ዘፀአት 22:21 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም “እናንተም በግብጽ ምድር መጻተኞች ስለ ነበራችሁ መጻተኛውን በመጨቈን አታጒላሉ፤ አዲሱ መደበኛ ትርጒም “መጻተኛውን አትበድሉት ወይም አታስጨንቁት፤ እናንተ በግብጽ መጻተኛ ነበራችሁና። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) መበለቲቱንና ድሀ አደጉን አታስጨንቁአቸው። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እናንተ በግብፅ ምድር ስደተኞች ነበራችሁና ስደተኛውን አትበድሉት፤ ግፍም አታድርጉበት። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እናንተ በግብፅ ምድር ስደተኞች ነበራችሁና ስደተኛውን አትበድለው፥ ግፍም አታድርግበት። |
መልካም ማድረግንም ተማሩ፤ ፍትሕ እንዳይጓደል አድርጉ፤ የተጨቈኑትን ታደጉ፤ አባትና እናት የሞቱባቸውን ልጆች መብት ጠብቁ፤ ባሎቻቸው የሞቱባቸውንም ሴቶች አቤቱታ ስሙ።”
“እኔ እግዚአብሔር ትክክለኛ ፍርድና እውነት የሆነውን ነገር እንድታደርጉ አዛችኋለሁ፤ አንዱ ሌላውን በመቀማት ግፍ እንዳይሠራ ጠብቁ፤ መጻተኞችን፥ እናትና አባት የሞቱባቸውን ልጆችና፥ ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች በመጨቈን አታንገላቱ፤ በዚህም በተቀደሰ ስፍራ የንጹሕ ሰው ደም አታፍስሱበት።
መጻተኞችን፥ እናትና አባት የሞቱባቸውን ልጆችና፥ ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች በመጨቈን አትበዝብዙ፤ በዚህች ምድር የሚኖሩ ንጹሓን የሆኑ ሰዎችን በግፍ አትግደሉ፤ እንዳትጠፉም ለሐሰተኞች አማልክት አትስገዱ።
ለእስራኤላዊ ወገናችሁ በምታደርጉት ዐይነት መልካም ነገር አድርጉላቸው፤ እንደ ራሳችሁም አድርጋችሁ ውደዱአቸው፤ እናንተም ከዚህ በፊት በግብጽ ምድር ባዕዳን እንደ ነበራችሁ አስታውሱ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።
“በአቅራቢያህ የሚኖር እስራኤላዊ ወገንህ ደኽይቶ ራሱን መርዳት የማይችል ቢሆን በአጠገብህ መኖር ይችል ዘንድ ላስጠጋኸው መጻተኛ በምታደርገው ዐይነት የሚያስፈልገውን ሁሉ በፈቃድህ አድርግለት።
በመካከላችሁ የሚኖሩትን ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች፥ አባትና እናት የሌላቸውን ድኻ አደጎች፥ መጻተኞችንና ችግረኞችን አትጨቊኑ፤ እርስ በርሳችሁ አንዳችሁ ሌላውን ለመጒዳት አታስቡ።’
የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል፦ “ለፍርድ ወደ እናንተ እቀርባለሁ፤ በአስማተኞች፥ በዘማውያን፥ በሐሰት መስካሪዎች፥ የቀን ሠራተኞችን ደመወዝ አታለው በሚያስቀሩ አሠሪዎች፥ ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች፥ እናትና አባት የሌላቸው ልጆችንና ስደተኞችን በሚጨቊኑና እኔን በማይፈሩ ሰዎች ላይ ፈጣን ፍርዴን አስተላልፋለሁ።
“በዚያን ጊዜ እነርሱን እንዲህ ብዬ ነገርኳቸው፤ ‘በሕዝባችሁ መካከል የሚነሣውን የጠብና የክርክር አቤቱታ አድምጡ፤ በራሳችሁ ሕዝብ ወይም በእናንተ ውስጥ በሚኖሩት መጻተኞች መካከል ስለሚነሣው ጠብና ክርክር ሁሉ በትክክል ፍረዱ።
እርሱ እናትና አባት ለሌላቸው ድኻ አደጎችና ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ሴቶች በትክክል ይፈርዳል፤ እርሱ በእኛ ሕዝብ መካከል የሚኖሩትንም መጻተኞች ሁሉ ስለሚወድ ምግብና ልብስ ይሰጣቸዋል።
አንተም በግብጽ ምድር ባሪያ እንደ ነበርክና እግዚአብሔር አምላክህ ነጻ ያወጣህ መሆኑን አስታውስ፤ እኔም ዛሬ ይህን ትእዛዝ የማዝህ በዚህ ምክንያት ነው።
“ ‘መብት በመግፈፍ መጻተኞችን፥ ወላጆቻቸው የሞቱባቸው ልጆችንና ባሎቻቸው የሞቱባቸው መበለቶችን የሚያንገላታ ሁሉ የተረገመ ይሁን!’ “ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይበሉ።