በላይ በሰማይ ወይም በታች በምድር ካለው ወይም ከምድር በታች ወይም በውሃ ውስጥ ከሚኖሩ ነገሮች በማናቸውም ዐይነት ምስል ለራስህ ጣዖትን አታብጅ። አትስገድላቸው ወይም አታምልካቸውም፤ እኔ አምላክህ እግዚአብሔር የሚጠሉኝን ስለ አባቶቻቸው ኀጢአት እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድ ድረስ ልጆቻቸውን የምቀጣ ቀናተኛ አምላክ ነኝ፤
የአሕዛብ ጣዖታት ከብርና ከወርቅ የተሠሩ፣ የሰው እጅ ያበጃቸው ናቸው። አፍ አላቸው፤ አይናገሩም፤ ዐይን አላቸው፤ አያዩም፤ ጆሮ አላቸው፤ አይሰሙም፤ በአፋቸውም እስትንፋስ የለም። እነዚህን የሚያበጁ፣ የሚታመኑባቸውም ሁሉ እንደ እነርሱ ይሁኑ።
“በምድሪቱ ከሚኖሩት ጋራ ቃል ኪዳን እንዳታደርግ ተጠንቀቅ፤ ምክንያቱም አምላኮቻቸውን ተከትለው ባመነዘሩና መሥዋዕትም ባቀረቡላቸው ጊዜ ይጋብዙሃል፤ አንተም መሥዋዕታቸውን ትበላለህ።
በባሉጥ ዛፎች መካከል፣ ቅጠሉ በተንዠረገገ ዛፍ ሥር በዝሙት የምትቃጠሉ፣ በሸለቆዎች፣ በዐለት ስንጣቂዎችም ውስጥ ልጆቻችሁን የምትሠዉ አይደላችሁምን?
“እያንዳንዳቸው ጅሎችና ዕውቀት የለሽ ናቸው፤ የወርቅ አንጥረኛው ሁሉ በሠራው ጣዖት ዐፍሯል፤ የቀረጻቸው ምስሎቹ የሐሰት ናቸው፤ እስትንፋስም የላቸውም።
እርሱም የሰጡትን ወስዶ በመሣሪያ በመቅረጽ በጥጃ ምስል ጣዖት አድርጎ ሠራው፤ ከዚያም እነርሱ፣ “እስራኤል ሆይ፤ ከግብጽ ያወጡህ አማልክት እነዚህ ናቸው” አሉ።
ሁሉም ሰው ጅልና ዕውቀት የለሽ ነው። የወርቅ አንጥረኛው ሁሉ በሠራው ጣዖት ዐፍሯል፤ የቀረጻቸው ምስሎቹ የሐሰት ናቸው፤ እስትንፋስም የላቸውም።
ታዲያ፣ ለጣዖት የተሠዋ ነገርም ሆነ ጣዖቱ ራሱ ዋጋ ያለው ነገር ነው ማለቴ ነውን? እነርሱ ሁሉ ከሙሴ ጋራ ለመተባበር በደመናና በባሕር ተጠመቁ። አይደለም፤ አሕዛብ የሚሠዉት ለእግዚአብሔር ሳይሆን ለአጋንንት ነው፤ ከአጋንንት ጋራ እንድትተባበሩም አልሻም።
“ነገር ግን እግዚአብሔርን ለተዋችሁት ለእናንተ፣ የተቀደሰ ተራራዬን ለረሳችሁት፣ ‘ዕጣ ፈንታ’ ለተባለ ጣዖት ቦታ ላዘጋጃችሁት፣ ‘ዕድል’ ለተባለም ጣዖት ድብልቅ የወይን ጠጅ በዋንጫ ለሞላችሁት፣
“እጄን በይሁዳ፣ በኢየሩሳሌምም በሚኖሩት ሁሉ ላይ አነሣለሁ፤ የበኣልን ትሩፍ፣ የጣዖታቱንና የአመንዝራ ካህናቱን ስም ሁሉ ከዚህ ስፍራ አጠፋለሁ፤
ከዚህም በቀር ኢዮስያስ ሙታን አነጋጋሪዎችንና መናፍስት ጠሪዎችን፣ የየቤተ ሰቡ ሰውን አማልክት፣ ጣዖታትን እንዲሁም በይሁዳና በኢየሩሳሌም የተገኙትን ሌሎች አስጸያፊ ነገሮች ሁሉ አስወገደ፤ ይህን ያደረገውም ካህኑ ኬልቅያስ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ባገኘው መጽሐፍ የተጻፈው የሕጉ ቃል ተፈጻሚነት እንዲኖረው ለማድረግ ነው።
ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ለሞሎክ ይሠዉ ዘንድ በሄኖም ሸለቆ ለበኣል መስገጃ ኰረብቶችን ሠሩ፤ ነገር ግን ይሁዳን ኀጢአት ለማሠራት እንደዚህ ያለውን አስጸያፊ ተግባር እንዲፈጽሙ እኔ አላዘዝሁም፤ ከቶም አላሰብሁም።
ሳኦልም አገልጋዮቹን፣ “እስኪ ሙታን ሳቢ ሴት ፈልጉልኝና ሄጄ ልጠይቃት” አላቸው። እነርሱም፣ “እነሆ፤ ሙታን የምትስብ ሴት በዓይንዶር አለች” አሉት። ስለዚህ ሳኦል ሌላ ልብስ በመልበስ መልኩን ለውጦ ከሁለት ሰዎች ጋራ በሌሊት ወደ ሴቲቱ ሄደ። እርሱም፣ “እባክሽ፣ ጠንቍዪልኝ፤ የምነግርሽንም ሰው አስነሺልኝ” አላት።
ይሁን እንጂ የምነቅፍብህ ጥቂት ነገር አለኝ፤ የእስራኤል ልጆች ለጣዖት የተሠዋ ምግብ እንዲበሉና እንዲሴስኑ በፊታቸው መሰናከያ ያስቀምጥ ዘንድ ባላቅን ያስተማረውን የበለዓምን ትምህርት የሚከተሉ አንዳንድ ሰዎች በመካከልህ አሉ፤
በእነዚህ መቅሠፍቶች ሳይገደሉ የቀሩት ሰዎች አሁንም ከእጃቸው ሥራ ንስሓ አልገቡም፤ አጋንንትን እንዲሁም ማየት ወይም መስማት ወይም መሄድ የማይችሉትን፣ ከወርቅ፣ ከብር፣ ከናስ፣ ከድንጋይና ከዕንጨት የተሠሩትን ጣዖቶች ማምለክ አልተዉም፤ ደግሞም ከነፍስ ግድያቸው፣ ከጥንቈላ ሥራቸው፣ ከዝሙት ርኩሰታቸው ወይም ከስርቆት ተግባራቸው ንስሓ አልገቡም።
የአማልክታቸውን ምስሎች በእሳት አቃጥል፤ በላያቸው የሚገኘውን ብርና ወርቅ አትመኝ፤ ለራስህ አታድርግ፤ አለዚያ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ስለ ሆነ ያሰናክልሃል።
የእነርሱ ጣዖታት ግን የሰው እጅ ያበጃቸው፣ ብርና ወርቅ ናቸው። አፍ አላቸው፤ አይናገሩም፤ ዐይን አላቸው፤ አያዩም፣ ጆሮ አላቸው፤ አይሰሙም፤ አፍንጫ አላቸው፤ አያሸትቱም፤ እጅ አላቸው፤ አይዳስሱም፤ እግር አላቸው፤ አይሄዱም፤ በጕሮሯቸውም ድምፅ አይፈጥሩም።
ጣዖቶቻቸው በኪያር ዕርሻ መካከል እንደ ቆመ ማስፈራርቾ ናቸው፤ የመናገር ችሎታ የላቸውም፤ መራመድም ስለማይችሉ፣ ተሸካሚ ያስፈልጋቸዋል፤ ጕዳት ማድረስም ሆነ፣ መልካምን ነገር ማድረግ ስለማይችሉ፣ አትፍሯቸው።”
“ሕዝቤ ሁለት ኀጢአት ፈጽመዋል፤ ሕያው የውሃ ምንጭ የሆንሁትን፣ እኔን ትተዋል፤ ውሃ መያዝ የማይችሉትን ቀዳዳ የውሃ ማጠራቀሚያ ጕድጓዶች፣ ለራሳቸው ቈፍረዋል።
ነቢይ ወይም ሕልም ዐላሚ ከመካከልህ ተነሥቶ ምልክት ወይም ድንቅ አደርጋለሁ ቢልህ፣ የባርነት ምድር ከሆነው ከግብጽ ካወጣህ ከአምላክህ ከእግዚአብሔር ሊያርቅህ ፈልጓልና እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ውገረው። ከዚያም እስራኤል ሁሉ ሰምተው ይፈራሉ፤ ከመካከልህም ማንም እንደዚህ ያለውን ክፉ ነገር ዳግም አያደርግም። አምላክህ እግዚአብሔር እንድትኖርባቸው ከሚሰጥህ ከተሞች በአንዲቱ ውስጥ እንዲህ ሲባል ብትሰማ፣ ምናምንቴ ሰዎች ከመካከላችሁ ተነሥተው አንተ የማታውቃቸውን፣ “ሌሎች አማልክትን ሄደን እናምልክ” በማለት የከተማቸውን ሕዝብ እያሳቱ ቢሆን፣ ጕዳዩን አጣራ፤ መርምር፤ በሚገባም ተከታተል፤ ነገሩ እውነት ሆኖ ከተገኘና ይህ አስጸያፊ ነገር በመካከልህ መፈጸሙ ከተረጋገጠ፣ በዚያች ከተማ የሚኖሩትን ሁሉ በሰይፍ ግደላቸው፤ ከተማዪቱን ከነሕዝቧና ከነቀንድ ከብቷ ፈጽሞ ደምስሳት። በከተማዪቱ የተገኘውን የምርኮ ዕቃ ሁሉ በአደባባይዋ መካከል ላይ ሰብስበህ፣ ከተማዪቱን ከነምርኮዋ እንዳለ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መሥዋዕት አድርገህ በሙሉ አቃጥል። ለዘላለም እንደ ፈረሰች ትቅር፤ ተመልሳም አትሠራ። እግዚአብሔር ከብርቱ ቍጣው ይመለስ ዘንድ ዕርም ነገሮች በእጅህ አይገኙ፤ እርሱ ምሕረቱን ያሳይሃል፤ ይራራልሃል፤ ለአባቶችህ በመሐላ ተስፋ በሰጠው መሠረት ቍጥርህን ያበዛዋል፤ ይህም የሚሆነው ዛሬ እኔ የምሰጥህን ትእዛዞቹን ሁሉ በመጠበቅና መልካም የሆነውን በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት በማድረግ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ስለ ታዘዝህለት ነው። የተናገረው ምልክት ወይም ድንቅ ቢፈጸም፣ “አንተ የማታውቃቸውን ሌሎች አማልክት እናምልካቸው” ቢልህ፣ አምላካችሁ እግዚአብሔር በፍጹም ልባችሁና በፍጹም ነፍሳችሁ ትወድዱት እንደ ሆነ ያውቅ ዘንድ ሊፈትናችሁ ነውና፣ የዚያን ነቢይ ቃል ወይም ሕልም ዐላሚውን አትስማ።
“ርኩስ መንፈስ ከሰው ከወጣ በኋላ፣ ዕረፍት ፍለጋ ውሃ በሌለበት ስፍራ ይንከራተታል፤ የሚሻውን ዕረፍት ግን አያገኝም። ከዚያም፣ ‘ወደ ነበርሁበት ቤት ተመልሼ ልሂድ’ ይላል፤ ሲመለስም ቤቱ ባዶ ሆኖ፣ ጸድቶና ተዘጋጅቶ ያገኘዋል። ከዚያም በኋላ ሄዶ ከርሱ የከፉ ሌሎች ሰባት ክፉ መናፍስት ይዞ ይመጣል፤ ገብተውበትም በዚያ ይኖራሉ። ለዚያም ሰው ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው ሁኔታ የከፋ ይሆናል። በዚህ ክፉ ትውልድም ላይ እንዲሁ ይሆንበታል።”
ሰዎች፣ የሚያነበንቡትንና የሚያንሾካሽኩትን ሟርተኞችንና መናፍስት ጠሪዎችን ጠይቁ ቢሏችሁ፣ ሕዝቡ አምላኩን መጠየቅ አይገባውምን? በሕያዋን ምትክ ሙታንን መጠየቅ ለምን አስፈለገ?
የሴሰኝነታችሁን ዋጋ ታገኛላችሁ፤ ጣዖት በማምለክ ለፈጸማችሁት ኀጢአት ቅጣት ትሸከማላችሁ፤ በዚያ ጊዜ እኔ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።”
አሁንም ኀጢአትን መሥራት አበዙ፤ ብራቸውን አቅልጠው ለራሳቸው ጣዖት ሠሩ፣ በጥበብ የተሠሩ ምስሎችን አበጁ፤ ሁሉም የእጅ ጥበብ ባለሙያ ናቸው። ስለ እነዚህ ሰዎች እንዲህ ተብሏል፤ “ሰውን መሥዋዕት አድርገው ያቀርባሉ፤ የጥጃ ጣዖቶችንም ይስማሉ!”
ምድራቸውን የምታስለቅቃቸው አሕዛብ፣ መተተኞችን ወይም ሟርተኞችን ያደምጣሉ፤ አንተ ግን ይህን እንድታደርግ አምላክህ እግዚአብሔር አልፈቀደልህም።
እኔም፣ “እያንዳንዳችሁ ዐይኖቻችሁን ያሳረፋችሁባቸውን ርኩስ ምስሎች አስወግዱ፤ በግብጽ ጣዖታትም ራሳችሁን አታርክሱ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ” አልኋቸው።
ሳሙኤልም የእስራኤልን ቤት ሁሉ፣ “በፍጹም ልባችሁ ወደ እግዚአብሔር የምትመለሱ ከሆነ፣ ሌሎችን አማልክትና አስታሮትን ከመካከላችሁ አስወግዱ፤ ራሳችሁንም ለእግዚአብሔር አሳልፋችሁ ስጡ፤ እርሱንም ብቻ አምልኩ፤ እርሱም ከፍልስጥኤማውያን እጅ ይታደጋችኋል።” አላቸው።
ለርዳታ በምትጮኺበት ጊዜ፣ የሰበሰብሻቸው ጣዖቶች እስኪ ያድኑሽ! ነፋስ ጠራርጎ ይወስዳቸዋል፤ ሽውሽውታም ይበትናቸዋል። እኔን መጠጊያው ያደረገ ሰው ግን፣ ምድሪቱን ይወርሳል፤ የተቀደሰ ተራራዬንም ገንዘቡ ያደርገዋል።”
እነዚህ ከሰይፍ የተረፉት፣ ከእኔ ዘወር ባለ አመንዝራ ልባቸውና ጣዖትን በተከተለ አመንዝራ ዐይናቸው የቱን ያህል እንዳሳዘኑኝ፤ በአሕዛብ ምድር ሆነው ያስታውሱኛል፤ ካደረጉት ክፋትና ከፈጸሙት ርኩስ ተግባር ሁሉ የተነሣም ራሳቸውን ይጸየፋሉ።
እንግዲህ፣ ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ ስለ መብላት፣ በዚህ ዓለም ጣዖት ከንቱ እንደ ሆነና ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ እናውቃለን።
ስለዚህ፣ የባቢሎንን ንጉሥ አታገለግሉም የሚሏችሁን ነቢያታችሁን፣ ሟርተኞቻችሁን፣ ሕልመኞቻችሁን፤ መናፍስት ጠሪዎቻችሁንና መተተኞቻቸሁን አትስሙ፤
እንዲህም በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የሕዝብን ነፍስ ለማጥመድ፣ ለአስማታቸው ለእጃቸው አንጓ ሁሉ አሸንክታብ ለሚያሰፉና፣ የተለያየ መጠን ያለውን የራስ መሸፈኛ ለሚያበጁ ሴቶች ወዮላቸው! በውኑ የሕዝቤን ነፍስ እያጠመዳችሁ የራሳችሁን ነፍስ ታድናላችሁን?
“ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ የሕዝብን ነፍስ እንደ ወፍ በምታጠምዱበት አሸንክታብ ላይ ተነሥቻለሁ፤ ከክንዳችሁ ላይ እቀዳድደዋለሁ፤ እንደ ወፍ የምታጠምዱትንም ሕዝብ ነጻ አወጣዋለሁ።
ተራፊም አሳሳች ነገር ይናገራል፤ ሟርተኞች የሐሰት ራእይ ያያሉ፤ የውሸት ሕልም ይናገራሉ፤ ከንቱ መጽናናት ይሰጣሉ፤ ስለዚህ ሕዝቡ እንደ በጎች ተቅበዘበዙ፤ እረኛ በማጣትም ተጨነቁ።
የሥጋ ሥራ ግልጽ ነው፦ ይኸውም ዝሙት፣ ርኩሰት፣ መዳራት፣ የምለውን አስተውሉ! ትገረዙ ዘንድ ብትፈልጉ፣ ክርስቶስ ፈጽሞ ለእናንተ እንደማይበጃችሁ እኔ ጳውሎስ እነግራችኋለሁ። ጣዖትን ማምለክ፣ ሟርት፣ ጥላቻ፣ ጠብ፣ ቅናት፣ ቍጣ፣ ራስ ወዳድነት፣ መለያየት፣ ዐድመኛነት፣
ነገር ግን ፈሪዎች፣ የማያምኑ፣ ርኩሶች፣ ነፍሰ ገዳዮች፣ አመንዝሮች፣ አስማተኞች፣ ጣዖት አምላኪዎች፣ ውሸተኞች ሁሉ ዕጣ ፈንታቸው በዲንና በእሳት ባሕር ውስጥ መጣል ይሆናል። ይህም ሁለተኛው ሞት ነው።”
“ ‘ወደ ሙታን ጠሪዎችና ጠንቋዮች ዘወር በማለት፣ በሚከተላቸውና ከእነርሱም ጋራ በሚያመነዝር ሰው ላይ ጠላት እሆንበታለሁ፤ ከወገኖቹም ለይቼ አጠፋዋለሁ።
“ ‘ከመካከላችሁ ሙታን ጠሪ ወይም መናፍስት ጠሪ የሆነ ማንኛውም ወንድ ወይም ሴት ይገደል፤ በድንጋይም ይወገሩ፤ ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው።’ ”
በመካከልህ ወንድ ወይም ሴት ልጁን በእሳት የሚሠዋ ሟርተኛ ወይም መተተኛ፣ ሞራ ገላጭ፣ ጠንቋይ ወይም በድግምት የሚጠነቍል፣ መናፍስት ጠሪ ወይም ሙት አነጋጋሪ በመካከልህ ከቶ አይገኝ። እነዚህን የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነውና። ከእነዚህ አስጸያፊ ልምዶች የተነሣም አምላክህ እግዚአብሔር እነዚያን አሕዛብ ከፊትህ ያባርራቸዋል።
የምትወርሯቸውንና የምታስለቅቋቸውን አሕዛብ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከፊታችሁ ያስወግዳቸዋል፤ ባስወጣችኋቸውና በምድራቸው በተቀመጣችሁ ጊዜ ግን፣ መሠዊያዎቻቸውን አፍርሱ፤ የማምለኪያ ዐምዶቻቸውን ሰባብሩ፤ የአሼራ ምስል ዐምዶቻቸውን በእሳት አቃጥሉ፤ የአማልክታቸውን ጣዖቶች ቈራርጣችሁ ጣሉ፤ ስማቸውንም ከእነዚያ ስፍራዎች ላይ አጥፉ። ከፊትህ ከጠፉ በኋላ፣ “እነዚህ ሕዝቦች አማልክታቸውን የሚያመልኩት እንዴት ነው? እኔም እንደ እነርሱ አደርጋለሁ” ብለህ በመጠየቅ እንዳትጠመድ ተጠንቀቅ። አምላክህን እግዚአብሔርን በእነርሱ መንገድ ፈጽሞ አታምልክ፤ ምክንያቱም አማልክታቸውን ሲያመልኩ እግዚአብሔር የሚጸየፈውን ሁሉንም ዐይነት ነገር ያደርጋሉና፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን እንኳ ለአማልክታቸው መሥዋዕት አድርገው ያቃጥላሉ።
የገዛ ወንድ ልጁን በእሳት ሠዋ፤ አስማት፣ መተትና ጥንቈላ አደረገ፤ ሙታን ጠሪዎችንና መናፍስት ሳቢዎችን ጠየቀ። ለቍጣ ያነሣሣው ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ክፉ ነገር አደረገ።
እርሱም በሄኖም ልጅ ሸለቆ ወንዶች ልጆቹን በእሳት ሠዋ፤ ሟርት፣ አስማት፣ መተትና ጥንቈላ አደረገ፤ ሙታን ጠሪዎችንና መናፍስት ሳቢዎችን ጠየቀ። ለቍጣ ያነሣሣው ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ክፉ ነገር አደረገ።
እንዲሁም ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ። ጥንቈላና መተት አደረጉ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር ለማድረግ ራሳቸውን ሸጡ፤ ለቍጣም አነሣሡት።
እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “ነቢያቱ በስሜ የሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፤ እኔ አልላክኋቸውም፤ አላዘዝኋቸውም፤ አልተናገርኋቸውምም። የሐሰት ራእይ፣ ሟርት፣ ከንቱ ነገርንና የልባቸውን ሽንገላ ይተነብዩላችኋል።
የባቢሎን ንጉሥ በጥንቈላ ምሪት ለማግኘት በመንታ መንገድ ላይ በሁለቱ ጐዳናዎች መጋጠሚያ ላይ ይቆማል፤ ቀስቶቹን በመወዝወዝ ዕጣ ይጥላል፤ አማልክቱን ያማክራል፤ ጕበትንም ይመረምራል።
ነቢያቷም በሐሰት ራእይና በውሸት ሟርት ይህን ሁሉ ድርጊት ያድበሰብሱላቸዋል፤ እግዚአብሔርም ሳይናገር፣ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል’ ይላሉ።
ኤልያስም በሕዝቡ ፊት ቀርቦ፣ “በሁለት ሐሳብ የምትዋልሉት እስከ መቼ ድረስ ነው? እግዚአብሔር አምላክ ከሆነ እግዚአብሔርን ተከተሉ፤ በኣል አምላክ ከሆነም በኣልን ተከተሉ” አለ። ሕዝቡ ግን አንዲት ቃል አልመለሱም።
ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ለአጋንንት ሠዉ። የወንዶችና የሴቶች ልጆቻቸውን ደም፣ ለከነዓን ጣዖታት የሠዉአቸውን፣ ንጹሕ ደም አፈሰሱ፤ ምድሪቱም በደም ተበከለች።
በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም ዙሪያ በሚገኙ ኰረብቶች ላይ ዕጣን እንዲያጥኑ የይሁዳ ነገሥታት የሾሟቸውን የጣዖት ካህናት አባረረ እንዲሁም ለበኣል፣ ለፀሓይና ለጨረቃ፣ ለስብስብ ከዋክብትና ለመላው የሰማይ ከዋክብት ሰራዊት የሚያጥኑትን አስወገደ።
በያዕቆብ ላይ የሚሠራ አስማት የለም፤ በእስራኤልም ላይ የሚሠራ ሟርት አይኖርም፤ ለያዕቆብና ለእስራኤል፣ ‘እግዚአብሔር ያደረገውን እዩ!’ ይባልላቸዋል።
በዚህ ጊዜ አካዝያስ በሰማርያ ካለው እልፍኝ ሰገነቱ ላይ ሳለ፣ ከዐይነ ርግቡ ሾልኮ ወድቆ ነበርና ታመመ፤ ስለዚህ፣ “ሄዳችሁ ከዚህ ሕመም እድን እንደ ሆነ የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ጠይቁ” ሲል መልእክተኞች ላከ። የእግዚአብሔር መልአክ ግን ቴስብያዊውን ኤልያስን እንዲህ አለው፤ “ተነሥተህ የሰማርያን ንጉሥ መልእክተኞች ለመገናኘት ውጣና፣ ‘የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ለመጠየቅ የምትሄዱ በእስራኤል አምላክ ስለሌለ ነውን?’ ብለህ ጠይቃቸው።
የያዕቆብ ቤት የሆነውን ሕዝብህን ትተሃል፤ እነርሱ በምሥራቅ ሰዎች ከንቱ አምልኮ ተሞልተዋልና፤ እንደ ፍልስጥኤማውያን ያሟርታሉ፤ ከባዕዳን ጋራ አገና ይማታሉ።
አባቱ ሕዝቅያስ ያፈራረሳቸውን የኰረብታ ላይ ማምለኪያ ስፍራዎች መልሶ ሠራ፤ ለበኣሊም መሠዊያዎችን አቆመ፤ የአሼራንም ምስል ዐምዶች ሠራ፤ ለሰማይ ከዋክብት ሰራዊትም ሁሉ ሰገደ፤ አመለካቸውም።
ዐመፅ እንደ ጥንቈላ ያለ ኀጢአት፣ እልኸኝነትም እንደ ጣዖት አምልኮ ያለ ክፉ ነገር ነው። አንተ የእግዚአብሔርን ቃል ስለ ናቅህ፣ እርሱም ንጉሥ እንዳትሆን ንቆሃል።”
ሲጠነቍሉ ከነበሩትም መካከል ብዙዎች መጽሐፋቸውን ሰብስበው በማምጣት በሕዝብ ፊት አቃጠሉ፤ ዋጋቸውም ሲሰላ ዐምሳ ሺሕ ብር ያህል ሆኖ ተገኘ።
የመብራት ብርሃን፣ ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ አይበራም፤ የሙሽራውና የሙሽራዪቱ ድምፅ፣ ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ አይሰማም፤ ነጋዴዎችሽ የዓለም ታላላቅ ሰዎች ነበሩ፤ በአስማትሽም ሕዝቦች ሁሉ ስተዋል።
ወደ ሰማይ ቀና ብለህ ፀሓይን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን፣ የሰማይ ሰራዊትንም ሁሉ በምትመለከትበት ጊዜ፣ ወደ እነርሱ እንዳትሳብና እንዳትሰግድላቸው፣ አምላክህ እግዚአብሔር ከሰማይ በታች ላሉ ሕዝቦች ሁሉ ድርሻ አድርጎ የሰጣቸውንም ነገሮች እንዳታመልክ ተጠንቀቅ።
“በይ እንግዲህ፣ ከልጅነትሽ ጀምሮ የደከምሽባቸውን፣ አስማቶችሽን፣ ብዙ መተቶችን ቀጥዪባቸው፤ ምናልባት ይሳካልሽ፣ ምናልባትም ጠላቶችሽን ታሸብሪባቸው ይሆናል። የተቀበልሽው ምክር ሁሉ ድካም ብቻ ሆኖ አስቀርቶሻል! እነዚያ ከወር እስከ ወር ከዋክብትን አንጋጦ በማየት የሚተነብዩ፣ ኮከብ ቈጣሪዎች እስኪ ይምጡ፤ ከሚደርስብሽም ነገር እስኪ ያድኑሽ።
ይህ ሁሉ የሆነው ቅጥ ባጣች፣ አሳሳችና መተተኛ በሆነች ዘማዊት ምክንያት ነው፤ ይህች የጠንቋዮች እመቤት በዝሙቷ አሕዛብን፣ በጥንቈላዋም ሕዝቦችን ባሪያ ያደረገች ናት።
“የእስራኤል ንጉሥና ቤዛ እግዚአብሔር፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የፊተኛውም እኔ ነኝ፤ የኋለኛውም እኔ ነኝ፤ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም።
እኔም ገብቼ አየሁ፤ እነሆ የሚሳቡ ፍጥረታትና የርኩሳን አራዊት ዐይነት ሁሉ፣ የእስራኤልም ቤት ጣዖታት ሁሉ ዙሪያውን በግንቡ ላይ ተቀርጸው ነበር።
ከአንተ በፊት ከነበሩት ሁሉ ይልቅ አንተ የከፋ ሥራ ሠራህ፤ ለራስህም ከቀለጠ ብረት ሌሎች አማልክትን ሠራህ፤ ቍጣዬን አነሣሣህ፤ ወደ ኋላህም ጣልኸኝ።