ኢዮሣፍጥ እጅግ ስለ ፈራ ፈቃዱን እንዲገልጥለት ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ ከዚህ በኋላ በመላው አገሪቱ ሕዝቡ ሁሉ እንዲጾም ትእዛዝ አስተላለፈ፤
ዕዝራ 8:21 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እግዚአብሔር ጒዞአችንን እንዲያቃናልን፥ እኛንና ልጆቻችንን፥ እንዲሁም ንብረታችንን ሁሉ እንዲጠብቅልን በእርሱ ፊት ራሳችንን ዝቅ አድርገን እንለምነው ዘንድ በዚያው በአሀዋ ወንዝ አጠገብ ጾም ዐወጅኩ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ራሳችንን በአምላካችን ፊት ዝቅ እንድናደርግ፣ ጕዞውም ለእኛና ለልጆቻችን፣ ለንብረታችንም ሁሉ የተቃና እንዲሆንልን፣ እዚያው በአኅዋ ወንዝ አጠገብ ጾም ዐወጅሁ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በአምላካችን ፊት ራሳችንን ዝቅ እንድናደርግ፥ ከእርሱም የቀናውን መንገድ ለእኛና ለልጆቻችን ለንብረታችንም ሁሉ እንድንለምን በዚያ በአኅዋ ወንዝ አጠገብ ጾም አወጅሁ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በአምላካችን ፊት ራሳችንን እናዋርድ ዘንድ፥ ከእርሱም የቀናውን መንገድ ለእኛና ለልጆቻችን፥ ለንብረታችንም ሁሉ እንለምን ዘንድ በዚያ በአኅዋ ወንዝ አጠገብ ጾምን አወጅሁ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በአምላካችን ፊት ራሳችንን እናዋርድ ዘንድ፥ ከእርሱም የቀናውን መንገድ ለእኛና ለልጆቻችን ለንብረታችንም ሁሉ እንለምን ዘንድ በዚያ በአኅዋ ወንዝ አጠገብ ጾም አወጅሁ። |
ኢዮሣፍጥ እጅግ ስለ ፈራ ፈቃዱን እንዲገልጥለት ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ ከዚህ በኋላ በመላው አገሪቱ ሕዝቡ ሁሉ እንዲጾም ትእዛዝ አስተላለፈ፤
እኔ ዕዝራ ወደ አሀዋ በሚፈሰው ወንዝ አጠገብ መላውን ጉባኤ ሰበሰብኩ፤ በዚያም ሰፍረን ለሦስት ቀኖች ቈየን፤ በዚያም ጉባኤ ውስጥ ከካህናት በቀር ሌዋውያን አለመኖራቸውን ተገነዘብኩ፤
ከአሀዋ ወንዝ ተነሥተን ወደ ኢየሩሳሌም ጒዞ የጀመርነውም የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥራ ሁለተኛው ቀን ነበር፤ በምንጓዝበትም ጊዜ አምላካችን ከእኛ ጋር ስለ ነበር ከጠላት አደጋና ከደፈጣ ተዋጊዎች ሽመቃ ጠበቀን።
በዚሁ ወር በሃያ አራተኛው ቀን የእስራኤል ሕዝብ በአንድነት ተሰበሰቡ፤ ስለ ኃጢአታቸው መጸጸታቸውንና ማዘናቸውን ለመግለጥም ማቅ ለብሰው፥ በራሳቸው ላይ ትቢያ ነስንሰው ጾሙ፤
“ሄደህ በሱሳ የሚገኙትን አይሁድ በአንድነት ሰብስብ፤ ጾም ዐውጃችሁም ለእኔ ጸልዩ፤ እስከ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ምንም ዐይነት ምግብ አትብሉ፤ ምንም ዐይነት መጠጥ አትጠጡ፤ እኔና ደንገጡሮቼም በዚሁ ዐይነት እንቈያለን፤ ከዚህም በኋላ በሕግ የተከለከለ ቢሆንም ደፍሬ ወደ ንጉሡ ዘንድ እገባለሁ፤ ይህን በማድረጌ ብሞትም ልሙት።”
ጠላቶቼ የሚናገሩት ሁሉ ከእውነት የራቀ ስለ ሆነ፥ ከአፋቸው እውነት አይገኝም፤ ሐሳባቸውም በተንኰል የተሞላ ነው፤ ጒሮሮአቸውም እንደ ተከፈተ መቃብር ነው፤ በምላሳቸውም ሰውን ይሸነግላሉ።
ከመንገድ ወጥታችሁ ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ብትባዝኑ ከበስተኋላችሁ “ትክክለኛው መንገድ ይህ ነው! በዚህ ሂድ” የሚለውን ድምፅ ትሰማላችሁ።
በዚያ “ቅዱስ ጐዳና” የሚባል መንገድ ይኖራል፤ እርሱም ለእግዚአብሔር ሰዎች ይሆናል፤ ንጹሕ ያልሆነ ሰው በዚያ መንገድ አይሄድም፤ ሞኞችም ሊሄዱበት አይችሉም።
“ዕውሮችን ሄደውበት በማያውቁት መንገድ እመራቸዋለሁ፤ ቀድሞ ባላወቁትም መንገድ እመራቸዋለሁ፤ በፊታቸው የተጋረደውንም ጨለማ ወደ ብርሃንነት እለውጣለሁ፤ ወጣገባ የሆነውንም ስፍራ አስተካክላለሁ፤ እነዚህ ነገሮች ሁሉ እኔ የምፈጽማቸው ናቸው፤ አልተዋቸውምም።
መራብና መጠማትም አይደርስባቸውም፤ የሚያቃጥል ነፋስ ወይም ፀሐይ አይጐዳቸውም፤ ይህም የሚሆነው የሚራራላቸው እርሱ የውሃ ምንጭ ወደሚገኝበት ቦታ ስለሚመራቸው ነው።
ሕዝቡም “እነሆ እኛ እንጾማለን፤ አንተ ግን አትመለከተንም፤ የማትመለከተንስ ከሆነ ሰውነታችንን ለምን እናዋርዳለን?” ይላሉ። እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፦ “እነሆ እናንተ በምትጾሙበት ጊዜ የልባችሁን ፈቃድ ትፈጽማላችሁ፤ ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ትጨቊናላችሁ፤
እናንተ በምትጾሙበት ጊዜ ሰውነታችሁን ታጐሳቊላላችሁ፤ ራሳችሁን እንደ ሸምበቆ ዝቅ ታደርጋላችሁ፤ አመድ ነስንሳችሁ፥ ማቅም አንጥፋችሁ ትተኛላችሁ? ታዲያ እናንተ ጾም የምትሉት ይህን ነውን? እኔስ በዚህ ዐይነቱ ጾም ደስ የሚለኝ ይመስላችኋልን?
የተለየ የጾም ቀን ዐውጁ! መንፈሳዊ ስብስባ ጥሩ! ሽማግሌዎችንና ሌሎችንም የአገሪቱን ኗሪዎች ሁሉ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ቤት ሰብስቡ፤ በዚያም ወደ እግዚአብሔር ጩኹ።
“ከዚህ የሚከተሉትን መመሪያዎች በሚመጡት ዘመናት ሁሉ ቋሚ ሥርዓት አድርጋችሁ ትጠብቁአቸዋላችሁ፦ ሰባተኛው ወር በገባ በዐሥረኛው ቀን እስራኤላውያንና በእነርሱ መካከል የሚኖሩ መጻተኞች ራሳቸውን ማዋረድ አለባቸው፤ በዚያን ቀን ምንም ሥራ አይሥሩበት።
ለነነዌም ሕዝብ እንዲህ ሲል ዐዋጅ አስነገረ፥ “ከንጉሡና ከመኳንንቱ በተላለፈው ትእዛዝ መሠረት፥ ማንም ሰው ወይም እንስሳ፥ የከብትም ሆነ የበግ መንጋ አንዳች ምግብ አይቅመሱ፤ ውሃም አይጠጡ፤
እግዚአብሔር ወደዚያች ምድር የሚወስደን ለምንድን ነው? እኛ ሁላችን በጦርነት እናልቃለን፤ ሚስቶቻችንና ልጆቻችንም ይማረካሉ፤ ወደ ግብጽ ብንመለስ መልካም አይሆንምን?”
ከዚህም በኋላ የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ወደ ቤትኤል ሄደው አለቀሱ፤ በዚያም ምንም ሳይበሉ እስከ ምሽት በእግዚአብሔር ፊት ተቀምጠው ቈዩ፤ የሚቃጠልና የደኅንነት መሥዋዕት አቀረቡ፤
እነርሱም በአንድነት በምጽጳ ተሰበሰቡ፤ ውሃም ቀድተው ለእግዚአብሔር መባ አድርገው በማፍሰስ በዚያን ዕለት ቀኑን ሙሉ ጾሙ፤ “እኛ እግዚአብሔርን በድለናል” ብለውም ተናዘዙ፤ ሳሙኤል በእስራኤላውያን መካከል ይፈርድ የነበረው በምጽጳ ነበር።