ዘፀአት 15:11 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም “አምላክ ሆይ፥ ከአማልክት መካከል አንተን የሚመስል ማን ነው? በቅድስናስ እንደ አንተ ያለ ባለግርማ ማን ነው? አንተ ያደረግሃቸውን ተአምራትና አስገራሚ ሥራዎች ሊያደርግ የሚችልስ ማን አለ? አዲሱ መደበኛ ትርጒም አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ ከአማልክት መካከል፣ እንደ አንተ ማን አለ? በቅድስናው የከበረ፣ በክብሩ የሚያስፈራ፣ ድንቆችን የሚያደርግ፣ እንደ አንተ ማን አለ? መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ከአማልክት መካከል ጌታ ሆይ፥ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? በቅድስና ባለግርማ፥ በምስጋና የተፈራህ፥ ድንቅንም የምታደርግ፥ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) አቤቱ፦ በአማልክት መካከል አንተን የሚመስል ማን ነው? በቅዱሳንም ዘንድ እንደ አንተ የከበረ ማን ነው? በምስጋና የተደነቅህ ነህ፤ ድንቅንም የምታደርግ ነህ፤ መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) አቤቱ፥ በአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ ማን ነው? በምስጋና የተፈራህ፥ ድንቅንም የምታደርግ፥ በቅድስና የከበረ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? |
እንዲህም አለ፦ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! ለአገልጋዮቹ ቃል ኪዳኑን የሚጠብቅና ከልባቸው ታማኞች እስከ ሆኑ ድረስ ፍቅሩን የሚያጸና በላይ በሰማይ በታችም በምድር እንደ አንተ ያለ አምላክ የለም!
“የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! በሰማይም ሆነ በምድር ሁሉ እንደ አንተ ያለ አምላክ ከቶ የለም፤ አንተ ከሕዝብህ ጋር የገባኸውን ቃል ኪዳን ትጠብቃለህ፤ በፍጹም ልባቸው በመንገድህ ለሚሄዱ ዘለዓለማዊ ፍቅርህን ትገልጥላቸዋለህ።
እናንተ እግዚአብሔርን የምትፈሩት አመስግኑት! እናንተ የያዕቆብ ዘሮች ሁሉ አክብሩት! እናንተ የእስራኤል ዘሮች ሁሉ በፍርሃት ከፍ ከፍ አድርጉት!
ጌታ ሆይ! ሁለመናዬ እንዲህ ብሎ ይናገራል፤ ተበዳዮችን ከበደለኛ የሚያድን፥ ድኾችንና ተጨቋኞችን ከነጣቂዎች የሚጠብቅ እንደ አንተ ያለ ማነው?
ግብጻውያን በእስራኤል ሕዝብ ላይ ታብየው ያን ያኽል አሳፋሪ ድርጊት በመፈጸማቸው ይህን ሁሉ አስደናቂ ነገር ስላደረገ እነሆ፥ እኔም እግዚአብሔር ከአማልክት ሁሉ የሚበልጥ መሆኑን አሁን ዐወቅሁ።”
ስለዚህም እጅግ አስፈሪ የሆኑ ድንቅ ተአምራትን በማድረግ የኀይል ክንዴን ዘርግቼ ግብጻውያንን እቀጣለሁ፤ ከዚያም በኋላ እንድትወጡ ይፈቅድላችኋል።
ንጉሡም “እንግዲያውስ ነገውኑ ጸልይልኝ” አለ። ሙሴም እንዲህ አለ፤ “እንዳልከው አደርጋለሁ፤ አንተም እንደ አምላካችን እንደ እግዚአብሔር ያለ ሌላ አምላክ እንደሌለ በዚያን ጊዜ ታውቃለህ።
ነገር ግን እምቢ ብትል፥ በዓለም ላይ እኔን የመሰለ ሌላ አምላክ እንደሌለ ታውቅ ዘንድ አንተን ራስህን፥ መኳንንትህንና ሕዝብህን በመቅሠፍቴ ኀይል አሁኑኑ እቀጣለሁ።
እኔ ብቻ አምላክ መሆኔንና ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ ዕወቁ፤ በቀድሞ ዘመን የተደረጉትን የጥንቱን ነገሮች አስታውሱ፤ እኔ አምላክ ነኝ፤ እኔንም የሚመስል ሌላ የለም።
ከፍተኛውና ከሁሉ የላቀው፥ ለዘለዓለም የሚኖር ቅዱሱ እንዲህ ይላል፦ “እኔ በተቀደሰና በከፍተኛ ቦታ፥ እንዲሁም ልባቸው ከተሰበረና መንፈሳቸው ትሑት ከሆኑት ጋር እኖራለሁ፤ ይኸውም ትሑት መንፈሳቸውንና የተሰበረ ልባቸውን ለማደስ ነው።
የያዕቆብ አምላክ ግን እንደ እነርሱ አይደለም፤ እርሱ የሁሉ ነገር ፈጣሪ ነው። እስራኤልንም የራሱ ሕዝብ እንዲሆን መርጦታል፤ ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው።
አንበሳ ጥቅጥቅ ካለው ከዮርዳኖስ ጫካ ወጥቶ ለምለም ወደ ሆነው ወደ በጎች መሰማርያ መስክ እንደሚመጣ እኔም በድንገት መጥቼ የኤዶም መሪዎችን አባርራለሁ፤ ከዚህ በኋላ የምመርጠውን እሾማለሁ፤ እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ሊጠይቀኝ የሚደፍር ማን ነው? በፊቴ ቆሞ የሚቋቋመኝስ መሪ ማን ነው?
ኃጢአትን ይቅር የሚል፥ በቀሪውም ሕዝቡ ላይ በደልን የማይቈጥር እንደ አንተ ያለ አምላክ ማን ነው? ምሕረት ማድረግ ስለሚያስደስትህ ቊጣህ ለዘለዓለም የሚቈይ አይደለም።
ነገር ግን ማንን መፍራት እንደሚገባችሁ እነግራችኋለሁ፤ ይኸውም ከገደለ በኋላ ወደ ገሃነም ለመጣል ሥልጣን ያለውን እግዚአብሔርን ነው፤ አዎ፥ እርሱን ብቻ ፍሩ እላችኋለሁ!
‘ልዑል እግዚአብሔር ሆይ! ወደ ፊት ከምታደርጋቸው ታላላቅና አስደናቂ ነገሮች ሁሉ ያሳየኸኝ የመጀመሪያውን ክፍል ብቻ እንደ ሆነ ዐውቃለሁ፤ አንተ የምታደርጋቸውን ታላላቅ ነገሮች የሚያደርግ ሌላ አምላክ በሰማይም ሆነ በምድር የለም።
ወይስ በፈተና፥ በተአምራትና በድንቅ ነገሮች፥ በጦርነት፥ በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ፥ በሚያስፈራ ኀይል፥ በዐይናችሁ እያያችሁት እግዚአብሔር አምላካችሁ እናንተን ከግብጽ ምድር እንዳወጣችሁ ያለ አንድን ሕዝብ ከሌላ ሕዝብ መካከል ወስዶ የራሱ ሕዝብ ለማድረግ የሞከረ ሌላ አምላክ አለን?
ለአውሬው ሥልጣን በመስጠቱ ሰዎች ሁሉ ለዘንዶው ሰገዱለት፤ “አውሬውን የሚመስል ማን ነው? ከእርሱስ ጋር ማን ሊዋጋ ይችላል?” እያሉ ለእርሱም ሰገዱለት።
ጌታ ሆይ! አንተን የማይፈራና ስምህንም የማያከብር ማን ነው? አንተ ብቻ ቅዱስ ነህ፤ የእውነት ፍርድህ ስለ ተገለጠ፥ ሕዝቦች ሁሉ መጥተው በፊትህ ይሰግዳሉ።”
አራቱም እንስሶች እያንዳንዳቸው ስድስት ክንፎች ነበሩአቸው፤ በዙሪያቸውና በውስጣቸውም ዐይኖች ሞልተውባቸዋል፤ ሌሊትና ቀን፦ “ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ ሁሉን የሚችል ጌታ አምላክ፥ የነበረ፥ ያለና የሚመጣውም” ከማለት አያቋርጡም ነበር።