ነህምያ 9:6 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም አንተ ብቻ እግዚአብሔር ነህ። ሰማያትን፣ ከሰማያት በላይ ያሉትን ሰማያትና የከዋክብታቸውን ሰራዊት ሁሉ፣ ምድርንና በላይዋ ያለውን ሁሉ፣ ባሕሮችንና በውስጣቸውም የሚኖሩትን ሁሉ ፈጥረሃል። ለሁሉም ሕይወትን ትሰጣለህ፤ የሰማይ ሰራዊትም ይሰግዱልሃል። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) አንተ ብቻህን ጌታ ነህ፥ ሰማይንና የሰማያት ሰማይን ሠራዊታቸውንም ሁሉ፥ ምድርንና በእርሷ ያሉትን ሁሉ፥ ባሕሮቹንና በእነርሱ ውስጥ ያለውን ሁሉ፥ ፈጠርህ፥ ለሁሉም ሕይወትን ሰጠሃቸው፤ የሰማይ ሠራዊት ለአንተ ይሰግዳሉ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ከዚህም ሁሉ በኋላ የእስራኤል ሕዝብ እንዲህ ሲሉ ጸለዩ፦ “እግዚአብሔር ሆይ፥ አምላክ አንተ ብቻ ነህ፤ ሰማያትን፥ የሰማያትንም ሰማያት ከነሠራዊታቸው፥ ምድርንና በእርስዋም ላይ የሚገኘውን ሁሉ፥ ባሕሮችንና በእነርሱም ውስጥ የሚገኙትን ሁሉ፥ ፈጠርክ፤ ለሁሉም ሕይወትን ሰጠሃቸው፤ የሰማይ ሠራዊት ይሰግዱልሃል። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ዕዝራም እንዲህ አለ፥ “አንተ ብቻ እግዚአብሔር ነህ፤ ሰማዩንና የሰማያት ሰማይን፥ ሠራዊታቸውንም ሁሉ፥ ምድርንና በእርስዋ ላይ ያሉትን ሁሉ፥ ባሕሮቹንና በእነርሱ ውስጥ ያለውን ሁሉ ፈጥረሃል፤ ሁሉንም ሕያው አድርገኸዋል፤ የሰማዩም ሠራዊት ለአንተ ይሰግዳሉ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) አንተ ብቻ እግዚአብሔር ነህ፥ ሰማዩንና የሰማያት ሰማይን ሠራዊታቸውንም ሁሉ፥ ምድሩንና በእርስዋ ላይ ያሉትን ሁሉ፥ ባሕሮቹንና በእነርሱ ውስጥ ያለውን ሁሉ፥ ፈጥረሃል፥ ሁሉንም ሕያው አድርገኸዋል፥ የሰማዩም ሠራዊት ለአንተ ይሰግዳሉ። |
ከዚያም ሚክያስ እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ፣ የሰማይም ሰራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ።
“ነገር ግን አምላክ በርግጥ በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፤ ሰማይ፣ ከሰማያትም በላይ ያለው ሰማይ እንኳ ይይዝህ ዘንድ አይችልም፤ ታዲያ እኔ የሠራሁት ይህ ቤተ መቅደስማ ምንኛ ያንስ!
ሕዝቅያስም እንዲህ ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ “በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ በምድር መንግሥታት ሁሉ ላይ አንተ ብቻ አምላክ ነህ፤ ሰማይንና ምድርንም ፈጥረሃል።
ሌዋውያኑ ኢያሱ፣ ቀድምኤል፣ ባኒ፣ አሰበንያ፣ ሰራብያ፣ ሆዲያ፣ ሰበንያና ፈታያ፣ “ተነሥታችሁ ቁሙ፤ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የሚኖረውን አምላካችሁን እግዚአብሔርን ወድሱ” አሉ። “ክቡር ስምህ የተመሰገነ ይሁን፤ ከምስጋና ሁሉና ከውዳሴም በላይ ከፍ ከፍ ይበል።
“በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ፣ የእስራኤል አምላክ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ በምድር መንግሥታት ሁሉ ላይ አንተ ብቻ አምላክ ነህ፤ ሰማይንና ምድርንም ፈጥረሃል።
አሁንም እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፤ የምድር መንግሥታት ሁሉ አንተ እግዚአብሔር ብቻ አምላክ መሆንህን ያውቁ ዘንድ፣ አቤቱ ከእጁ አድነን።”
“ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ፣ እርሱ እኔ እንደ ሆንሁ ትረዱ ዘንድ፣ እናንተ ምስክሮቼ፣ የመረጥሁትም ባሪያዬ ናችሁ” ይላል እግዚአብሔር። “ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም፤ ከእኔም በኋላ አይኖርም።
“የእስራኤል ንጉሥና ቤዛ እግዚአብሔር፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የፊተኛውም እኔ ነኝ፤ የኋለኛውም እኔ ነኝ፤ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም።
አትፍሩ፤ አትደንግጡ፤ ይህን አልነገርኋችሁምን? ቀድሞስ አላሳወቅኋችሁምን? ለዚህ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ። ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አለን? ፈጽሞ! ወይም ሌላ ዐለት አለ? የለም! ማንንም አላውቅም።”
“አቤት፣ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ሰማያትንና ምድርን በታላቅ ኀይልህና በተዘረጋች ክንድህ ፈጥረሃል፤ የሚሳንህም አንዳች ነገር የለም።
እነርሱም ይህን በሰሙ ጊዜ ድምፃቸውን በአንድነት ወደ እግዚአብሔር ከፍ አድርገው እንዲህ አሉ፤ “ልዑል ጌታ ሆይ፤ አንተ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንም፣ በውስጣቸውም የሚኖሩትን ሁሉ ፈጥረሃል፤
“እኔ ራሴ እርሱ እንደ ሆንሁ እዩ፤ ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ እገድላለሁ፤ አድናለሁም፤ አቈስላለሁ፤ እፈውሳለሁም፤ ከእጄም የሚያስጥል ማንም የለም።
እርሱ የእግዚአብሔር ክብር ነጸብራቅና የባሕርዩ ትክክለኛ ምሳሌ ሆኖ፣ በኀያል ቃሉ ሁሉን ደግፎ ይዟል። የኀጢአት መንጻት ካስገኘ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ።
በታላቅ ድምፅም፣ “እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ክብርም ስጡት፤ ምክንያቱም የፍርዱ ሰዓት ደርሷል፤ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንና የውሃ ምንጮችን ለፈጠረው ስገዱ” አለ።