ዘፍጥረት 15:13 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “ዘርህ በባዕድ አገር መጻተኛ እንደሚሆን በርግጥ ዕወቅ፤ አራት መቶ ዓመትም በባርነት ተረግጦ ይገዛል። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) አብራምንም አለው፦ “ዘርህ ለእርሱ ባልሆነች ምድር ስደተኞች እንደሚሆኑ በእርግጥ እወቅ፥ ባርያዎች አድርገውም አራት መቶ ዓመት ያስጨንቋቸዋል። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እግዚአብሔር አብራምን እንዲህ አለው፦ “የልጅ ልጆችህ በባዕድ አገር ስደተኞች እንደሚሆኑ ዕወቅ፤ እዚያም በባርነትና በጭቈና ለአራት መቶ ዓመት ያስጨንቁአቸዋል፤ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እግዚአብሔርም አብራምን አለው፥ “ዘርህ ለእነርሱ ባልሆነች ምድር ስደተኞች እንዲሆኑ በእርግጥ ዕወቅ፤ አራት መቶ ዓመታትም ባሪያዎች አድርገው ይገዙአቸዋል፤ ያሠቃዩአቸዋል፤ ያስጨንቋቸዋልም። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) አብራምንም አለው፤ ዘርህ ለእርሱ ባልሆነች ምድር ስደተኞች እንዲሆኑ በእርግጥ እወቅ ባሪያዎች አድርገውም አራት መቶ ዓመት ያስጨንቋቸዋል። |
ይህችን አሁን በእንግድነት የምትኖርባትን የከነዓንን ምድር በሙሉ ለአንተና ከአንተም በኋላ ለዘርህ ለዘላለም ርስት አድርጌ እሰጣቸዋለሁ፤ አምላካቸውም እሆናለሁ።”
ደግሞም፣ “በከነዓን ምድር ራቡ እጅግ የጸና በመሆኑ በጎችና ፍየሎች የሚሰማሩበት በማጣታቸው፣ ለጊዜው እዚህ ለመኖር መጥተናል፤ አሁንም ባሮችህ በጌሤም ምድር እንድንኖር እንድትፈቅድልን እንለምንሃለን” አሉት።
ስለዚህ እያስጨነቁ የግዳጅ ሥራ የሚያሠሯቸውን አሠሪ አለቆች ሾሙባቸው። እስራኤላውያንም ፊቶምና ራምሴ የተባሉ ንብረት ማከማቻ ከተሞችን ለፈርዖን ሠሩለት።
ጭቃ በማስቦካት፣ ጡብ በማሠራትና በዕርሻም ሁሉ እያስጨነቁ ከባድ ሥራ እንዲሠሩ በማድረግ ሕይወታቸውን አስመረሩ፤ ግብጻውያኑ በሚያሠሯቸው ከባድ ሥራ ሁሉ ፈጽሞ አይራሩላቸውም ነበር።
ስለዚህም በግብጽ ከምትቀበሉት መከራ አውጥቼ ማርና ወተት ወደምታፈስሰው ወደ ከነዓናውያን፣ ወደ ኬጢያውያን፣ ወደ አሞራውያን፣ ወደ ፌርዛውያን፣ ወደ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን ምድር አገባችኋለሁ’ ብሏል ብለህ ንገራቸው” አለኝ።
ስለዚህም ከግብጻውያን እጅ ልታደጋቸውና ማርና ወተት ወደምታፈስሰው ሰፊና ለም ወደሆነችው ወደ ከነዓናውያን፣ ኬጢያውያን፣ አሞራውያን፣ ፌርዛውያን፣ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን ምድር ላወጣቸው ወርጃለሁ።
ዐብሯችሁ የሚኖረው መጻተኛ እንደ ገዛ ወገናችሁ ይታይ፤ እንደ ራሳችሁም ውደዱት፤ እናንተም በግብጽ መጻተኞች ነበራችሁና፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።
የምለው እንዲህ ነው፦ ከአራት መቶ ሠላሳ ዓመት በኋላ የተሰጠው ሕግ፣ አስቀድሞ በእግዚአብሔር የጸናውን ኪዳን አፍርሶ የተስፋውን ቃል አይሽርም።
በግብጽ ሳለህ አንተም ባሪያ እንደ ነበርህ፣ ከዚያም አምላክህ እግዚአብሔር በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ እንዳወጣህ አስታውስ፤ ስለዚህ አምላክህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ታከብረው ዘንድ አዘዘህ።