ጻድቃን ሲጮኹ፣ እግዚአብሔር ይሰማቸዋል፤ ከመከራቸውም ሁሉ ያድናቸዋል። እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል።
በልዑል መጠጊያ የሚኖር፣ በሁሉን ቻይ አምላክ ጥላ ሥር ያድራል። ክፉ ነገር አያገኝህም፤ መቅሠፍትም ወደ ድንኳንህ አይገባም፤ በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ፣ እግርህም ከድንጋይ ጋራ እንዳይሰናከል፤ በእጆቻቸው ያነሡህ ዘንድ፣ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዝልሃል። በአንበሳና በእፉኝት ላይ ትጫማለህ፤ ደቦሉን አንበሳና ዘንዶውን ትረግጣለህ። “ወድዶኛልና እታደገዋለሁ፤ ስሜን ዐውቋልና እከልለዋለሁ። ይጠራኛል፤ እመልስለታለሁ፤ በመከራው ጊዜ ከርሱ ጋራ እሆናለሁ፤ አድነዋለሁ፤ አከብረዋለሁ። ረዥም ዕድሜን አጠግበዋለሁ፤ ማዳኔንም አሳየዋለሁ።” እግዚአብሔርን፣ “መጠጊያዬ፣ ምሽጌ፣ የምታመንብህ አምላኬ” እለዋለሁ።
በሰዎች ሁሉ ላይ ከደረሰው የተለየ ፈተና አልደረሰባችሁም፤ እግዚአብሔር ታማኝ ነው፤ ስለዚህ ከምትችሉት በላይ እንድትፈተኑ አይተዋችሁም፤ ነገር ግን በምትፈተኑበት ጊዜ ፈተናውን መታገሥ እንድትችሉ፣ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል።
በውሃ ውስጥ በምታልፍበት ጊዜ፣ ከአንተ ጋራ እሆናለሁ፤ ወንዙን ስትሻገረው፣ አያሰጥምህም፤ በእሳት ውስጥ ስትሄድ፣ አያቃጥልህም፤ ነበልባሉም አይፈጅህም።
እግዚአብሔር ከክፉ ሁሉ ይጠብቅሃል፤ ነፍስህንም ይንከባከባታል። እግዚአብሔር ከአሁን ጀምሮ እስከ ዘላለም፣ መውጣትህንና መግባትህን ይጠብቃል።
ተራሮች ቢናወጡ፣ ኰረብቶች ከስፍራቸው ቢወገዱ እንኳ፣ ለአንቺ ያለኝ ጽኑ ፍቅር አይናወጥም፤ የገባሁትም የሰላም ቃል ኪዳን አይፈርስም” ይላል መሓሪሽ እግዚአብሔር።
በዚህ ብቻ ሳይሆን በመከራችንም ሐሤት እናደርጋለን፤ ምክንያቱም መከራ ትዕግሥትን እንደሚያስገኝ እናውቃለን። ትዕግሥት ጽናትን፣ ጽናት የተፈተነ ባሕርይን፣ የተፈተነ ባሕርይ ተስፋን፤
የእግዚአብሔርን ቸርነት በሕያዋን ምድር እንደማይ ሙሉ እምነቴ ነው። እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ አይዞህ፣ በርታ፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ።
ስለዚህም አምላክህ እግዚአብሔር አምላክ መሆኑን ዕወቅ፤ እርሱ ለሚወድዱትና ትእዛዞቹን ለሚጠብቁት የፍቅሩን ኪዳን እስከ ሺሕ ትውልድ ድረስ የሚጠብቅ ታማኝ አምላክ ነው።
በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ፣ ከምስጋናም ጋራ ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ እንጂ ስለ ማንኛውም ነገር አትጨነቁ። ከማስተዋል በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም፣ ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።
“ስለዚህ እላችኋለሁ፣ ስለ ኑሯችሁ ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? በማለት አትጨነቁ። ሕይወት ከምግብ፣ ሰውነትስ ከልብስ አይበልጥምን? እስኪ የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱም፤ በጐተራም አያከማቹም፤ ይሁን እንጂ የሰማዩ አባታችሁ ይመግባቸዋል። እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን?
እንግዲህ በእኛ ውስጥ እንደሚሠራው እንደ ኀይሉ መጠን፣ ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ እጅግ አብልጦ ማድረግ ለሚቻለው፣ በቤተ ክርስቲያን እንዲሁም በክርስቶስ ኢየሱስ፣ በዘመናት ሁሉ ከዘላለም እስከ ዘላለም ለርሱ ክብር ይሁን! አሜን።
እግዚአብሔርን ደጅ ጠናሁት፤ እርሱም ዘንበል አለልኝ፤ ጩኸቴንም ሰማ። ጽድቅህን በልቤ አልሸሸግሁም፤ ታማኝነትህንና ማዳንህን እናገራለሁ፤ ምሕረትህንና እውነትህን፣ ከታላቅ ጉባኤ አልደበቅሁም። እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህን አትንፈገኝ፤ ቸርነትህና እውነትህ ዘወትር ይጠብቁኝ፤ ስፍር ቍጥር የሌለው ክፋት ከብቦኛልና፤ የኀጢአቴ ብዛት ስለ ያዘኝ ማየት ተስኖኛል፤ ከራሴ ጠጕር ይልቅ በዝቷል፤ ልቤም ከድቶኛል። እግዚአብሔር ሆይ፤ ታድነኝ ዘንድ ፈቃድህ ይሁን፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔን ለመርዳት ፍጠን። ነፍሴን ለመንጠቅ የሚፈልጉ ይፈሩ፤ ይዋረዱም፤ ጕዳቴንም የሚሹ፣ ተዋርደው በመጡበት ይመለሱ። በእኔ ላይ፣ “ዕሠይ! ዕሠይ!” የሚሉ፣ በራሳቸው ዕፍረት ይደንግጡ። አንተን የሚፈልጉ ሁሉ ግን፣ ሐሤት ያድርጉ፤ በአንተም ደስ ይበላቸው፤ ዘወትር የአንተን ማዳን የሚወድዱ፣ “እግዚአብሔር ከፍ ከፍ ይበል!” ይበሉ። እኔ ግን ችግረኛና ድኻ ነኝ፤ ጌታ ግን ያስብልኛል። አንተ ረዳቴና ታዳጊዬም ነህና፤ አምላኬ ሆይ፤ አትዘግይ። ከሚውጥ ጕድጓድ፣ ከሚያዘቅጥ ማጥ አወጣኝ፤ እግሮቼን በዐለት ላይ አቆመ፤ አካሄዴንም አጸና። ለአምላካችን የሚሆን ውዳሴ፣ አዲስ ዝማሬን በአፌ ላይ አኖረ፤ ብዙዎች ያያሉ፤ ይፈራሉም፤ በእግዚአብሔር ይታመናሉ።
ነፍሴ ዕረፍት የምታገኘው በእግዚአብሔር ብቻ ነው፤ ድነቴም የሚመጣልኝ ከርሱ ዘንድ ነው። በዝርፊያ አትታመኑ፤ በቅሚያም ተስፋ አታድርጉ፤ በዚህ ብትበለጽጉም፣ ልባችሁ ይህን አለኝታ አያድርግ። እግዚአብሔር አንድ ነገር ተናገረ፤ እኔም ይህን ሁለት ጊዜ ሰማሁ፤ ኀይል የእግዚአብሔር ነው። ጌታ ሆይ፤ ምሕረትም የአንተ ነው፤ አንተ ለእያንዳንዱ፣ እንደ ሥራው ትከፍለዋለህ። ዐለቴና መድኀኒቴ እርሱ ብቻ ነው፤ መጠጊያዬም እርሱ ነው፤ ከቶም አልናወጥም።
የርኅራኄ አባት፣ የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። እኛ ራሳችን ከእግዚአብሔር በተቀበልነው መጽናናት፣ በመከራ ያሉትን ማጽናናት እንድንችል፣ እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል።
እግዚአብሔር ከቶ ሊዋሽ አይችልም፤ እርሱ በሁለት በማይለወጡ ነገሮች በፊታችን ያለውን ተስፋ ለመያዝ ወደ እርሱ ለሸሸን ለእኛ ብርቱ መጽናናት እንድናገኝ አድርጓል።
እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አምላኬ ነህ፤ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፤ ስምህንም አወድሳለሁ፤ አስቀድሞ የታሰበውን፣ ድንቅ ነገር፣ በፍጹም ታማኝነት አድርገሃልና።
በእኔ ኑሩ፤ እኔም በእናንተ እኖራለሁ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ካልሆነ በቀር ብቻውን ፍሬ ሊያፈራ አይችልም፤ እናንተም በእኔ ካልኖራችሁ ፍሬ ልታፈሩ አትችሉም። “እኔ የወይን ተክል ነኝ፤ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ማንም በእኔ ቢኖር እኔም በርሱ ብኖር፣ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል፤ ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና።
ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማን ነው? ችግር ነው ወይስ ሥቃይ፣ ወይስ ስደት፣ ወይስ ራብ፣ ወይስ ዕራቍትነት፣ ወይስ አደጋ፣ ወይስ ሰይፍ? ይህም፣ “ስለ አንተ ቀኑን ሙሉ እንገደላለን፤ እንደሚታረዱ በጎች ተቈጥረናል” ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። ምንም አይለየንም፤ በዚህ ሁሉ በወደደን በርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ይህን ተረድቻለሁ፤ ሞትም ይሁን ሕይወት፣ መላእክትም ይሁኑ አጋንንት፣ ያለውም ይሁን የሚመጣው፣ ወይም ማንኛውም ኀይል፣ ከፍታም ይሁን ጥልቀት ወይም የትኛውም ፍጥረት፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ካለው ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን አይችልም።
በእግዚአብሔር ፊት ለመቅረብ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ ማንኛውንም ነገር እንደ ፈቃዱ ብንለምን እርሱ ይሰማናል። የምንለምነውን ሁሉ እንደሚሰማን ካወቅን፣ የለመንነውንም ነገር እንደ ተቀበልን እናውቃለን።
“እናንተ ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ በልቤ የዋህና ትሑት ነኝና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ “ይመጣል ተብሎ የሚጠበቀው አንተ ነህ? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ሲል ጠየቀ። ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነውና።”
ነፍሳችን እግዚአብሔርን ተስፋ ታደርጋለች፤ እርሱ ረዳታችንና ጋሻችን ነው። ልባችን በርሱ ደስ ይለዋል፤ በቅዱስ ስሙ ታምነናልና። እግዚአብሔር ሆይ፤ ተስፋ ባደረግንህ፣ በእኛ ላይ ምሕረትህ ትሁን።
ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፤ ጸንታችሁ ቁሙ፤ በምንም ነገር አትናወጡ። ለጌታ ሥራ ዘወትር የምትተጉ ሁኑ፤ ምክንያቱም ለጌታ የምትደክሙት በከንቱ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ።
በእግዚአብሔር የሚታመኑ፣ ሳትናወጥ ለዘላለም እንደምትኖር እንደ ጽዮን ተራራ ናቸው። ተራሮች ኢየሩሳሌምን እንደ ከበቧት፣ ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም፣ እግዚአብሔር በሕዝቡ ዙሪያ ነው።
እኔ፣ “እግሬ አዳለጠኝ” ባልሁ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህ ደግፎ ያዘኝ። የውስጤ ጭንቀት በበዛ መጠን፣ ማጽናናትህ ነፍሴን ደስ አሰኛት።
ፍርሀት በሚይዘኝ ጊዜ፣ መታመኔን በአንተ ላይ አደርጋለሁ። ቃሉን በማመሰግነው አምላክ፣ በእግዚአብሔር ታምኛለሁ፤ አልፈራም፤ ሥጋ ለባሽ ምን ሊያደርገኝ ይችላል?
የጽድቅ ፍሬ ሰላም፣ የጽድቅ ውጤትም ጸጥታና ለዘላለም ያለ ሥጋት ይሆናል። ሕዝቤ ሰላማዊ በሆነ መኖሪያ፣ በሚያስተማምን ቤት፣ ጸጥ ባለም ስፍራ ዐርፎ ይኖራል።
አንተ መሸሸጊያዬ ነህ፤ ከመከራ ትጠብቀኛለህ፤ በድል ዝማሬም ትከብበኛለህ። ሴላ አስተምርሃለሁ፤ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ እመክርሃለሁ፤ በዐይኔም እከታተልሃለሁ።
እናንተም በመጨረሻው ዘመን ሊገለጥ የተዘጋጀው ድነት እስኪመጣ ድረስ በእምነት አማካይነት በእግዚአብሔር ኀይል ተጠብቃችኋል። አሁን በብዙ ዐይነት ፈተና ውስጥ ሆናችሁ ለጥቂት ጊዜ መከራን ብትቀበሉም እንኳ በዚህ እጅግ ደስ ይላችኋል።
ምክንያቱም፣ እግዚአብሔር አስቀድሞ እንድንመላለስባቸው ያዘጋጀልንን መልካም የሆኑትን ሥራዎች እንድንሠራ በክርስቶስ ኢየሱስ የተፈጠርን የእግዚአብሔር እጅ ሥራዎች ነን።
ስለዚህ ታላቅ ዋጋ ያለውን መታመናችሁን አትጣሉ። የእግዚአብሔርን ፈቃድ ፈጽማችሁ የተስፋ ቃሉን እንድትቀበሉ፣ ጸንታችሁ መቆም ያስፈልጋችኋል።
“ወድዶኛልና እታደገዋለሁ፤ ስሜን ዐውቋልና እከልለዋለሁ። ይጠራኛል፤ እመልስለታለሁ፤ በመከራው ጊዜ ከርሱ ጋራ እሆናለሁ፤ አድነዋለሁ፤ አከብረዋለሁ።
የእግዚአብሔር ምሕረት ግን፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም በሚፈሩት ላይ ነው፤ ጽድቁም እስከ ልጅ ልጅ ድረስ በላያቸው ይሆናል፤ ኪዳኑን በሚጠብቁት ላይ፣ ትእዛዙንም ለመፈጸም በሚተጕት ላይ ይሆናል።
የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋራ ሆኖ ይመሰክርልናል። ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ የክብሩ ተካፋዮች እንሆን ዘንድ በርግጥ የመከራው ተካፋዮች ብንሆን፣ የእግዚአብሔር ወራሾች፣ ከክርስቶስ ጋራ ዐብረን ወራሾች ነን።
እርሱንም ሳታዩት ትወድዱታላችሁ፤ አሁን ባታዩትም በርሱ ታምናላችሁ፤ መግለጽ በማይቻልና ክብር በሞላበት ሐሤት ደስ ብሏችኋል፤ የእምነታችሁን ፍጻሜ፣ እርሱም የነፍሳችሁን ድነት እየተቀበላችሁ ነውና።
እንግዲህ እነዚህን የመሳሰሉ ብዙ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፣ ሸክም የሚሆንብንን ሁሉ፣ በቀላሉም ተብትቦ የሚይዘንን ኀጢአት አስወግደን በፊታችን ያለውን ሩጫ በጽናት እንሩጥ። አባቶቻችን መልካም መስሎ እንደ ታያቸው ለጥቂት ጊዜ ይቀጡን ነበር፤ እግዚአብሔር ግን የቅድስናው ተካፋዮች እንድንሆን ለእኛ ጥቅም ሲል ይቀጣናል። ቅጣት ሁሉ በወቅቱ የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፤ በኋላ ግን ለለመዱት ሰዎች የጽድቅና የሰላም ፍሬ ያስገኝላቸዋል። ስለዚህ የዛለውን ክንዳችሁንና የደከመውን ጕልበታችሁን አበርቱ። ዐንካሳው እንዲፈወስ እንጂ የባሰውኑ እንዳያነክስ “ለእግራችሁ ቀና መንገድ አብጁ።” ከሰው ሁሉ ጋራ በሰላም ለመኖር የሚቻላችሁን ሁሉ አድርጉ፤ ለመቀደስም ፈልጉ፤ ያለ ቅድስና ማንም ጌታን ማየት አይችልም። ከእናንተ ማንም የእግዚአብሔር ጸጋ እንዳይጐድልበት፣ ደግሞም መራራ ሥር በቅሎ ችግር እንዳያስከትልና ብዙዎችን እንዳይበክል ተጠንቀቁ። ለአንድ ጊዜ መብል ሲል ብኵርናውን እንደ ሸጠው እንደ ዔሳው፣ ማንም ሴሰኛ ወይም እግዚአብሔርን የማያከብር ሆኖ እንዳይገኝ ተጠንቀቁ። በኋላም ይህንኑ በረከት ሊወርስ በፈለገ ጊዜ እንደ ተከለከለ ታውቃላችሁ፤ በረከቱን በእንባ ተግቶ ቢፈልግም ለንስሓ ስፍራ ሊያገኝ አልቻለም። ሊዳሰስ ወደሚችለውና በእሳት ወደሚቃጠለው ተራራ፣ ወደ ጨለማው፣ ወደ ጭጋጉና ወደ ዐውሎ ነፋሱ አልደረሳችሁም፤ ወደ መለከት ድምፅ ወይም ቃልን ወደሚያሰማ ድምፅ አልመጣችሁም፤ የሰሙትም ሌላ ቃል ተጨምሮ እንዳይናገራቸው ለመኑ። የእምነታችን ጀማሪና ፍጹም አድራጊ የሆነውን ኢየሱስን እንመልከት፤ እርሱ በፊቱ ስላለው ደስታ መስቀሉን ታግሦ፣ የመስቀሉንም ውርደት ንቆ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጧል።
እግዚአብሔር ሁልጊዜ ይመራሃል፤ ፀሓይ ባቃጠለው ምድር ፍላጎትህን ያሟላል፤ ዐጥንትህን ያበረታል፤ በውሃ እንደ ረካ የአትክልት ቦታ፣ እንደማይቋርጥም ምንጭ ትሆናለህ።
አሁን በብዙ ዐይነት ፈተና ውስጥ ሆናችሁ ለጥቂት ጊዜ መከራን ብትቀበሉም እንኳ በዚህ እጅግ ደስ ይላችኋል። እነዚህ ነገሮች በእናንተ ላይ የደረሱት፣ በእሳት ተፈትኖ ቢጠራም፣ ጠፊ ከሆነው ወርቅ ይልቅ እጅግ የከበረው እምነታችሁ፣ እውነተኛ መሆኑ እንዲረጋገጥና ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ምስጋናን፣ ክብርንና ውዳሴን እንዲያስገኝላችሁ ነው።
በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ፣ ለጥቂት ጊዜ መከራ ከተቀበላችሁ በኋላ እርሱ ራሱ መልሶ ያበረታችኋል፤ አጽንቶም ያቆማችኋል።
እግዚአብሔር ግን ምሕረት ሊያደርግላችሁ ይታገሣል፤ ርኅራኄም ሊያሳያችሁ ይነሣል። እግዚአብሔር የፍትሕ አምላክ ነውና፣ እርሱን በመተማመን የሚጠባበቁት ብፁዓን ናቸው!
ስለዚህ ከቶ የማይናወጥ መንግሥት ስለምንቀበል እግዚአብሔርን እናመስግን፤ ደግሞም ደስ በሚያሠኘው መንገድ በአክብሮትና በፍርሀት እናምልከው፤
እግዚአብሔርን ደጅ እጠናለሁ፤ ነፍሴም በትዕግሥት ትጠብቀዋለች፤ በቃሉም ተስፋ አደርጋለሁ። ዘብ ዐዳሪ ንጋትን ከሚጠባበቅ ይልቅ፣ አዎን፤ ዘብ ዐዳሪ ንጋትን ከሚጠባበቅ ይልቅ፣ ነፍሴ ጌታን ትጠባበቃለች።
በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔ ዐውቃቸዋለሁ፤ እነርሱም ይከተሉኛል፤ እኔ የዘላለም ሕይወት እሰጣቸዋለሁ፤ ከቶ አይጠፉም፤ ከእጄም ሊነጥቃቸው የሚችል ማንም የለም።
“ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ አንኳኩ፣ በሩም ይከፈትላችኋል። የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፤ የሚፈልግም ያገኛል፤ ለሚያንኳኳም ይከፈትለታል።
እንግዲህ በእምነት ስለ ጸደቅን፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከእግዚአብሔር ጋራ ሰላም አለን። የእግዚአብሔር ጠላቶች ሳለን በልጁ ሞት ከርሱ ጋራ ከታረቅን፣ ዕርቅን ካገኘን በኋላ፣ በሕይወቱማ መዳናችን እንዴት የላቀ አይሆንም! ይህ ብቻ አይደለም። ነገር ግን አሁን ዕርቅን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ ሐሤት እናደርጋለን። ስለዚህ ኀጢአት በአንድ ሰው በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ ሁሉ፣ ሞትም በኀጢአት በኩል ገብቷል፤ በዚሁ መንገድ ሞት ወደ ሰዎች ሁሉ መጣ፤ ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤ ሕግ ከመሰጠቱ በፊት ኀጢአት በዓለም ላይ ነበር፤ ነገር ግን ሕግ በሌለበት ኀጢአት አይቈጠርም። ይሁን እንጂ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ባሉት፣ እንደ አዳም ሕግን በመጣስ ኀጢአት ባልሠሩት ላይ እንኳ ሞት ነገሠ፤ አዳም ይመጣ ዘንድ ላለው አምሳሉ ነበረ። ነገር ግን ስጦታው እንደ በደሉ መጠን አይደለም፤ በአንድ ሰው መተላለፍ ብዙዎቹ ከሞቱ፣ የእግዚአብሔር ጸጋና በአንዱ ሰው፣ ይኸውም በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የመጣው ስጦታ ለብዙዎች እንዴት አብልጦ ይትረፈረፍ! ደግሞም የእግዚአብሔር ስጦታ እንደ አንዱ ሰው የኀጢአት ውጤት አይደለም፤ ምክንያቱም ፍርዱ የአንድን ሰው ኀጢአት ተከትሎ ኵነኔን አመጣ፤ ስጦታው ግን አያሌ መተላለፍን ተከትሎ ጽድቅን አመጣ። በአንድ ሰው መተላለፍ ምክንያት ሞት በዚህ ሰው በኩል የነገሠ ከሆነ፣ የእግዚአብሔርን የተትረፈረፈ ጸጋና የጽድቅ ስጦታ የተቀበሉት፣ በአንዱ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እንዴት አብልጠው በሕይወት አይነግሡ! ከእንግዲህ በአንድ ሰው መተላለፍ የተነሣ ኵነኔ በሁሉ ሰው ላይ እንደ መጣ፣ እንዲሁም በአንዱ የጽድቅ ሥራ ለሰው ሁሉ ሕይወትን የሚሰጥ ጽድቅ ተገኘ። በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኀጢአተኞች እንደ ሆኑ፣ በአንዱ ሰው መታዘዝ ደግሞ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ። በርሱም በኩል አሁን ወደ ቆምንበት ጸጋ በእምነት መግባት ችለናል፤ የእግዚአብሔርንም ክብር ተስፋ በማድረግ ሐሤት እናደርጋለን።
እንዲሁም በርሱ የተጠራችሁለት ተስፋ፣ ይህም በቅዱሳኑ ዘንድ ያለውን ክቡር የሆነውን የርስቱን ባለጠግነት ምን እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ የልባችሁ ዐይኖች እንዲበሩ ለእኛ ለምናምነውም ከሁሉ በላይ ታላቅ የሆነውን ኀይሉን እንድታውቁ እጸልያለሁ። ይህም ኀይል እንደ እርሱ ታላቅ ብርታት አሠራር፣
ለእናንተ ያለኝን ዕቅድ እኔ ዐውቃለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ዕቅዱም ፍጻሜው ያማረና ተስፋ የሚሰጣችሁ፣ የሰላም ሐሳብ እንጂ ለክፉ አይደለም።
በዘላለም ኪዳን ደም የበጎች ታላቅ እረኛ የሆነውን ጌታችን ኢየሱስን ከሞት ያስነሣው የሰላም አምላክ፣ ፈቃዱን እንድታደርጉ በመልካም ነገር ሁሉ ያስታጥቃችሁ፤ ደስ የሚያሠኘውንም በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእኛ ያድርግ፤ ለርሱ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን። አሜን።
ስለዚህ እርሱ በወሰነው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከእግዚአብሔር ብርቱ እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤ እርሱ ስለ እናንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በርሱ ላይ ጣሉት።
እግዚአብሔር ሆይ፤ ቃልህ በሰማይ፣ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል። ጕልማሳ መንገዱን እንዴት ያነጻል? በቃልህ መሠረት በመኖር ነው። ታማኝነትህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ሁሉ ይኖራል፤ ምድርን መሠረትሃት፤ እርሷም ጸንታ ትኖራለች።
በውስጥ ሰውነታችሁ እንድትጠነክሩ፣ ከክብሩ ባለጠግነት በመንፈሱ በኩል ኀይል እንዲሰጣችሁ እጸልያለሁ፤ ይኸውም በእምነት ክርስቶስ በልባችሁ እንዲያድር ነው። ደግሞም ሥር ሰድዳችሁ፣ በፍቅር ታንጻችሁ፣