ዘዳግም 6:13 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም አምላክህን እግዚአብሔርን ፍራ፤ እርሱን ብቻ አገልግል፤ በስሙም ማል። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ጌታ እግዚአብሔርን ፍራ፤ እርሱንም አምልክ፥ በስሙም ማል። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም አምላክህን እግዚአብሔርን በመፍራት አክብረው፤ እርሱን ብቻ አምልክ፤ መሐላህም በእርሱ ስም ብቻ ይሁን። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) አምላክህን እግዚአብሔርን ፍራ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ፤ እርሱንም ተከተል በስሙም ማል። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) አምላክህን እግዚአብሔርን ፍራ፤ እርሱንም አምልክ፤ በስሙም ማል። |
መፍራት የሚገባችሁ ግን በታላቅ ኀይልና በተዘረጋች ክንድ ከግብጽ ምድር ያወጣችሁን እግዚአብሔርን ብቻ ነው። ለርሱ ስገዱ፤ ለርሱም መሥዋዕት አቅርቡ።
“የያዕቆብ ቤት ሆይ፤ እናንተ በእስራኤል ስም የተጠራችሁ፣ ከይሁዳ ዘር የተገኛችሁ፣ እናንተ በእግዚአብሔር ስም የምትምሉ፣ በእውነት ወይም በጽድቅ ሳይሆን፣ የእስራኤልን አምላክ የምትጠሩ ይህን ስሙ!
ስለዚህ በምድሪቱ ላይ በረከትን የሚጠራ፣ በእውነት አምላክ ስም ይባረካል፤ በምድሪቱ መሐላን የሚምል፣ በእውነት አምላክ ስም ይምላል፤ ያለፉት ችግሮች ተረስተዋል፤ ከዐይኖቼም ተሰውረዋል።
የሕዝቤን መንገድ በትጋት ቢማሩና ሕዝቤን በበኣል እንዲምል እንዳስተማሩት ሁሉ፣ ‘ሕያው እግዚአብሔርን’ ብለው በስሜ ቢምሉ፣ በዚያ ጊዜ በሕዝቤ መካከል ይመሠረታሉ፤
“ታዲያ፣ እንዴት ይቅር ልልሽ እችላለሁ? ልጆችሽ ትተውኛል፤ እውነተኛውን አምላክ ትተው አማልክት ባልሆኑት ምለዋል፤ እስኪጠግቡ ድረስ መገብኋቸው፤ እነርሱ ግን አመነዘሩ፤ ወደ ጋለሞቶችም ቤት ተንጋጉ።
አሁንም እስራኤል ሆይ፤ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? አምላክህን እግዚአብሔርን እንድትፈራው፣ በመንገዶቹ ሁሉ እንድትሄድ፣ እንድትወድደው፣ በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ እንድታገለግለው፣
ከግብጽ ባወጣችሁና ከባርነት ምድር በዋጃችሁ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ላይ እንድታምፁ ተናግሯልና፣ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንድትከተሉት ካዘዛችሁ መንገድ እንድትመለሱ አድርጓልና፣ ያ ነቢይ ወይም ሕልም ዐላሚ ይገደል፤ ስለዚህ ክፉውን ከመካከልህ አስወግድ።
ታዲያ ለእነርሱም ሆነ ለልጆቻቸው ለዘላለም መልካም እንዲሆንላቸው፣ እኔን እንዲፈሩና ሁልጊዜ ትእዛዞቼን ሁሉ እንዲጠብቁ እንደዚህ ያለ ልብ ቢኖራቸው ምናለ!
ይኸውም፣ የምሰጣችሁን ሥርዐቱንና ትእዛዙን ሁሉ በመጠበቅ፣ ዕድሜያችሁ እንዲረዝም፣ አንተ፣ ልጆችህና ከእነርሱ በኋላ የሚመጡት ልጆቻቸው በሕይወት ዘመናችሁ ሁሉ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትፈሩት ዘንድ ነው።
“እንግዲህ እኔ በጎነትን እንዳሳየኋችሁ ሁሉ፣ እናንተም በጎነትን ለአባቴ ቤት እንድታሳዩ በእግዚአብሔር ማሉልኝ፤ መተማመኛ የሚሆን ምልክትም ስጡኝ፤
“አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩ፤ በፍጹም ታማኝነትም ተገዙለት። የቀድሞ አባቶቻችሁ ከወንዙ ማዶና በግብጽ ያመለኳቸውን አማልክት ከእናንተ አርቁ፤ እግዚአብሔርን ብቻ አምልኩ።
ዳዊት ግን፣ “በፊትህ ሞገስ ማግኘቴን አባትህ በሚገባ ያውቃል፤ እርሱም በልቡ፤ ‘ዮናታን እንዳያዝን ይህን ማወቅ የለበትም’ ብሏል፤ ነገር ግን ሕያው እግዚአብሔርን! በነፍስህ እምላለሁ በእኔና በሞት መካከል አንድ ርምጃ ብቻ ቀርቷል” ብሎ ማለ።
ሳሙኤልም የእስራኤልን ቤት ሁሉ፣ “በፍጹም ልባችሁ ወደ እግዚአብሔር የምትመለሱ ከሆነ፣ ሌሎችን አማልክትና አስታሮትን ከመካከላችሁ አስወግዱ፤ ራሳችሁንም ለእግዚአብሔር አሳልፋችሁ ስጡ፤ እርሱንም ብቻ አምልኩ፤ እርሱም ከፍልስጥኤማውያን እጅ ይታደጋችኋል።” አላቸው።