ኢሳይያስ 25:9 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ይህም በሚፈጸምበት ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ “እነሆ፥ እርሱ አምላካችን ነው፤ በእርሱ ስለ ታመንን አድኖናል፤ እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ እኛም በእርሱ ታምነናል፤ እርሱ ስለ ታደገን በደስታ ተሞልተን ሐሴት እናደርጋለን!” ይላሉ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም በዚያ ቀን እንዲህ ይባላል፤ “እነሆ፤ አምላካችን ይህ ነው፤ በርሱ ታመንን፤ እርሱም አዳነን፤ እግዚአብሔር ይህ ነው፤ በርሱ ታመንን፤ በማዳኑም ደስ ይበለን፤ ሐሤትም እናድርግ።” መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በዚያም ቀን፦ እነሆ፥ አምላካችን ይህ ነው፤ ተስፋ አድርገነዋል፥ ያድነንማል፤ ጌታ ይህ ነው፤ ጠብቀነዋል፤ በማዳኑ ደስ ይለናል፤ ሐሤትም እናደርጋለን፥ ይባላል። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በዚያም ቀን፥ “እነሆ፥ አምላካችን ይህ ነው፤ ተስፋ አድርገነዋል፤ ያድናልም፤ እግዚአብሔር ይህ ነው፤ ጠብቀነዋል፤ በመዳናችንም ደስ ይለናል፤ ሐሤትም እናደርጋለን” ይላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በዚያም ቀን፦ እነሆ፥ አምላካችን ይህ ነው፥ ተስፋ አድርገነዋል፥ ያድነንማል፥ እግዚአብሔር ይህ ነው፥ ጠብቀነዋል፥ በማዳኑ ደስ ይለናል ሐሤትም እናደርጋለን ይባላል። |
እግዚአብሔር የታደጋቸው ሰዎች ተመልሰው ይመጣሉ፤ እየዘመሩም ወደ ጽዮን ይገባሉ፤ ዘወትር የደስታን ዘውድ ይቀዳጃሉ፤ ተድላና ደስታንም ያገኛሉ፤ ማዘንና መቃተት ከእነርሱ ይርቃል።
ምድረ በዳዎች በፈኩ አበቦች ይሞላሉ፤ የደስታ መዝሙርም ይዘምራሉ፤ እንደ ሊባኖስ ተራራ ግርማ ያላቸው ይሆናሉ፤ እንደ ቀርሜሎስም ተራራ ወይም እንደ ሻሮን ሸለቆ ክብርን የተጐናጸፉ ይሆናሉ። ሁሉም የእግዚአብሔርን ክብር የአምላካችንንም ግርማ ያያሉ።
ፈሪ ልብ ላላቸው “እነሆ አምላካችሁ ጠላቶቻችሁን ለመበቀልና የበደላቸውንም ዋጋ ለመክፈል መጥቶ ስለሚያድናችሁ በርቱ! አትፍሩ!” በሉአቸው።
ለጽዮን መልካም ነገርን የምታበሥሩ ሆይ! ወደ ከፍተኛ ተራራ ውጡ! እናንተ ለኢየሩሳሌም መልካም ዜናን የምታበሥሩ ሆይ! ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ጩኹ! ጮክ በሉ አትፍሩ! ለይሁዳ ከተሞች፥ “እነሆ፥ አምላካችሁ” በሉ።
ወደ ሰማይ ትበትናቸዋለህ፤ ነፋስም ጠራርጎ ይወስዳቸዋል፤ ዐውሎ ነፋስም ይበትናቸዋል፤ በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል፤ በእኔ በእስራኤል ቅዱስም ትመካለህ።
ነገሥታት አሳዳጊ አባቶችሽ ይሆናሉ፤ እቴጌዎቻቸውም ሞግዚቶችሽ ይሆናሉ፤ ግንባራቸውንም ወደ ምድር ዝቅ አድርገው ይሰግዱልሻል። የእግርሽንም ትቢያ ይልሳሉ፤ ከዚህም የተነሣ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቂአለሽ፤ የእኔን ርዳታ ለማግኘት የሚጠባበቁ ከቶ አያፍሩም።”
“እኔ እግዚአብሔር ጽዮንንና ባድማ የሆኑባትን ቦታዎችዋን ሁሉ አጽናናለሁ፤ ምድረ በዳዋን እንደ ዔደን፥ በረሓዋንም እንደ ገነት አደርጋለሁ፤ በእርስዋም ተድላና ደስታ ይገኛል፤ እንዲሁም የምስጋና መዝሙር ድምፅ ይሰማል።
ልጆች የእናታቸውን ጡት እንደሚጠቡ የአንቺም ልጆች የሕዝቦችንና የነገሥታትን ሀብት በመውሰድ ይጠቀሙበታል፤ አንቺም እኔ እግዚአብሔር አዳኝሽና ታዳጊሽ ኀያሉ የያዕቆብ አምላክ መሆኔን ታውቂአለሽ።
እኔ በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤ ሁለንተናዬም በአምላኬ ሐሴትን ያደርጋል፤ የአበባ አክሊል በራሱ ላይ እንደሚያደርግ ሙሽራ፥ በጌጣጌጥም እንዳሸበረቀች ሙሽሪት አድርጎ፥ የመዳንን ልብስ አልብሶኛል፤ የጽድቅንም መጐናጸፊያ ደርቦልኛል።
ከጥንት ጀምሮ ተስፋቸውን በእርሱ አድርገው ለሚተማመኑበት ወገኖች እነዚያን ሁሉ ድንቅ ነገሮች ያደረገ አምላክ ከአንተ በቀር አልተሰማም፤ አልታየም፤ የተረዳም የለም።
የእስራኤል ሕዝብ እንደ ብርቱ ጦረኞች ይሆናሉ፤ የወይን ጠጅ እንደ ጠጣ ሰውም ደስተኞች ይሆናሉ፤ ልጆቻቸውም ይህን ድል በማስታወስ ደስ ይላቸዋል፤ በእግዚአብሔርም ሐሤት ያደርጋሉ።
ጽዮን ሆይ! ደስ ይበልሽ! ኢየሩሳሌም ሆይ! በደስታ እልል በይ! እነሆ ንጉሥሽ ትሑት ሆኖ፥ በአህያይቱ ማለትም በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ፥ በድል አድራጊነት ወደ አንቺ ይመጣል።
በዚያን ጊዜ በኢየሩሳሌም ስምዖን የሚባል አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም ሕይወቱን ለእግዚአብሔር የሰጠ ጻድቅ ሰው ነበር፤ የእስራኤልን የመዳን ተስፋ ይጠባበቅ ነበር፤ መንፈስ ቅዱስም በእርሱ ላይ ነበር።
በመጨረሻም ወንድሞቼ ሆይ! በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ያንን ከዚህ በፊት የጻፍኩላችሁን ነገር ደግሜ ብጽፍላችሁ እኔን አያሰለቸኝም፤ እናንተን ግን ከስሕተት ሊጠብቃችሁ ይችላል።
እኛ እግዚአብሔርን በመንፈስ የምናመልክና በውጭ በሚታየው ሥርዓት ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ የምንመካ ስለ ሆንን በእውነት ተገርዘናል።
ኢየሱስ ክርስቶስን ያላያችሁት እንኳ ብትሆኑ ትወዱታላችሁ፤ አሁን እንኳ የማታዩት ብትሆኑ ታምኑበታላችሁ፤ በቃላት ሊገለጥ በማይቻልና በከበረ ደስታ ደስ ይላችኋል።
እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት በናፍቆት የምትጠባበቁና በቶሎም እንዲመጣ የምትሠሩ ሁኑ፤ በዚያን ቀን ሰማይ በእሳት ተቃጥሎ ይጠፋል፤ ፍጥረቶችም በእሳት ግለት ይቀልጣሉ፤
እነሆ በደመና ይመጣል፤ የወጉት ሰዎች እንኳ ሳይቀሩ ሰው ሁሉ ያየዋል፤ የምድርም ሕዝቦች ሁሉ በእርሱ ምክንያት ያለቅሳሉ፤ ይህ ነገር እውነት ነው፤ አሜን።