የእግዚአብሔር ፍቅር ሁሉንም ገደብ ያልፋል። ንፁህና ርኅሩኅ ፍቅር ነው፤ ሁሉንም ነገር ለአንተ ለመስጠት የተዘጋጀ። በአንዳች ሁኔታ ላይ የተመሠረተ አይደለም፤ ነገር ግን ለአንተ ለመሞት አንድያ ልጁን የላከው የቅዱሱ አምላክ እምነት ላይ የተመሠረተ ነው። ይህም ከአባትና ከልጅ ጋር እንዳለው ግንኙነት ከእርሱ ጋር እንድትኖር ያስችልሃል።
ቀደም ሲል ሁላችንም በስህተታችንና በድክመታችን ምክንያት ከእግዚአብሔር ፊት ተለይተን ነበርን። ነገር ግን ኢየሱስን በልባችን ስንቀበል የእግዚአብሔር ልጆች እንሆናለን። ዘላለማዊው አምላክ ከእርሱ ጋር እንድትቀርብ ያደረገልህን ሁሉ አስብበት። የማይነፃፀረውን ፍቅሩን አመስግንና በቅድስናው ፊት በቅንነት ኑር።
እርሱ የሚኮራበት ልጅ ሁን፤ በሰማይ ሆኖ ሲያይህ የሚያስደስተው ልጅ ሁን። በፍጹም ልብህ ውደደው። ጥልቅ ጭንቀቶችህን የምትነግረው፣ የሚያስፈልግህን የምትጠይቀው፣ ድክመቶችህን የምታሳየው የመተማመን ድፍረት ይኑርህ። እርሱ በፍፁም አይኮንንህም፤ በተቃራኒው እርሱ በጣም ይወድሃል፤ የሚፈልገው እንድታውቀውና ሁልጊዜ እንድትታዘዘው ብቻ ነው።
እግዚአብሔር ድንቅ፣ ርኅሩኅ፣ ታጋሽ፣ የሚገስጽና የሚያርም አባት ነው። ነገር ግን መልካም ሥራህንም የሚክስ ነው። ወላጆችህ ቢተዉህም እግዚአብሔር ግን በፍፁም አይተውህም። ብቻህን አይደለህም። እርሱ ሊጠብቅህ፣ ሊንከባከብህና "አትፍራ እኔ እረዳሃለሁ" ሊልህ ከአንተ ጋር ነው። ከሁሉ በላይ የሆነ፣ በሁሉም የሚሠራና በሁሉም ውስጥ ያለ የሁሉም አምላክና አባት ነው። ኤፌሶን 4:6
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባትና አምላክ ይባረክ፤ እርሱ ከታላቅ ምሕረቱ የተነሣ በኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት መነሣት ምክንያት ለሕያው ተስፋ በሚሆን አዲስ ልደት፣
የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን እንድንጠራ አብ አትረፍርፎ ያፈሰሰልን ፍቅር ምንኛ ታላቅ ነው! እኛም እንዲሁ ልጆቹ ነን። ዓለም እኛን የማያውቀንም እርሱን ስላላወቀው ነው።
የርኅራኄ አባት፣ የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። እኛ ራሳችን ከእግዚአብሔር በተቀበልነው መጽናናት፣ በመከራ ያሉትን ማጽናናት እንድንችል፣ እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል።
ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር፣ “አባ፣ አባት” ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ ወደ ልባችን ላከ። ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅም ስለ ሆንህ፣ እግዚአብሔር ወራሽ አድርጎሃል።
እርሱ ከጨለማ አገዛዝ ታደገን፤ ወደሚወድደው ልጁ መንግሥትም አሻገረን፤ በርሱም ቤዛነትን በደሙ አግኝተናል፤ ይህም የኀጢአት ይቅርታ ነው።
እስኪ የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱም፤ በጐተራም አያከማቹም፤ ይሁን እንጂ የሰማዩ አባታችሁ ይመግባቸዋል። እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን?
ልጄ ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ተግሣጽ አትናቅ፤ በዘለፋውም አትመረር፤ አባት ደስ የሚሰኝበትን ልጁን እንደሚቀጣ ሁሉ፣ እግዚአብሔርም የሚወድደውን ይገሥጻልና።
አብርሃም ባያውቀን፣ እስራኤልም ባያስታውሰን እንኳ፣ አንተ እኮ አባታችን ነህ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አባታችን ነህ፤ ከጥንትም ቢሆን ስምህ “ቤዛችን” ነው።
ኢየሱስም፣ “ገና ወደ አብ ስላላረግሁ፣ አትንኪኝ፤ ይልቁንስ ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ፣ ‘ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ፣ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዐርጋለሁ’ ብሏል ብለሽ ንገሪአቸው” አላት።
እናንተ ግን ለድኾች ስትሰጡ፣ ቀኝ እጃችሁ የሚያደርገውን ግራ እጃችሁ አይወቅ፤ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፤ እግዚአብሔር ዛሬ ታይቶ ነገ ወደ እሳት የሚጣለውን የሜዳ ሣር እንዲህ የሚያለብስ ከሆነ፣ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁ? ስለዚህ፣ ‘ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን?’ ብላችሁ አትጨነቁ፤ አሕዛብ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ለማግኘት አጥብቀው ይሻሉና፤ የሰማዩ አባታችሁም እነዚህ ሁሉ ለእናንተ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል። ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን ፈልጉ፤ እነዚህም ሁሉ ይጨመሩላችኋል። ስለዚህ ለነገ በማሰብ አትጨነቁ፤ የነገ ጭንቀት ለነገ ይደር፤ እያንዳንዱ ዕለት የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለውና። ምጽዋታችሁ በስውር ይሁን፤ በስውር የተደረገውን የሚያይ አባታችሁም ዋጋችሁን ይከፍላችኋል።
እኔ የዘላለም ሕይወት እሰጣቸዋለሁ፤ ከቶ አይጠፉም፤ ከእጄም ሊነጥቃቸው የሚችል ማንም የለም። እነርሱን የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፤ ከአባቴም እጅ ማንም ሊነጥቃቸው አይችልም። በር ጠባቂው በሩን ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰማሉ። የራሱንም በጎች በየስማቸው እየጠራ ያወጣቸዋል። እኔና አብ አንድ ነን።”
ልጆች እንደ መሆናችሁ እንዲህ በማለት የተናገራችሁን ማበረታቻ ቃልም ረስታችኋል፦ “ልጄ ሆይ፤ የጌታን ተግሣጽ አታቃልል፤ በሚቀጣህም ጊዜ ተስፋ አትቍረጥ፤ ምክንያቱም ጌታ የሚወድደውን ይገሥጻል፤ እንደ ልጅ የሚቀበለውንም ይቀጣል።”
“ከእናንተ መካከል አባት ሆኖ ሳለ ልጁ ዓሣ ቢለምነው እባብ የሚሰጠው ይኖራልን? ወይስ ዕንቍላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋልን? እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳለ፣ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታን መስጠት ካወቃችሁበት፣ በሰማይ ያለው አባት ታዲያ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጥ?”
አንተ ውስጣዊ ሰውነቴን ፈጥረሃልና፤ በእናቴም ማሕፀን ውስጥ አበጃጅተህ ሠራኸኝ። ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፤ ነፍሴም ይህን በውል ተረድታለች።
እንግዲህ ከክርስቶስ ጋራ ከተነሣችሁ፣ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ በተቀመጠበት በላይ ያሉ ነገሮችን ፈልጉ፤ የፈጣሪውን መልክ እንዲመስል በዕውቀት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችኋል፤ በዚያ ግሪክ ወይም ይሁዲ፣ የተገረዘ ወይም ያልተገረዘ፣ አረማዊ ወይም እስኩቴስ፣ ባሪያ ወይም ጌታ ብሎ ልዩነት የለም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉም ነው፤ በሁሉም ነው። እንግዲህ የተቀደሳችሁና የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ምርጦች እንደ መሆናችሁ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ ጨዋነትንና ትዕግሥትን ልበሱ፤ እርስ በርሳችሁም ተቻቻሉ፤ ከእናንተ አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሠኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ፤ ጌታ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም ሌላውን ይቅር በሉ። በእነዚህ ሁሉ ላይ ሁሉን በፍጹም አንድነት የሚያስተሳስረውን ፍቅርን ልበሱት። እንደ አንድ አካል ሆናችሁ የተጠራችሁበት የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይንገሥ፤ የምታመሰግኑም ሁኑ። የክርስቶስ ቃል በሙላት ይኑርባችሁ፤ እርስ በርሳችሁ በጥበብ ሁሉ ተማማሩ፤ ተመካከሩ፤ በመዝሙርና በማሕሌት፣ በመንፈሳዊም ቅኔ በማመስገን በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ። በርሱ በኩል ለእግዚአብሔር አብ ምስጋና እያቀረባችሁ፣ በቃልም ሆነ በተግባር የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት። ሚስቶች ሆይ፤ በጌታ ዘንድ ተገቢ በመሆኑ ለባሎቻችሁ ተገዙ። ባሎች ሆይ፤ ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ መራራም አትሁኑባቸው። ሐሳባችሁም በላይ ባለው ላይ እንጂ በምድራዊ ነገር ላይ አይሁን።
ስለዚህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር እናውቃለን፤ በፍቅሩም እናምናለን። እግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ በፍቅር የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል፤ እግዚአብሔርም በርሱ ይኖራል።
ኖኅ ገና ስለማይታየው ነገር እግዚአብሔር ባስጠነቀቀው ጊዜ፣ እግዚአብሔርን ፈርቶ ቤተ ሰዎቹን ለማዳን መርከብን በእምነት ሠራ፤ በእምነቱ ዓለምን ኰነነ፤ በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ።
እርሱም በሙሴ ፊት እንዲህ እያለ እያወጀ ዐለፈ፤ “እግዚአብሔር ርኅሩኅና ቸር አምላክ፣ እግዚአብሔር ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩና ታማኝነቱ የበዛ፣ ፍቅርን ለሺሕዎች የሚጠብቅ፣ ክፋትን፣ ዐመፅንና ኀጢአትን ይቅር የሚል፣ በደለኛውን ግን ሳይቀጣ ዝም ብሎ አይተውም፤ በአባቶች ኀጢአት ልጆችን የልጅ ልጆቻቸውን እስከ ሦስትና አራት ትውልድ ይቀጣል።”
እንደዚህም በማድረጋችሁ በሰማይ ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆናላችሁ። እርሱ ፀሓዩን ለክፉዎችና ለመልካሞች ያወጣል፤ ዝናቡንም ለኀጢአተኞችና ለጻድቃን ያዘንባል።