ዘፀአት 27:21 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም አሮንና ልጆቹ ከምሽት እስከ ንጋት ይበራ ዘንድ የእግዚአብሔር መገኛ ከሆነው ፊት ከቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ለፊት ካለው መጋረጃ ውጪ ያኑሩት፤ ይህም በእስራኤል ሕዝብና ወደፊትም በሚነሣው ትውልድ ዘንድ ቋሚ ሥርዓት ሆኖ ይኑር። አዲሱ መደበኛ ትርጒም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ከመጋረጃው በስተውጭ ይኸውም ከምስክሩ ታቦት ፊት ለፊት፣ አሮንና ወንድ ልጆቹ መብራቶቹን ከምሽት እስከ ንጋት በእግዚአብሔር ፊት እንዲበሩ ያድርጉ፤ ይህም በእስራኤላውያን ዘንድ ከትውልድ እስከ ትውልድ የዘላለም ሥርዐት ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ከመጋረጃው ውጭ ባለው በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በምስክሩ ታቦት ፊት አሮንና ልጆቹ ከማታ እስከ ማለዳ ድረስ በጌታ ፊት ያሰናዱት፤ በእስራኤል ልጆች ዘንድ በትውልዳቸው የዘለዓለም ሥርዓት ይሁን።” የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በምስክሩ ድንኳን ውስጥ በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ካለው መጋረጃ ውጭ አሮንና ልጆቹ ከማታ እስከ ማለዳ ድረስ በእግዚአብሔር ፊት ያብሩት፤ በእስራኤል ልጆች ዘንድ ለልጅ ልጃቸው የዘለዓለም ሥርዐት ይሁን። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በምስክሩ ታቦት ፊት ባለው መጋረጃ ውጭ አሮንና ልጆቹ ከማታ እስከ ማለዳ ድረስ በእግዚአብሔር ፊት እንዲበራ ያሰናዱት፤ በእስራኤል ልጆች ዘንድ ለልጅ ልጃቸው የዘላለም ሥርዓት ይሁን። |
በየቀኑ ጧትና ማታ መዓዛው ጣፋጭ የሆነውን ዕጣንና የሚቃጠለውን የእንስሳት መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ያሳርጋሉ፤ በነጻው ገበታም ላይ የመባ ኅብስት ያቀርባሉ፤ ዘወትር ማታ ማታም ከወርቅ በተሠራው መቅረዝ ላይ ያሉትን ቀንዲሎች ያበራሉ፤ እኛ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እንፈጽማለን፤ እናንተ ግን እግዚአብሔርን ትታችኋል።
እኔ እግዚአብሔር ያደረግኹላችሁን ሁሉ በማስታወስ ይህ ቀን መንፈሳዊ ክብረ በዓል ይሁንላችሁ፤ እርሱንም በሚመጡት ዘመናት ሁሉ እንድታከብሩት ቋሚ ሥርዓት ይሁንላችሁ።”
አሮንና ልጆቹ ዘወትር ወደ ድንኳን ሲገቡ ወይም በተቀደሰው ስፍራ በክህነት ለማገልገል ወደ መሠዊያው ሲቀርቡ ይለብሱታል፥ በዚህ ዐይነት የውስጥ ሰውነታቸው ስለማይጋለጥ ከሞት ይድናሉ፤ ይህ እንግዲህ ለአሮንና ለትውልዱ ሁሉ ጸንቶ የሚኖር ሥርዓት ነው።
ሕዝቤ የአንድነት መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ የእንስሳው ፍርምባና በቀኝ በኩል ያለውን የኋላ እግር ለአሮንና ለልጆቹ ድርሻ ሆኖ እንዲመደብ ወስኛለሁ፤ ውሳኔውም ቋሚ ሥርዓት ይሆናል፤ ይህ እንግዲህ ሕዝቡ ለእኔ ለእግዚአብሔር የሚያቀርበው መባ ነው።
ለሚመጡት ዘመናት ሁሉ ይህ የሚቃጠል መሥዋዕት በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ መቅረብ አለበት፤ እኔ ሕዝቤን የምገናኘውና አንተንም የማነጋግርበት ስፍራ ይኸው ነው።
ስለዚህ እንዳይሞቱ እጃቸውንና እግራቸውን ይታጠቡ፤ ይህም እነርሱና ከእነርሱ በኋላ የሚነሡት ዘሮቻቸው ለዘለዓለም የሚጠብቁት ቋሚ ሥርዓት ነው።”
ከእርሱም ጥቂቱን ወስደህ በመውቀጥ ካላምከው በኋላ ወደ ድንኳኑ ወስደህ በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት እርጨው፤ ይህንንም ዕጣን ፍጹም የተቀደሰ እንዲሆን አድርግ።
“አንተና ልጆችህ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ የሚያሰክር መጠጥ ጠጥታችሁ ወደ መገናኛው ድንኳን እንዳትገቡ ተጠንቀቁ፤ ይህን ብታደርጉ ትሞታላችሁ፤ ይህም ሕግ ከእናንተ በኋላ በሚነሣውም ትውልድ ዘንድ ሁሉ ተጠብቆ መኖር አለበት።
በዓመት አንድ ጊዜ የእስራኤላውያንን ኃጢአት ሁሉ ማስተስረይ የዘለዓለም ሥርዓት ይሆናል።” በዚህም ዐይነት ሙሴ እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ።
የእስራኤል ሕዝብ ከእምነታቸው ለሚያርቁአቸው አጋንንት መሥዋዕት አድርገው እንስሶቻቸውን በየሜዳው በማረድ በእግዚአብሔር ላይ ማመፅ አይገባቸውም፤ እስራኤላውያን ይህን ሥርዓት በሚመጡት ዘመናት ሁሉ ይጠብቁት።
ይህንንም ስጦታ ለእግዚአብሔር ከማቅረባችሁ በፊት ከአዲሱ እህል ጥሬውን ወይም የተቈላውን ወይም እንጀራ ጋግራችሁ አትብሉ። ይህም ድንጋጌ በሚመጡት ዘመናት ሁሉ በልጅ ልጆቻችሁ ተጠብቆ ይኑር።
በዚያም ቀን የአምልኮ ስብሰባ እንዲሆንላችሁ ታውጃላችሁ፤ ምንም ሥራ አትሥሩ፤ ይህ በምትኖሩበት አገር ሁሉ ለልጅ ልጆቻችሁ የዘለዓለም ሥርዓት ነው።
“በድንኳኑ ውስጥ ያለው መብራት ዘወትር ሲበራ እንዲኖር ለማድረግ ተጨምቆ የተጠለለ ንጹሕ የወይራ ዘይት ያመጡልህ ዘንድ እስራኤላውያንን እዘዝ።
አሮን በየምሽቱ መብራቱን ያቀጣጥላል፤ እርሱም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ባለው በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ለፊት ካለው መጋረጃ ውጪ በእግዚአብሔር ፊት እስከ ንጋት ድረስ ሲበራ ያድራል፤ ይህም ድንጋጌ በሚመጡት ዘመናት ሁሉ ተጠብቆ ይኖራል።
ይህም የእስራኤል ሕዝብ ዘወትር ሊፈጽሙት የሚገባ የቃል ኪዳን ሥርዓት ነው። ኅብስቱ የአሮንና የልጅ ልጆቹ ድርሻ ይሆናል፤ እነርሱም በተቀደሰ ቦታ ይብሉት፤ እርሱ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል ቅዱስ መሥዋዕት ሆኖ ከቀረበ በኋላ ለካህናቱ የተለየ ቋሚ ድርሻ ይሆናል።”
ከእስራኤላውያን ወገን ስብ የሆነውን ሥጋ ወይም የእንስሶችን ደም የሚመገብ አይኑር፤ ይህም እስራኤላውያን በሚኖሩበት ዘመንና ቦታ ሁሉ ለዘለዓለሙ ተጠብቆ የሚኖር ቋሚ ሥርዓት ይሁን።
ከዚህም በኋላ ካህኑ ዘይት ካለበት ከላመ ዱቄት በእፍኙ ወስዶና በእህሉ መባ ላይ ያለውን ዕጣን በሙሉ አንሥቶ ለእግዚአብሔር ያቀረበ መሆኑን ለማሳወቅ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው፤ የዚህም መሥዋዕት መዓዛ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት ይሆናል።
በዚያን ቀን እግዚአብሔር ይህን የመሥዋዕት ክፍል ለካህናቱ እንዲሰጡአቸው የእስራኤልን ሕዝብ አዘዘ፤ ይህም በሚመጡት ዘመናት ሁሉ የካህናቱ ድርሻ እንዲሆን ቋሚ ሥርዓት አደረገው።”
ከእንግዲህ ወዲህ ለመገናኛው ድንኳን እንክብካቤ የሚያደርጉትና ለእርሱም ሙሉ ኀላፊነት የሚኖራቸው ሌዋውያን ብቻ ናቸው፤ ይህም ለዘሮቻችሁ የሚተላለፍ የማይሻር ሕግ ሆኖ ይኖራል፤ ሌዋውያን ዘላቂነት ያለው ቋሚ ርስት በእስራኤል ምድር አይኖራቸውም።
ቊጣዬ በእስራኤል ሕዝብ ላይ እንደገና እንዳይገለጥ በተቀደሰው ስፍራና በመሠዊያው ላይ ያለውን የአገልግሎት ኀላፊነት የምትፈጽሙት እናንተና ልጆቻችሁ ብቻ ናችሁ።
ይህን ሕግ ለሚመጡት ዘመናት ሁሉ መጠበቅ ይኖርባችኋል፤ ለማንጻት የሚያገለግለውን ውሃ በላዩ የሚረጨው ሰው ልብሱን ማጠብ ይኖርበታል፤ ውሃውን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ያልነጻ ሆኖ ይቈያል፤
“ብርሃን በጨለማ ውስጥ ይብራ!” ብሎ የተናገረ እግዚአብሔር በክርስቶስ መልክ የሚያበራውን የእግዚአብሔርን ክብር የማወቅ ብርሃን እንዲሰጠን ብርሃኑን በልባችን ውስጥ እንዲበራ አደረገ።
ይህ ሁሉ ነቢያት የተናገሩት እውነት መሆኑን በበለጠ ያረጋግጡልናል፤ ስለዚህ በጨለማ ቦታ ለሚገኝ መብራት ትኲረት እንደምትሰጡ ነቢያት ለተናገሩት ትኲረት ስጡት፤ ይህንንም የምታደርጉት ጎሕ እስኪቀድና አጥቢያ ኮከብ በልባችሁ እስኪገለጥ ድረስ ነው።
ለኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ “ይህ ሰባቱን ኮከቦች በቀኝ እጁ ከያዘውና በሰባቱ የወርቅ መቅረዞች መካከል ከሚመላለሰው የተነገረ ነው፤