ኤርምያስ 43:12 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም እርሱ የግብጽ አማልክት ቤተ ጣዖቶች ላይ እሳት ይለኵሳል፤ ያቃጥላቸዋልም፣ አማልክታቸውንም ማርኮ ይወስዳል። እረኛ ልብሱን እንደሚጐናጸፍ የግብጽን ምድር ተጐናጽፎ ከዚያ በሰላም ይሄዳል። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በግብጽም አማልክት ቤቶች እሳትን አነድዳለሁ፤ የባቢሎንም ንጉሥ ያቃጥላቸዋል ይማርካቸዋልም፤ እረኛም ደበሎውን እንደሚደርብ እንዲሁ የግብጽን አገር ይደርባል፤ ከዚያም ስፍራ በሰላም ይወጣል። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም በግብጽ የጣዖትን ቤተ መቅደሶች ያቃጥላል፤ ጣዖቶቹን ይማርካል፤ እረኛ ለምዱን እንደሚደርብ ግብጽን በግዛቱ ላይ ደርቦ ምንም ጒዳት ሳይደርስበት በድል አድራጊነት ይወጣል። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በግብፅም አማልክት ቤቶች እሳትን ያነድዳል፤ ያቃጥላቸውማል፤ ይማርካቸውማል፤ እረኛም ልብሱን እንደሚቀምል እንዲሁ የግብፅን ሀገር ይቀምላታል፤ ከዚያም በሰላም ይወጣል። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በግብጽም አማልክት ቤቶች እሳትን ያነድዳል ያቃጥላቸውማል ይማርካቸውማል፥ እረኛም ደበሎውን እንደሚደርብ እንዲሁ የግብጽን አገር ይደርባል፥ ከዚያም በሰላም ይወጣል። |
ከዚያም ልብሱና ፈረሱ እጅግ ከከበሩት ከንጉሡ ልዑላን መሳፍንት በአንዱ እጅ ይሰጥለት። ንጉሡ ሊያከብረው የወደደውን ሰው ያልብሱት፤ በፈረሱም ላይ አስቀምጠውም በከተማዪቱ ዋና ዋና መንገዶች ላይ እየመሩ፣ ‘ንጉሡ ሊያከብረው ለሚወድደው ሰው ይህ ተደርጎለታል’ ይበሉ።”
“እኔም በዚያች ሌሊት በግብጽ ምድር ላይ ዐልፋለሁ፤ ከሰውም ከእንስሳም የተወለደውን የበኵር ልጅ ሁሉ እገድላለሁ፤ የግብጽን አማልክት ሁሉ እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
ስለ ግብጽ የተነገረ ንግር፤ እነሆ፤ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ላይ ተቀምጦ ወደ ግብጽ ይመጣል፤ የግብጽ ጣዖቶች በፊቱ ይርዳሉ፤ የግብጻውያንም ልብ በውስጣቸው ይቀልጣል።
እነሆ፤ አንድ ሰው በፈረሶች በሚሳብ በሠረገላ መጥቷል፤ እንዲህም ሲል መለሰ፣ ‘ባቢሎን ወደቀች፣ ወደቀች! የአማልክቷም ምስሎች ሁሉ፣ ተሰባብረው ምድር ላይ ወደቁ!’ ”
ቤል ተዋረደ፤ ናባው እጅግ ዝቅ አለ፤ ጣዖቶቻቸው በአጋሰስ ተጭነዋል፤ ይዘዋቸው የሚዞሩት ምስሎች ሸክም ናቸው፤ ለደከሙ እንስሳት ከባድ ጭነት ናቸው።
ዐይንሽን ቀና አድርጊ፤ ዙሪያውንም ተመልከቺ፤ ልጆችሽ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ። እኔ ሕያው ነኝ፤ እነዚህን ሁሉ እንደ ጌጥ ትለብሻቸዋለሽ፤ እንደ ሙሽራም ትጐናጸፊያቸዋለሽ” ይላል እግዚአብሔር።
ጽዮን ሆይ፤ ተነሺ፤ ተነሺ፤ ኀይልን ልበሺ፤ ቅድስቲቱ ከተማ፤ ኢየሩሳሌም ሆይ! የክብር ልብስሽን ልበሺ፤ ያልተገረዘ የረከሰም ከእንግዲህ ወደ አንቺ አይገባም።
በእግዚአብሔር እጅግ ደስ ይለኛል፤ ነፍሴ በአምላኬ ሐሤት ታደርጋለች፤ ሙሽራ ራሱን እንደሚያሳምር፣ ሙሽራዪቱም በዕንቈቿ እንደምታጌጥ፣ የድነትን ልብስ አልብሶኛል፤ የጽድቅንም መጐናጸፊያ ደርቦልኛል።
የእስራኤል አምላክ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በቴብስ አምላክ በአሞን ላይ፣ በፈርዖን ላይ፣ በግብጽና በአማልክቷ ላይ፣ በነገሥታቷም ላይ፣ እንዲሁም በፈርዖን በሚታመኑት ላይ ቅጣት አመጣለሁ፤
“በሕዝቦች መካከል ተናገሩ፤ አስታውቁም፤ ሰንደቅ ዐላማ አንሡ፤ ዐውጁ፤ አንዳች ሳታስቀሩ፣ እንዲህ በሉ፤ ‘ባቢሎን ትያዛለች፤ ቤል ይዋረዳል፤ ሜሮዳክ በሽብር ይሞላል፤ ጣዖቶቿ ይዋረዳሉ፤ አማልክቷም ይሸበራሉ።’
ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ግብጽን ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እሰጣለሁ፤ ሀብቷን ሁሉ ያግዛል፤ ለሰራዊቱም ደመወዝ ይሆን ዘንድ ምድሪቱን ይበዘብዛል፤ ይመዘብራልም።
“ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘ጣዖታትን አጠፋለሁ፤ በሜምፊስ ያሉትን ምስሎች እደመስሳለሁ። ከእንግዲህ በግብጽ ገዥ አይኖርም፣ በምድሪቱም ላይ ፍርሀት እሰዳለሁ።
አማልክታቸውን፣ የብረት ምስሎቻቸውን፣ ከብርና ከወርቅ የተሠሩ የከበሩ ዕቃዎቻቸውን ይማርካል፤ ወደ ግብጽም ይወስዳል። ለጥቂት ዓመታትም ከሰሜኑ ንጉሥ ጋራ ከመዋጋት ይቈጠባል።
እግዚአብሔር የምድሪቱን አማልክት ሁሉ በሚደመስስበት ጊዜ፣ በእነርሱ ዘንድ የተፈራ ይሆናል፤ በየባሕሩ ጠረፍ የሚኖሩ ሕዝቦች፣ እያንዳንዳቸው በያሉበት ሆነው ለርሱ ይሰግዳሉ።