የእግዚአብሔር ደስታ ሀዘንህን ሁሉ አጥፍቶ ልብህን በደስታ ሊሞላው ይችላል። ይህ ደስታ በስሜትህ ላይ የተመሰረተ አይደለም፣ በየቀኑ በመንፈስ ቅዱስ ፊት እየገነባኸው የምትሄድ ነው። ከእርሱ ጋር ያለህ ግንኙነት በጥልቅ እንድትረዳው የሚያደርግህ ነው፣ እርሱን በደንብ ስትረዳው ደግሞ የመድኃኒትህን ታላቅነት እያሰብክ ውስጥህ እንደ ወንዝ የሚፈስ የምስጋና ማዕበል ይሞላሃል። ምን ያህል መልካም እንደሆነልህ ስትረዳ አፍህ በሳቅ ይሞላል። የዚህ ዓለም ደስታ በጊዜያዊ ነገሮች ላይ የተመሰረተ እንደሆነ፣ የኢየሱስ ደስታ ግን ለዘላለም እንደሚኖር በዚህ ጊዜ ትረዳለህ።
እግዚአብሔር በዚህ ጊዜ ልጆቹ በእርሱ እንዲጠለሉ ይፈልጋል። እንባ በሚፈስበት ጊዜ እንኳን የምስጋና መዝሙር እንድናቀርብ ይፈልጋል። በእግሩ ስር ስንወድቅ ሙላቱን እናገኛለን፣ እንጽናናለን። በመከራ፣ በፈተና እና በችግር ጊዜ የጌታ ደስታ ብርታታችን ይሆናል፤ ተልእኳችንንም አንተወውም። በእግዚአብሔር ጸጋ የእርሱ ደስታ ይደግፈናል፣ እያንዳንዱን ሁኔታ ለመቋቋምም ብርታት ይሰጠናል። እግዚአብሔር ኃይሌና ጋሻዬ ነው፤ ልቤ በእርሱ ታምኖአል፤ እርዳታም አግኝቻለሁ፤ ስለዚህ ልቤ ደስ ይለዋል፤ በመዝሙሬም አመሰግነዋለሁ (መዝሙር 28:7)።
እርሱንም ሳታዩት ትወድዱታላችሁ፤ አሁን ባታዩትም በርሱ ታምናላችሁ፤ መግለጽ በማይቻልና ክብር በሞላበት ሐሤት ደስ ብሏችኋል፤ የእምነታችሁን ፍጻሜ፣ እርሱም የነፍሳችሁን ድነት እየተቀበላችሁ ነውና።
የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ታማኝነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት ነው። እንደነዚህ ያሉትንም የሚከለክል ሕግ የለም።
ጊዜው መልካም ሲሆን፣ ደስ ይበልህ፤ ጊዜው ክፉ ሲሆን ግን ይህን ዐስብ፤ አምላክ አንዱን እንዳደረገ፣ ሌላውንም አድርጓል፤ ስለዚህ ሰው ስለ ወደ ፊት ሁኔታው፣ ምንም ሊያውቅ አይችልም።
የክርስቶስ ቃል በሙላት ይኑርባችሁ፤ እርስ በርሳችሁ በጥበብ ሁሉ ተማማሩ፤ ተመካከሩ፤ በመዝሙርና በማሕሌት፣ በመንፈሳዊም ቅኔ በማመስገን በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ።
ምድር ሁሉ ለእግዚአብሔር እልል በሉ፤ ውዳሴን አፍልቁ፤ በደስታና በዝማሬ አመስግኑ፤ ለእግዚአብሔር በገና ደርድሩለት፤ በበገናና በዝማሬ ድምፅ ዘምሩለት፤ በእንቢልታና በመለከት ድምፅ፣ በንጉሡ በእግዚአብሔር ፊት እልል በሉ።
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ማደሪያህ ምንኛ የተወደደ ነው! በሌላ ስፍራ ሺሕ ቀን ከመኖር፣ በአደባባይህ አንዲት ቀን መዋል ይሻላል፤ በክፉዎች ድንኳን ከመቀመጥ ይልቅ፣ በአምላኬ ቤት ደጅ መቆም እመርጣለሁ። እግዚአብሔር አምላክ ፀሓይና ጋሻ ነውና፤ እግዚአብሔር ሞገስንና ክብርን ይሰጣል፤ እግዚአብሔር ያለ ነቀፋ የሚሄዱትን፣ መልካም ነገር አይነፍጋቸውም። የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ በአንተ የታመነ ሰው ብፁዕ ነው። ነፍሴ የእግዚአብሔርን አደባባዮች ትናፍቃለች፤ እጅግም ትጓጓለታለች፤ ልቤና ሥጋዬም፣ ለሕያው አምላክ እልል በሉ።
በእግዚአብሔር እጅግ ደስ ይለኛል፤ ነፍሴ በአምላኬ ሐሤት ታደርጋለች፤ ሙሽራ ራሱን እንደሚያሳምር፣ ሙሽራዪቱም በዕንቈቿ እንደምታጌጥ፣ የድነትን ልብስ አልብሶኛል፤ የጽድቅንም መጐናጸፊያ ደርቦልኛል።
እኔ ግን በእግዚአብሔር ቤት፣ እንደ ለመለመ የወይራ ዛፍ ነኝ፤ ከዘላለም እስከ ዘላለም፣ በእግዚአብሔር ምሕረት እታመናለሁ። ስላደረግኸው ነገር ለዘላለም አመሰግንሃለሁ፤ ስምህ መልካም ነውና፣ ስምህን ተስፋ አደርጋለሁ፤ በቅዱሳንም መካከል አመሰግንሃለሁ።
የእምነታችን ጀማሪና ፍጹም አድራጊ የሆነውን ኢየሱስን እንመልከት፤ እርሱ በፊቱ ስላለው ደስታ መስቀሉን ታግሦ፣ የመስቀሉንም ውርደት ንቆ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጧል።
የሁሉ ዐይን አንተን በተስፋ ይጠብቃል፤ አንተም ምግባቸውን በወቅቱ ትሰጣቸዋለህ። አንተ እጅህን ትዘረጋለህ፤ የሕያዋን ፍጥረታትንም ሁሉ ፍላጎት ታረካለህ።
ወንድሞቼ ሆይ፤ ልዩ ልዩ መከራ ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት፤ የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አያመጣምና። ስለዚህ ርኩሰትንና ተንሰራፍቶ የሚገኘውን ክፋትን አስወግዳችሁ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን፣ በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በትሕትና ተቀበሉ። ቃሉ የሚናገረውን አድርጉ እንጂ ሰሚዎች ብቻ ሆናችሁ ራሳችሁን አታታልሉ። ቃሉን የሚሰማ፣ ነገር ግን የሚለውን የማይፈጽም ሰው ፊቱን በመስተዋት እንደሚያይ ሰው ነው፤ ራሱንም አይቶ ይሄዳል፤ ወዲያውም ምን እንደሚመስል ይረሳል፤ ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹም ሕግ ተመልክቶ የሚጸና፣ የሰማውን የሚያደርግና የማይረሳ ሰው በሥራው ብሩክ ይሆናል። አንደበቱን ሳይገታ፣ ልቡን እያሳተ ሃይማኖተኛ ነኝ የሚል ሰው፣ ራሱን ያታልላል፤ ሃይማኖቱም ከንቱ ነው። በእግዚአብሔር አብ ፊት ንጹሕና ነውር የሌለበት ሃይማኖት ይህ ነው፤ ወላጆቻቸው የሞቱባቸውን ልጆችና ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች በችግራቸው መርዳትና ከዓለም ርኩሰት ራስን መጠበቅ ነው። ምክንያቱም የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንደሚያስገኝ ታውቃላችሁ።
“ጌታውም፣ ‘ደግ አድርገሃል፤ አንተ መልካም ታማኝ ባሪያ፤ በትንሽ ነገር ላይ ታማኝ ስለ ሆንህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው።
በጽዮን ያዘኑትን እንዳረጋጋ፣ በዐመድ ፈንታ፣ የውበት አክሊል እንድደፋላቸው፣ በልቅሶ ፈንታ፣ የደስታ ዘይት በራሳቸው ላይ እንዳፈስስላቸው፣ በትካዜ መንፈስ ፈንታ፣ የምስጋና መጐናጸፊያ እንድደርብላቸው ልኮኛል፤ እነርሱም የክብሩ መግለጫ እንዲሆኑ፣ እግዚአብሔር የተከላቸው፣ የጽድቅ ዛፎች ተብለው ይጠራሉ።
ምነው ለእስራኤል የሚሆን መዳን ከጽዮን በወጣ! እግዚአብሔር የሕዝቡን ምርኮ በሚመልስበት ጊዜ፣ ያዕቆብ ደስ ይበለው፤ እስራኤልም ሐሤት ያድርግ።
እግዚአብሔር ቸር ነውና አመስግኑ፤ ፍቅሩም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል። ሕዝቦች ሁሉ ከበቡኝ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ስም አስወግዳቸዋለሁ። መክበቡንስ በየአቅጣጫው ከበቡኝ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ስም አስወግዳቸዋለሁ። እንደ ንብ መንጋ ከበቡኝ፤ ነገር ግን እንደሚነድድ እሾኽ ከሰሙ፤ በርግጥም በእግዚአብሔር ስም አስወግዳቸዋለሁ። ተገፍትሬ ልወድቅ ተንገደገድሁ፤ እግዚአብሔር ግን ረዳኝ። እግዚአብሔር ብርታቴና ዝማሬዬ ነው፤ አዳኝ ሆነልኝ። በጻድቃን ድንኳን የእልልታና የሆታ ድምፅ፣ እንዲህ እያለ ያስተጋባል፤ “የእግዚአብሔር ቀኝ እጅ ብርቱ ሥራ ሠራች፤ የእግዚአብሔር ቀኝ እጅ ከፍ ከፍ አለች፤ የእግዚአብሔር ቀኝ እጅ ብርቱ ሥራ ሠራች።” ተርፌ በሕይወት እኖራለሁ እንጂ አልሞትም፤ የእግዚአብሔርንም ሥራ ገና እናገራለሁ። መገሠጹን እግዚአብሔር እጅግ ገሥጾኛል፤ ነገር ግን ለሞት አሳልፎ አልሰጠኝም። የጽድቅን ደጆች ክፈቱልኝ፤ በዚያ ገብቼ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። የእስራኤል ሕዝብ፣ “ምሕረቱ ለዘላለም ነው” ይበል።
እግዚአብሔር የተቤዣቸው ይመለሳሉ፤ በዝማሬ ወደ ጽዮን ይገባሉ፤ ዘላለማዊ ደስታን ይጐናጸፋሉ፤ ደስታና ሐሤት ይቀድማሉ፤ ሐዘንና ትካዜም ይሸሻሉ።
ስጦታው በገዛ ፈቃድና በፍጹም ልብ የቀረበ በመሆኑ፣ አለቆቹ ለእግዚአብሔር ስላደረጉት የበጎ ፈቃድ ስጦታ ሕዝቡ ደስ አለው፤ ንጉሥ ዳዊትም እንደዚሁ እጅግ ደስ አለው።
አንተን የሚፈልጉ ሁሉ ግን፣ ሐሤት ያድርጉ፤ በአንተም ደስ ይበላቸው፤ ዘወትር የአንተን ማዳን የሚወድዱ፣ “እግዚአብሔር ከፍ ከፍ ይበል!” ይበሉ።
በዚያ ቀን እንዲህ ይባላል፤ “እነሆ፤ አምላካችን ይህ ነው፤ በርሱ ታመንን፤ እርሱም አዳነን፤ እግዚአብሔር ይህ ነው፤ በርሱ ታመንን፤ በማዳኑም ደስ ይበለን፤ ሐሤትም እናድርግ።”
እግዚአብሔር የጽዮንን ምርኮ በመለሰ ጊዜ፣ ሕልም እንጂ እውን አልመሰለንም። በዚያ ጊዜ አፋችን በሣቅ፣ አንደበታችንም በእልልታ ተሞላ፤ በዚያ ጊዜም በሕዝቦች መካከል፣ “እግዚአብሔር ታላቅ ነገር አደረገላቸው” ተባለ።
ዳዊትም በዜማ መሣሪያ፣ ማለትም በመሰንቆ፣ በበገናና በጸናጽል እየታጀቡ የደስታ ዜማዎችን የሚያዜሙ መዘምራንን ከወንድሞቻቸው መካከል እንዲሾሙ ለሌዋውያኑ መሪዎች ነገራቸው።
“መንግሥተ ሰማይ በዕርሻ ውስጥ የተደበቀ ሀብት ትመስላለች፤ አንድ ሰው ባገኛት ጊዜ መልሶ ሸሸጋት፤ ከመደሰቱም የተነሣ፣ ሄዶ ያለውን ሁሉ በመሸጥ ያን የዕርሻ ቦታ ገዛ።
በተጨነቅሁ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤ እግዚአብሔርም መለሰልኝ፤ ከመጠበብም አወጣኝ። እግዚአብሔር ከእኔ ጋራ ነው፤ አልፈራም፤ ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?
ነህምያም፣ “ሂዱ፤ ጥሩ ምግብ በመብላት፣ ጣፋጩን በመጠጣት ደስ ይበላችሁ፤ ምንም የተዘጋጀ ነገር ለሌላቸውም ካላችሁ ላይ ከፍላችሁ ላኩላቸው። ይህች ቀን ለጌታችን የተቀደሰች ናት፤ የእግዚአብሔር ደስታ ብርታታችሁ ስለ ሆነ አትዘኑ” አላቸው።
አንተን መጠጊያ የሚያደርጉ ሁሉ ግን ደስ ይበላቸው፤ ዘላለም በደስታ ይዘምሩ፤ ስምህን የሚወድዱ በአንተ ደስ እንዲላቸው፣ ተከላካይ ሁንላቸው። እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ጻድቃንን ትባርካቸዋለህ፤ በሞገስህም እንደ ጋሻ ትከልላቸዋለህ።
እነሆ፣ አምላክ ድነቴ ነው፤ እታመናለሁ፣ ደግሞም አልፈራም፤ ጌታ እግዚአብሔር ብርታቴና ጋሻዬ ነው፤ ድነቴም ሆኗል።” ከድነቴ ምንጮች ውሃ በደስታ ትቀዳላችሁ።
እግዚአብሔር የተቤዣቸው ይመለሳሉ፤ በዝማሬ ወደ ጽዮን ይገባሉ፤ ዘላለማዊ ደስታን ይጐናጸፋሉ፤ ደስታና ሐሤት ይቀድማሉ፤ ሐዘንና ትካዜም ይሸሻሉ።