ፤ ተማምነው የሚጠባበቁት ሰውን ሳይሆን እግዚአብሔርን ብቻ ይሆናል።
“በዚያን ጊዜ በዳዊት ዘሮችና በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ላይ የርኅራኄና የጸሎት መንፈስ እሞላለሁ፤ ይህንንም የማደርገው እነርሱ ለአንድያ ልጅና ለበኲር ልጅ እንደሚለቀስ ለወጉት ምርር ብለው እንዲያለቅሱለት ነው።
ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ርኩስ መንፈስ ከሰው በወጣ ጊዜ የሚያርፍበት ቦታ በመፈለግ ውሃ በሌለበት በደረቅ ቦታ ይዞራል። ነገር ግን አያገኝም፤
‘እግዚአብሔር በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል ይላል፤ መንፈሴን በሰው ሁሉ ላይ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤ ጐልማሶቻችሁም ራእይ ያያሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ።
ከዚህም በኋላ እንዲህ አለኝ፤ “ተፈጸመ! አልፋና ዖሜጋ፥ የመጀመሪያውና የመጨረሻው እኔ ነኝ፤ ለተጠማ ከሕይወት ውሃ ምንጭ ያለ ምንም ዋጋ በነጻ እሰጠዋለሁ፤
መንፈስ ቅዱስና ሙሽራይቱ “ና!” ይላሉ፤ የሚሰማም “ና!” ይበል፤ የተጠማም ይምጣ፤ የፈለገም የሕይወትን ውሃ ያለ ምንም ዋጋ በነጻ ይጠጣ።