ዮሐንስ 19:30 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም ኢየሱስም ኮምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ፣ “ተፈጸመ” አለ፤ ራሱን አዘንብሎ፣ መንፈሱን አሳልፎ ሰጠ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ኢየሱስም ሆምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ “ተፈጸመ” አለ፤ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ኢየሱስም ሆምጣጤውን ከቀመሰ በኋላ “ተፈጸመ!” አለ። ራሱን ዘንበል አድርጎም ነፍሱን ሰጠ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ጌታችን ኢየሱስም ሆምጣጤውን ቀምሶ፥ “ሁሉ ተፈጸመ” አለ፤ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን ሰጠ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ኢየሱስም ሆምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ፦ “ተፈጸመ” አለ፥ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ። |
መድቀቁና መሠቃየቱ ግን የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበር፤ እግዚአብሔር ነፍሱን የኀጢአት መሥዋዕት ቢያደርገውም እንኳ፣ ዘሩን ያያል፤ ዕድሜውም ይረዝማል፤ የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል።
ስለዚህ ድርሻውን ከታላላቆች ጋራ እሰጠዋለሁ፤ ምርኮውን ከኀያላን ጋራ ይካፈላል፤ እስከ ሞት ድረስ ሕይወቱን አሳልፎ በመስጠቱ፣ ከክፉ አድራጊዎችም ጋራ በመቈጠሩ፣ የብዙዎችን ኀጢአት ተሸከመ፤ ስለ ዐመፀኞችም ማለደ።
“ዐመፃን ለማስቆም፣ ኀጢአትን ለማስወገድ፣ በደልን ለማስተስረይ፣ ዘላለማዊ ጽድቅን ለማምጣት፣ ራእይንና ትንቢትን ለማተምና፣ እጅግ ቅዱስ የሆነውን ለመቀባት ስለ ሕዝብህና ስለ ተቀደሰችው ከተማህ ሰባ ሱባዔ ታውጇል።
ከስድሳ ሁለቱ ሱባዔ በኋላ መሲሑ ይገደላል፤ ምንም አይቀረውም። የሚመጣው አለቃ ሰዎችም፣ ከተማውንና ቤተ መቅደሱን ይደመስሳሉ። ፍጻሜውም እንደ ጐርፍ ይመጣል፤ ጦርነት እስከ መጨረሻው ይቀጥላል፤ ጥፋትም ታውጇል።
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሰይፍ ሆይ፤ በእረኛዬ፣ በቅርብ ወዳጄ ላይ ንቃ! እረኛውን ምታ፣ በጎቹም ይበተናሉ፤ እኔም ክንዴን ወደ ታናናሾቹ አዞራለሁ።”
ሕይወቴን በራሴ ፈቃድ አሳልፌ እሰጣለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም፤ አሳልፌ ለመስጠትም ሆነ መልሼ ለመውሰድ ሥልጣን አለኝ፤ ይህን ትእዛዝ የተቀበልሁትም ከአባቴ ነው።”
በደሙም በሆነው እምነት፣ እግዚአብሔር የማስተሰረያ መሥዋዕት አድርጎ አቅርቦታል፤ ይህንም ያደረገው ቀድሞ የተፈጸመውን ኀጢአት ሳይቀጣ በትዕግሥት በማለፍ ጽድቁን ለማሳየት ነው፤
የእምነታችን ጀማሪና ፍጹም አድራጊ የሆነውን ኢየሱስን እንመልከት፤ እርሱ በፊቱ ስላለው ደስታ መስቀሉን ታግሦ፣ የመስቀሉንም ውርደት ንቆ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጧል።