ዘፀአት 15:20 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም የአሮን እኅት ነቢይቱ ማርያም ከበሮዋን አነሣች፤ ሌሎችም ሴቶች ከበሮዎቻቸውን እየመቱና እየጨፈሩ ይከተሉአት ጀመር፤ አዲሱ መደበኛ ትርጒም ከዚያም የአሮን እኅት ነቢዪቱ ማርያም ከበሮዋን አንሥታ ያዘች፤ የቀሩትም ሴቶች ሁሉ ከበሮ ይዘው እያሸበሸቡ ተከተሏት። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) የአሮን እኅት ነቢይቱ ማሪያምም ከበሮ በእጅዋ ወሰደች፤ ሴቶችም ሁሉ ከበሮ በመያዝና በጭፈራ በኋላዋ ወጡ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) የአሮን እኅት ነቢይቱ ማርያምም ከበሮ በእጅዋ ወሰደች፤ ሴቶችም ሁሉ በከበሮና በዝማሬ በኋላዋ ወጡ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) የአሮን እኅት ነቢይቱ ማሪያምም ከበሮ በእጅዋ ወሰደች፤ ሴቶችም ሁሉ በከበሮና በዘፈን በኋላዋ ወጡ። |
የፍልስጥኤማውያን ሴቶች ልጆች እንዳይደሰቱ፥ የአሕዛብ ሴቶች ልጆች እልል እንዳይሉ፥ ይህን ወሬ በጋት አታውሩ፤ በአስቀሎናም አደባባይ አታውጁ።
ታቦቱን ይዘው ወደ ከተማ በሚገቡበት ጊዜ የሳኦል ልጅ ሜልኮል በመስኮት ተመለከተች፤ ንጉሡ ዳዊት እየዘለለ ሲያሸበሽብ አይታም በልብዋ ናቀችው፤
ዳዊትና እስራኤላውያን ሁሉ የበገና፥ የመሰንቆ፥ የከበሮ፥ የጸናጽልና የቃጭል ድምፅ እያሰሙ ለእግዚአብሔር ክብር በመዘመር በሙሉ ኀይላቸው ያሸበሽቡ ነበር።
ሒልቂያ፥ አሒቃም፥ ዐክቦር፥ ሳፋንና ዐሣያ በኢየሩሳሌም አዲስ በተሠራው ሰፈር የምትኖረውን ሑልዳ ተብላ የምትጠራውን ነቢይት ለመጠየቅ ሄዱ፤ የሐርሐስ የልጅ ልጅ የቲቅዋ ልጅ የሆነው ባልዋ ሻሉም የቤተ መቅደስ አልባሳት ኀላፊ ነበር፤ እነርሱም የሆነውን ሁሉ ለነቢይቱ አስረዱአት።
ዳዊት “በገና፥ መሰንቆና ጸናጽል በመሳሰሉ የሙዚቃ መሣሪያዎች እየታጀቡ የደስታ መዝሙሮችን ይዘምሩ ዘንድ ወንድሞቻችሁ የሆኑትን ሌዋውያንን ሹሙአቸው” በማለት የሌዋውያኑን መሪዎች ተናገረ፤
ዓምራምም አሮንና ሙሴ ተብለው የሚጠሩ ሁለት ወንዶች ልጆችና ማርያም ተብላ የምትጠራ አንዲት ሴት ልጅ ወለደ። አሮንም ናዳብ፥ አቢሁ፥ አልዓዛርና ኢታማር ተብለው የሚጠሩ ወንዶች ልጆች ነበሩት።
እኔም “አምላክ ሆይ፥ ጦቢያና ሰንባላጥ ያደረጉትን ሁሉ ተመልከት፤ ፍረድባቸውም፤ ኖዓድያ የተባለችው ሴት ነቢይትና ሌሎቹም ነቢያት እኔን ለማስፈራራት ያደረጉትን ሁሉ አስብ” በማለት ጸለይኩ።
“እግዚአብሔር የተናገረው በሙሴ አማካይነት ብቻ ነውን? በእኛስ አማካይነት ተናግሮ የለምን?” እግዚአብሔርም እነርሱ የተናገሩትን ሁሉ ሰማ።
ዓሞራም በግብጽ የተወለደችውን የሌዊን ሴት ልጅ ዮኬቤድን አግብቶ ነበር፤ እርስዋም አሮንና ሙሴ የተባሉትን ሁለት ወንዶች ልጆችንና ማርያም የተባለችውን አንዲት ሴት ልጅ ወለደችለት።
እንዲሁም በዚያን ጊዜ ከአሴር ነገድ የሆነች የፋኑኤል ልጅ ሐና የምትባል አንዲት ነቢይት ነበረች። በዕድሜዋም በጣም የገፋች ሴት ነበረች፤ ከባልዋ ጋር ሰባት ዓመት ከተቀመጠች በኋላ ባልዋ ሞተባት፤
እንዲሁም ራስዋን ሳትከናነብ የምትጸልይ ወይም የትንቢት ቃል የምትናገር ሴት በሴት ላይ ሥልጣን ያለውን ወንድን ታዋርዳለች፤ ራስዋን የማትከናነብ ሴት እንደ ተላጨች ትቈጠራለች።
ዮፍታሔ በምጽጳ ወዳለው ቤቱ በተመለሰ ጊዜ ሴት ልጁ አታሞ ይዛ እየጨፈረች ልትቀበለው ወጣች፤ ያለ እርስዋም ሌላ ወንድ ወይም ሴት ልጅ አልነበረውም።
ተጠባበቁ፤ በበዓሉ ዕለት የሴሎ ልጃገረዶች ለመጨፈር ሲመጡ እናንተም ከወይኑ ተክል ውስጥ ውጡ፤ እያንዳንዳችሁ ከእነዚያ ልጃገረዶች መካከል እየጠለፋችሁ ሚስት አድርጋችሁ ውሰዱ፤ ወደ ብንያም ግዛትም ይዛችኋቸው ሂዱ።
ከዚያም አልፈህ የፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር ወደሚገኝበት ጊብዓ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ እግዚአብሔር ኮረብታ ትመጣለህ፤ ወደ ከተማይቱም መግቢያ በር በምትደርስበትም ጊዜ በኮረብታው ላይ መሥዋዕት አቅርበው የሚመለሱ የነቢያትን ጉባኤ ታገኛለህ፤ እነርሱም በገና እየደረደሩ፥ ከበሮ እየመቱ፥ ዋሽንት እየነፉ፥ በመሰንቆ ዜማ ሲዘምሩና ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ትንቢት ሲናገሩ ታገኛቸዋለህ።
ዳዊት ጎልያድን ገድሎ ሲመለስና ወታደሮችም ወደየቤታቸው በማምራት ላይ ሳሉ፥ በእስራኤል በሚገኙት ከተሞች ሁሉ የሚኖሩ ሴቶች ሳኦልን ለመቀበል ወጡ፤ እነርሱም በእልልታ እየዘፈኑና እየጨፈሩ፥ የመስንቆ ድምፅ እያሰሙ አታሞ ይመቱ ነበር።