ዘፀአት 10:21 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን “እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋው፤ በእጅ እስከሚዳሰስ ድረስ ጥቅጥቅ ያለ ጨለማ የግብጽን ምድር ይሸፍናል” አለው። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን፣ “በግብጽ ላይ ድቅድቅ ጨለማ እንዲወርድ እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ” አለው። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ጌታም ሙሴን፦ “በግብጽ ምድር ላይ ጨለማ እንዲሆን፥ ማንም ሰው የሚያውቀው ጨለማ እንዲሆን እጅህን ወደ ሰማያት ዘርጋ” አለው። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ፤ በግብፅም ሀገር ላይ ጨለማ ይሁን፤ ጨለማውም የሚዳሰስ ነው” አለው። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እግዚአብሔርም ሙሴን፦ እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ፤ በግብፅም አገር ላይ ሰው የሚዳስሰው ፅኑ ጨለማ ይሁን አለው። |
እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “አሮን በትሩን ወስዶ በግብጽ ምድር በሚገኙት ወንዞች፥ ቦዮችና ኲሬዎች ሁሉ ላይ እንዲዘረጋ ንገረው፤ በዚያን ጊዜ ውሃው ሁሉ ተለውጦ ደም ይሆናል፤ ከእንጨትና ከድንጋይ በተሠሩት የውሃ ማጠራቀሚያ ዕቃዎች እንኳ ሳይቀር በግብጽ ምድር የሚገኘው ውሃ ሁሉ ደም ይሆናል።”
ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን “እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ፤ በረዶም በግብጽ ምድር ሁሉ ላይ ይዘንባል፤ ሕዝቡን፥ እንስሶቹ በእርሻ ያለውን ተክል ሁሉ ይመታል” አለው።
ጥበበኞች ሰዎች መነሻና መድረሻቸውን ያውቃሉ፤ ሞኞች ግን ይህን ሁሉ አያውቁም፤” ይሁን እንጂ ጥበበኛም ሆነ ሞኝ ሁለቱም የሚኖራቸው ዕድል አንድ ዐይነት መሆኑን ተረዳሁ።
በእኩለ ቀን እንደ ዕውር ትደናበራለህ፤ የምትሄድበትንም መንገድ ማግኘት አትችልም፤ የምትሠራውም ነገር ሁሉ አይሳካልህም፤ ዘወትር ጭቈናና ምዝበራ ይደርስብሃል፤ የሚረዳህም ሰው አታገኝም።
ወይስ በፈተና፥ በተአምራትና በድንቅ ነገሮች፥ በጦርነት፥ በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ፥ በሚያስፈራ ኀይል፥ በዐይናችሁ እያያችሁት እግዚአብሔር አምላካችሁ እናንተን ከግብጽ ምድር እንዳወጣችሁ ያለ አንድን ሕዝብ ከሌላ ሕዝብ መካከል ወስዶ የራሱ ሕዝብ ለማድረግ የሞከረ ሌላ አምላክ አለን?
መላእክትን እንኳ ኃጢአት በሠሩ ጊዜ እግዚአብሔር ሳይራራላቸው በጨለመ ጥልቅ ጒድጓድ ውስጥ ሆነው የፍርድን ቀን እንዲጠባበቁ ወደ ገሃነም ጣላቸው፤
የአሳፋሪ ድርጊታቸውን ዐረፋ የሚደፍቁ፥ እንደ ተቈጣ የባሕር ማዕበል ናቸው፤ ድቅድቅ ጨለማ ለዘለዓለም እንደሚጠብቃቸውና፥ እንደሚንከራተቱ ኮከቦች ናቸው።
እንዲሁም ማዕርጋቸውን ባለመጠበቅ ስፍራቸውን የተዉትን መላእክት አስታውሱ፤ እነርሱን እግዚአብሔር እስከ ታላቁ የፍርድ ቀን ድረስ በዘለዓለም እስራት፥ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ጠብቆ አቆይቷቸዋል።
አራተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ፤ የፀሐይ አንድ ሦስተኛ፥ የጨረቃ አንድ ሦስተኛ፥ የኮከቦች አንድ ሦስተኛ ተመታ፤ ስለዚህ የእነርሱ አንድ ሦስተኛቸው ጨለመ፤ በዚህ ዐይነት የቀን አንድ ሦስተኛና የሌሊት አንድ ሦስተኛ ያለ ብርሃን ሆነ።