ኤርምያስ 23:14 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም በኢየሩሳሌም ባሉ ነቢያትም ላይ፣ የሚዘገንን ነገር አይቻለሁ፤ ያመነዝራሉ፤ በመዋሸትም ይኖራሉ፤ ማንም ከክፋቱ እንዳይመለስ፣ የክፉዎችን እጅ ያበረታሉ፤ በእኔ ዘንድ ሁሉም እንደ ሰዶም፣ ነዋሪዎቿም እንደ ገሞራ ናቸው።” መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በኢየሩሳሌምም ነቢያት መካከል አስደንጋጭ ነገር አይቻለሁ፤ ያመነዝራሉ በሐሰትም ይሄዳሉ፤ ማንም ከክፋቱ እንዳይመለስ የክፉ አድራጊዎችን እጅ ያበረታሉ፤ ሁላቸውም እንደ ሰዶም የሚኖሩባትም እንደ ገሞራ ሆኑብኝ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ነገር ግን በኢየሩሳሌም የሚገኙ ነቢያትም ከዚህ የባሰ ክፋት ሲያደርጉ አይቼአለሁ፤ እነርሱ ያመነዝራሉ፤ ሐሰትም ይናገራሉ፤ ሰዎችን ለክፉ ሥራ ያነሣሣሉ፤ ከዚህም የተነሣ ሕዝቡ ከክፉ ሥራቸው አይመለሱም። ስለዚህ እነርሱ በእኔ ዘንድ እንደ ሰዶምና እንደ ገሞራ ሕዝብ የከፉ ናቸው። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በኢየሩሳሌምም ነቢያት ላይ የሚያስደነግጥን ነገር አይቻለሁ፤ ያመነዝራሉ፤ በሐሰትም ይሄዳሉ፤ ማንም ከክፋቱ እንዳይመለስ የክፉ አድራጊዎችን እጅ ያበረታሉ፤ ሁሉም እንደ ሰዶም፥ የሚኖሩባትም እንደ ገሞራ ሆኑብኝ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በኢየሩሳሌምም ነቢያት ላይ የሚያስደነግጥን ነገር አይቻለሁ፥ ያመነዝራሉ በሐሰትም ይሄዳሉ፥ ማንም ከክፋቱ እንዳይመለስ የክፉ አድራጊዎችን እጅ ያበረታሉ፥ ሁሉም እንደ ሰዶም የሚኖሩባትም እንደ ገሞራ ሆኑብኝ። |
እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “ነቢያቱ በስሜ የሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፤ እኔ አልላክኋቸውም፤ አላዘዝኋቸውም፤ አልተናገርኋቸውምም። የሐሰት ራእይ፣ ሟርት፣ ከንቱ ነገርንና የልባቸውን ሽንገላ ይተነብዩላችኋል።
ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እስኪ አሕዛብን፣ ‘እንዲህ ዐይነት ነገር በመካከላችሁ ተሰምቶ ያውቃል?’ ብላችሁ ጠይቁ። ድንግሊቱ እስራኤል፣ እጅግ ክፉ ነገር አድርጋለች።
እኔን ለሚንቁኝ፣ ‘እግዚአብሔር ሰላም ይሆንላችኋል ብሏል’ ይላሉ፤ የልባቸውን እልኸኝነት ለሚከተሉም ሁሉ፣ ‘ክፉ ነገር አይነካችሁም’ ይሏቸዋል።
“እነሆ፤ ሐሰተኛ ሕልም ተመርኵዘው ትንቢት የሚናገሩትን ነቢያት እቃወማለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “እኔ ሳልልካቸው ወይም ሳልሾማቸው ደፍረው ውሸት ይናገራሉ፤ ሕዝቤንም ያስታሉ፤ ለዚህም ሕዝብ አንዳች አይረቡትም” ይላል እግዚአብሔር።
የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በስሜ የሐሰት ትንቢት ስለሚነግሯችሁ ስለ ቆላያ ልጅ ስለ አክዓብና ስለ መዕሤያ ልጅ ስለ ሴዴቅያስ እንዲህ ይላል፤ “እነዚህን ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ እርሱም ዐይናችሁ እያየ ይገድላቸዋል።
ከባልንጀሮቻቸው ሚስቶች ጋራ በማመንዘርና ያልነገርኋቸውን ቃል በስሜ በሐሰት በመናገር በእስራኤል ዘንድ በደል ፈጽመዋልና። ይህንም እኔ ዐውቃለሁ፤ ምስክር ነኝ” ይላል እግዚአብሔር።
“የብራና ጥቅልል ውሰድ፤ ለአንተም መናገር ከጀመርሁበት ከኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት አንሥቶ እስካሁን ድረስ ስለ እስራኤል፣ ስለ ይሁዳና ስለ ሌሎች ሕዝቦች ሁሉ የነገርሁህን ቃል ሁሉ ጻፍበት፤
በዙሪያቸው ካሉት ከተሞች ጋራ፣ ሰዶምና ገሞራ እንደ ተገለበጡ፣” ይላል እግዚአብሔር፤ “እንዲሁ ማንም በዚያ አይኖርም፤ አንድም ሰው አይቀመጥባትም።
ዕፍኝ ለማይሞላ ገብስና ለቍራሽ እንጀራ ስትሉ ሐሰትን የሚያደምጥ ሕዝቤን እየዋሻችሁ መሞት የማይገባውን በመግደል፣ መኖር የማይገባውንም በማትረፍ በሕዝቤ መካከል አርክሳችሁኛል።
መሳፍንቷ እያገሣ ግዳዩን እንደሚቦጫጭቅ አንበሳ በውስጧ ያሤራሉ፤ ሕዝቡን ይበላሉ፤ ንብረትንና የከበሩ ነገሮችን ይነጥቃሉ፤ ብዙዎችንም ሴቶች መበለት ያደርጋሉ።
“ሰዶምንና ገሞራን እንደ ገለበጥኋቸው፣ አንዳንዶቻችሁን ገለበጥሁ፤ ከእሳት እንደ ተነጠቀ ትንታግ ሆናችሁ፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፤” ይላል እግዚአብሔር።
ይህ ሁሉ የሚሆነው ስለ ያዕቆብ በደል፣ ስለ እስራኤልም ቤት ኀጢአት ነው። የያዕቆብ በደል ምንድን ነው? ሰማርያ አይደለችምን? የይሁዳስ የኰረብታ መስገጃ ምንድን ነው? ኢየሩሳሌም አይደለችምን?
መሪዎቿ በጕቦ ይፈርዳሉ፤ ካህናቷ ለዋጋ ሲሉ ያስተምራሉ፤ ነቢያቷም ለገንዘብ ይጠነቍላሉ። ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ ተደግፈውም፣ “እግዚአብሔር በመካከላችን አይደለምን? ምንም ዐይነት ክፉ ነገር አይደርስብንም” ይላሉ።
“በዚያ ቀን የጣዖታትን ስም ከምድሪቱ አጠፋለሁ፤ ከእንግዲህም አይታሰቡም” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። “ነቢያትንና ርኩስ መንፈስን ከምድሪቱ አስወግዳለሁ።
እንዲሁም ሰዶምና ገሞራ፣ በዙሪያቸውም ያሉ ከተሞች ለሴሰኛነትና ከተፈጥሮ ሥርዐት ውጭ ለሆነ ሩካቤ ሥጋ ራሳቸውን አሳልፈው ሰጡ፤ እነርሱም በዘላለም እሳት በመቀጣት ለሚሠቃዩት ምሳሌ ሆነዋል።
ነገር ግን አውሬው ተያዘ፤ ከርሱም ጋራ በፊቱ ምልክቶችን ያደርግ የነበረው ሐሰተኛው ነቢይ ተያዘ። በእነዚህ ምልክቶች የአውሬውን ምልክት የተቀበሉትንና ለምስሉ የሰገዱትን አሳተ። ሁለቱም በሕይወት እንዳሉ በዲን ወደሚቃጠለው የእሳት ባሕር ተጣሉ።
ነገር ግን ፈሪዎች፣ የማያምኑ፣ ርኩሶች፣ ነፍሰ ገዳዮች፣ አመንዝሮች፣ አስማተኞች፣ ጣዖት አምላኪዎች፣ ውሸተኞች ሁሉ ዕጣ ፈንታቸው በዲንና በእሳት ባሕር ውስጥ መጣል ይሆናል። ይህም ሁለተኛው ሞት ነው።”