ሥላሴ አንድ አምላክ በሦስት ዘላለማዊና እኩል አካላት መሆኑን ልብ በል። ምንም እንኳን በሥራቸው የተለያዩ ቢሆኑም፣ በመንፈስ ግን አንድ ናቸው።
ይህንን እውነት በብሉይ ኪዳን እንደምናየው "ምድርም ባዶ ነበረች፥ አንዳችም አልነበረባትም፤ ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረች፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውሃ ላይ ይወጣጠር ነበር" (ዘፍጥረት 1:1) ተብሎ ተጽፏል። እግዚአብሔር አንድ እንደሆነ ግን ደግሞ በሦስትነት እንደሚገለጥ እናያለን።
በአዲስ ኪዳንም "በዚያን ቀን እኔ በአባቴ እናንተም በእኔ፥ እኔም በእናንተ እንዳለሁ ታውቃላችሁ" የሚለው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ይህንኑ ያረጋግጥልናል። (ዮሐንስ 14:20)
እንዲያውም ብሉይ ኪዳን ስለ አምላክ ሦስትነት ፍንጭ ይሰጠናል። በዘፍጥረት 1:26 "እግዚአብሔርም፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ በባሕር ዓሣዎችም በሰማይም ወፎችም በእንስሶችም በምድርም ሁሉ ላይ በምድር ላይም በሚንቀሳቀሱ ሁሉ ላይ ይግዙ አለ።" እዚህ ላይ "እንፍጠር"፣ "በመልካችን"፣ "እንደ ምሳሌአችን" የሚሉት ቃላት ስለ አምላክ ሦስትነት ያመለክታሉ። ስለዚህ ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ ኢየሱስና መንፈስ ቅዱስ በአብ ዘንድ ነበሩ፤ ሦስቱም አንድ ናቸው።
እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ ካወቃቸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመታዘዝ በደሙ ለተረጩትና በመንፈስ አማካይነት ለተቀደሱት፤ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።
መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፤ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑልም ኀይል ይጸልልሻል፤ ስለዚህ የሚወለደው ቅዱሱ ሕፃን፣ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል።
እኔ አብን እለምናለሁ፤ እርሱም ከእናንተ ጋራ ለዘላለም የሚኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ እርሱም የእውነት መንፈስ ነው፤ ዓለም ስለማያየውና ስለማያውቀው ሊቀበለው አይችልም። እናንተ ግን፣ ዐብሯችሁ ስለሚኖርና በውስጣችሁ ስለሚሆን ታውቁታላችሁ።
በተጠራችሁ ጊዜ ወደ አንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ ሁሉ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ አንድ ጌታ፣ አንድ እምነትና አንድ ጥምቀት አለ፤ ከሁሉም በላይ የሆነ፣ በሁሉም የሚሠራ፣ በሁሉ የሚኖር የሁሉም አባት የሆነ አንድ አምላክ አለ።
ኢየሱስም እንደ ተጠመቀ ከውሃው ወጣ፤ ወዲያውኑም ሰማይ ተከፍቶ የእግዚአብሔር መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድበት አየ። እነሆ፤ “በርሱ ደስ የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይህ ነው” የሚል ድምፅ ከሰማይ ተሰማ።
ለእኛ ግን ሁሉም ነገር ከርሱ የሆነ፣ እኛም ለርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን፤ ደግሞም ሁሉም ነገር በርሱ አማካይነት የሆነ፣ እኛም በርሱ አማካይነት የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን።
የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል። እርሱ ከራሱ አይናገርም፤ የሚሰማውን ብቻ ይናገራል፤ እንዲሁም ወደ ፊት ስለሚሆነው ይነግራችኋል፤ የእኔ ከሆነው ወስዶ እንድታውቁ በማድረግ ያከብረኛል። የአብ የሆነው ሁሉ የእኔ ነው፤ እንግዲህ፣ ‘የእኔ ከሆነው ወስዶ እንድታውቁ ያደርጋል’ ያልኋችሁ ለዚሁ ነው።
እግዚአብሔር፣ “ሰውን በመልካችን፣ በአምሳላችን እንሥራ፤ በባሕር ዓሦች፣ በሰማይ ወፎች፣ በከብቶች፣ በምድር ሁሉ ላይ፣ እንዲሁም በምድር ላይ በሚሳቡ ፍጥረታት ሁሉ ላይ ሥልጣን ይኑራቸው” አለ።
“ወደ እኔ ቅረቡ፤ ይህን ስሙ፤ “ከመጀመሪያ ጀምሮ በስውር አልተናገርሁም፤ ሲፈጸምም እኔ እዚያው ነበርሁ።” አሁንም ጌታ እግዚአብሔርና መንፈሱ ልከውኛል።
የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድኾች ወንጌልን እንድሰብክ፣ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና። ልባቸው የተሰበረውን እንድጠግን፣ ለምርኮኞች ነጻነትን፣ ለእስረኞች መፈታትን እንዳውጅ ልኮኛል።
እርሱ እየተናገረ ሳለ፣ ብሩህ ደመና ሸፈናቸው፤ ከደመናውም ውስጥ፣ “በርሱ ደስ የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ድምፅ ተሰማ።
ከውሃው በሚወጣበትም ጊዜ፣ ሰማያት ተከፍተው፣ መንፈስ ቅዱስ እንደ ርግብ በርሱ ላይ ሲወርድ አየ፤ “የምወድድህ ልጄ አንተ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል” የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ።
ሕዝቡ ሁሉ ከተጠመቀ በኋላ ኢየሱስም ተጠመቀ፤ እየጸለየም ሳለ ሰማይ ተከፈተ፤ መንፈስ ቅዱስም በአካላዊ ቅርጽ እንደ ርግብ በርሱ ላይ ወረደ፤ ከሰማይም፣ “የምወድድህ ልጄ አንተ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል” የሚል ድምፅ መጣ።
እግዚአብሔር መንፈሱን ሳይሰፍር ስለሚሰጥ፣ እግዚአብሔር የላከው የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራል። አብ ወልድን ይወድዳል፤ ሁሉንም ነገር በእጁ ሰጥቶታል።
እንግዲህ አይሁድ፣ ኢየሱስ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ ሳይሆን፣ እግዚአብሔርን አባቱ በማድረግ፣ ራሱን ከእግዚአብሔር እኩል በማድረጉ፣ ሊገድሉት አጥብቀው ይፈልጉት ነበር።
ይህም፣ አባት ሆይ፤ አንተ በእኔ፣ እኔም በአንተ እንዳለሁ ሁሉም አንድ እንዲሆኑ፣ እንዲሁም አንተ እኔን እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ፣ እነርሱም በእኛ እንዲሆኑ ነው። እኛ አንድ እንደ ሆንን እነርሱም አንድ እንዲሆኑ፣ የሰጠኸኝን ክብር ሰጥቻቸዋለሁ።
ከእነርሱም ጋራ በማእድ ተቀምጦ ሳለ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “ከኢየሩሳሌም አትውጡ፤ ነገር ግን እኔ ስናገር የሰማችሁትን፣ አብ የሰጠውን ተስፋ ጠብቁ፤ ዮሐንስ በውሃ አጥምቆ ነበርና፣ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ።”
ይህን ኢየሱስ፣ እግዚአብሔር ከሞት አስነሣው፤ እኛም ሁላችን ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን። ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ካለ በኋላ፣ የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ ከአብ ተቀብሎ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው።
ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለ፤ “ሐናንያ ሆይ፤ መንፈስ ቅዱስን ትዋሽና ከመሬቱ ሽያጭ ታስቀር ዘንድ ሰይጣን ልብህን ለምን ሞላው? እናንተ በዕንጨት ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን፣ የአባቶቻችን አምላክ ከሙታን አስነሣው፤ እርሱም ለእስራኤል ንስሓንና የኀጢአትን ስርየት ይሰጥ ዘንድ፣ እግዚአብሔር የሁሉ ራስና አዳኝ አድርጎ በቀኙ ከፍ ከፍ አደረገው። እኛም ለእነዚህ ነገሮች ምስክር ነን፤ ደግሞም እግዚአብሔር ለሚታዘዙት የሰጠው መንፈስ ቅዱስ ምስክር ነው።” ሰዎቹም ይህን በሰሙ ጊዜ ክፉኛ ተቈጡ፤ ሊገድሏቸውም ፈለጉ። ነገር ግን በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ የተከበረ አንድ የሕግ መምህር፣ እርሱም ገማልያል የሚሉት ፈሪሳዊ ተነሥቶ በሸንጎው መካከል ቆመና ሐዋርያትን ወደ ውጭ አውጥተው ለጥቂት ጊዜ እንዲያዩአቸው አዘዘ፤ ለሸንጎውም እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፤ በእነዚህ ሰዎች ላይ ልታደርጉ ስላሰባችሁት ነገር በጥንቃቄ ልታጤኑ ይገባችኋል። ከዚህ ቀደም፣ ቴዎዳስ ራሱን ትልቅ አድርጎ በመቍጠር ተነሥቶ፣ አራት መቶ ያህል ሰዎች ተባበሩት፤ ነገር ግን እርሱም ተገደለ፤ ተከታዮቹም ሁሉ ተበታተኑ፤ ነገሩም እንዳልነበር ሆነ። ከርሱም በኋላ፣ በሕዝብ ቈጠራው ወቅት ገሊላዊው ይሁዳ ተነሥቶ ብዙ ሕዝብ አሸፈተ፤ ተከታይም አግኝቶ ነበር፤ እርሱም ጠፋ፤ ተከታዮቹም ተበተኑ። ስለዚህ አሁንም የምላችሁ፦ እነዚህን ሰዎች ተዉአቸው! አትንኳቸው! ሐሳባቸው ወይም አድራጎታቸው ከሰው ከሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር ከሆነ ግን ልትገቷቸው አትችሉም፤ እንዲያውም ከእግዚአብሔር ጋራ ስትጣሉ ትገኙ ይሆናል።” ሳትሸጠው በፊት የአንተው አልነበረምን? ከሸጥኸውስ በኋላ ቢሆን ገንዘቡ በእጅህ አልነበረምን? ለመሆኑ ይህን ነገር እንዴት በልብህ አሰብህ? የዋሸኸው እኮ እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አይደለም።”
እስጢፋኖስ ግን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኵር ብሎ ሲመለከት፣ የእግዚአብሔርን ክብር እንዲሁም ኢየሱስ በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና፣ “እነሆ፤ ሰማያት ተከፍተው፣ የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ” አለ።
በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና። እንደ ገና የፍርሀት ባሪያ የሚያደርጋችሁን መንፈስ ሳይሆን፣ “አባ፣ አባት” ብለን የምንጠራበትን የልጅነት መንፈስ ተቀብላችኋልና፤ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋራ ሆኖ ይመሰክርልናል። ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ የክብሩ ተካፋዮች እንሆን ዘንድ በርግጥ የመከራው ተካፋዮች ብንሆን፣ የእግዚአብሔር ወራሾች፣ ከክርስቶስ ጋራ ዐብረን ወራሾች ነን።
በእግዚአብሔር ወንጌል የክህነት ተግባር፣ ለአሕዛብ የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ ለመሆን ነው፤ ይኸውም አሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ ተቀድሰው በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት እንዲሆኑ ነው።
እግዚአብሔር ግን ይህን በመንፈሱ አማካይነት ለእኛ ገልጦልናል። መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር እንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራል። በውስጡ ካለው ከራሱ መንፈስ በቀር ከሰው መካከል የአንድን ሰው ሐሳብ የሚያውቅ ማን አለ? እንደዚሁም ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር፣ የእግዚአብሔርን ሐሳብ የሚያውቅ ማንም የለም።
ከእናንተ አንዳንዶቻችሁ እንደዚህ ነበራችሁ፤ አሁን ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስምና በአምላካችን መንፈስ ታጥባችኋል፤ ተቀድሳችኋል፤ ጸድቃችኋል።
ስጦታዎች ልዩ ልዩ ሲሆኑ፣ መንፈስ ግን አንድ ነው፤ አገልግሎትም ልዩ ልዩ ሲሆን፣ ጌታ ግን አንድ ነው፤ አሠራርም ልዩ ልዩ ሲሆን፣ ሁሉን በሁሉ የሚሠራው ግን ያው አንዱ እግዚአብሔር ነው።
እንግዲህ፣ እኛንም እናንተንም በክርስቶስ ጸንተን እንድንቆም የሚያደርገን እግዚአብሔር ነው፤ የቀባንም እርሱ ነው፤ የርሱ ለመሆናችን ማኅተሙን ያተመብን ደግሞም ወደ ፊት ለምናገኘው ነገር የመንፈሱን ዋስትና በልባችን ያኖረ እርሱ ነው።
ነገር ግን የተወሰነው ዘመን በደረሰ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን፣ ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤ ይህም የሆነው የልጅነትን መብት እናገኝ ዘንድ ከሕግ በታች ያሉትን ለመዋጀት ነው። ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር፣ “አባ፣ አባት” ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ ወደ ልባችን ላከ።
በዚህም ምክንያት በአብ ፊት እንበረከካለሁ፤ ከርሱም በሰማይና በምድር ያለ ቤተ ሰብ ሁሉ ስያሜ ያገኛል። በውስጥ ሰውነታችሁ እንድትጠነክሩ፣ ከክብሩ ባለጠግነት በመንፈሱ በኩል ኀይል እንዲሰጣችሁ እጸልያለሁ፤ ይኸውም በእምነት ክርስቶስ በልባችሁ እንዲያድር ነው። ደግሞም ሥር ሰድዳችሁ፣ በፍቅር ታንጻችሁ፣
በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ያ አስተሳሰብ፣ በእናንተም ዘንድ ይሁን፤ እርሱ በባሕርዩ አምላክ ሆኖ ሳለ፣ ከእግዚአብሔር ጋራ መተካከልን ሊለቅቀው እንደማይገባ አድርጎ አልቈጠረውም፤
እርሱ የማይታየው አምላክ አምሳል ነው፤ ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ ሁሉ ነገር በርሱ ተፈጥሯል፤ በሰማይና በምድር ያሉ፣ የሚታዩና የማይታዩ፣ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ኀይላት፣ ገዦች ቢሆኑ ወይም ባለሥልጣናት፣ ሁሉም ነገር በርሱና ለርሱ ተፈጥሯል። እርሱ ከሁሉ በፊት ነው፤ ሁሉም ነገር በአንድ ላይ ተያይዞ የጸናው በርሱ ነው።
በጌታ የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ፤ እኛ ግን ስለ እናንተ እግዚአብሔርን ሁልጊዜ ልናመሰግን ይገባናል። ምክንያቱም እግዚአብሔር እናንተን ከመጀመሪያ አንሥቶ በመንፈስ ተቀድሳችሁና በእውነትም አምናችሁ እንድትድኑ መርጧችኋል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ተካፋዮች እንድትሆኑም በወንጌላችን አማካይነት ጠርቷችኋል።
የእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት ምስጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ እርሱ በሥጋ ተገለጠ፤ በመንፈስ ጸደቀ፤ በመላእክት ታየ፤ በአሕዛብ ዘንድ ተሰበከ፤ በዓለም ባሉት ታመነ፤ በክብር ዐረገ።
ነገር ግን የአዳኛችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ፍቅር በተገለጠ ጊዜ፣ ስላደረግነው የጽድቅ ሥራ ሳይሆን፣ ከምሕረቱ የተነሣ አዳነን። ያዳነንም ዳግም ልደት በሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ መታደስ ነው፤ ይህንም መንፈስ እግዚአብሔር በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእኛ ላይ አትረፍርፎ አፈሰሰው፤
እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በተለያየ ጊዜና በልዩ ልዩ መንገድ በነቢያት በኩል ለአባቶቻችን ተናግሮ፣ ደግሞም እንዲህ ይላል፤ “ጌታ ሆይ፤ አንተ በመጀመሪያ የምድርን መሠረት አኖርህ፤ ሰማያትም የእጆችህ ሥራ ናቸው። እነርሱ ይጠፋሉ፤ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፤ እንደ መጐናጸፊያ ትጠቀልላቸዋለህ፤ እንደ ልብስም ይለወጣሉ። አንተ ግን ያው አንተ ነህ፤ ዘመንህም ፍጻሜ የለውም።” እግዚአብሔር፣ “ጠላቶችህን ለእግርህ መረገጫ እስከማደርግልህ ድረስ፣ በቀኜ ተቀመጥ” ያለው ከመላእክት ከቶ ለማን ነው? መላእክት ሁሉ መዳንን የሚወርሱትን ለማገልገል የሚላኩ አገልጋይ መናፍስት አይደሉምን? በዚህ መጨረሻ ዘመን ግን ሁሉን ወራሽ ባደረገውና ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ ለእኛ ተናገረን። እርሱ የእግዚአብሔር ክብር ነጸብራቅና የባሕርዩ ትክክለኛ ምሳሌ ሆኖ፣ በኀያል ቃሉ ሁሉን ደግፎ ይዟል። የኀጢአት መንጻት ካስገኘ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ።
በዘላለም መንፈስ አማካይነት ራሱን ነውር አልባ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቀረበው የክርስቶስ ደም፣ ሕያው እግዚአብሔርን እንድናመልክ ኅሊናችንን ከምውት ሥራ እንዴት ይበልጥ ያነጻ ይሆን!
እንዲሁም ክርስቶስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለ ኀጢአት ሞቷልና፤ ወደ እግዚአብሔር ያቀርባችሁ ዘንድ ጻድቅ የሆነው እርሱ ስለ ዐመፀኞች ሞተ፤ እርሱ በሥጋ ሞተ፤ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፤
መንፈሱን ስለ ሰጠን፣ እኛ በርሱ እንደምንኖር እርሱም በእኛ እንደሚኖር እናውቃለን። አብ ልጁን የዓለም አዳኝ ይሆን ዘንድ እንደ ላከው አይተናል፤ እንመሰክራለንም።
ከዮሐንስ፤ በእስያ አውራጃ ለሚገኙ ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት፤ ካለው፣ ከነበረውና ከሚመጣው፣ በዙፋኑም ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት፣ እንዲሁም ታማኝ ምስክር፣ ከሙታን በኵርና የምድር ነገሥታት ገዥ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስም ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። ለወደደንና ከኀጢአታችንም በደሙ ነጻ ላወጣን፣
አራቱም ሕያዋን ፍጡራን እያንዳንዳቸው ስድስት ስድስት ክንፎች ነበሯቸው፤ በዙሪያቸውና በውስጣቸው በዐይኖች የተሞሉ ነበሩ፤ ቀንና ሌሊትም፦ “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ የነበረው፣ ያለውና የሚመጣው፤ ሁሉን ቻይ ጌታ አምላክ” ማለትን አያቋርጡም።
አብ በማንም ላይ አይፈርድም፤ ነገር ግን ፍርድን ሁሉ ለወልድ አሳልፎ ሰጥቶታል፤ ይኸውም፣ ሁሉ አብን እንደሚያከብሩ ወልድን ያከብሩት ዘንድ ነው፤ ወልድን የማያከብር፣ የላከውን አብንም አያከብርም።
እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስና በኀይል ቀባው፤ እርሱም እግዚአብሔር ከርሱ ጋራ ስለ ነበረ በደረሰበት ሁሉ መልካም እያደረገ በዲያብሎስ ሥልጣን ሥር የነበሩትን ሁሉ ፈወሰ።
ለራሳችሁና መንፈስ ቅዱስ ኤጲስ ቆጶሳት አድርጎ በላዩ ለሾማችሁ መንጋ ሁሉ ተጠንቀቁ፤ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ጠብቁ።
ከእንግዲህ እኔ አልኖርም፤ ነገር ግን ክርስቶስ በውስጤ ይኖራል። አሁንም በሥጋ የምኖረው ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው።
የክብር አባት የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክ ይበልጥ እንድታውቁት፣ የጥበብና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ ያለ ማቋረጥ እለምናለሁ።
ከእምነት የሆነውን ሥራችሁን፣ ከፍቅር የመነጨውን ድካማችሁንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ባላችሁ ተስፋ የተገኘውን ጽናታችሁን በአምላካችንና በአባታችን ፊት ዘወትር እናስባለን። በእግዚአብሔር የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ፣ እርሱ እንደ መረጣችሁ እናውቃለን፤ ምክንያቱም ወንጌላችን ወደ እናንተ የመጣው በኀይልና በመንፈስ ቅዱስ፣ በብዙም መረዳት እንጂ በቃል ብቻ አይደለም። ደግሞ ስለ እናንተ ስንል በመካከላችሁ እንዴት እንደ ኖርን ታውቃላችሁ።
የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያና ሐዋርያ ስምዖን ጴጥሮስ፤ በአምላካችንና በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ በኩል እንደ ተቀበልነው ዐይነት ክቡር እምነት ለተቀበሉት፤ ስለዚህ ወንድሞች ሆይ፤ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ለማጽናት ከፊት ይልቅ ትጉ፤ ምክንያቱም እነዚህን ብታደርጉ ከቶ አትሰናከሉም። በዚህም ወደ ጌታችንና አዳኛችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊ መንግሥት መግባት በሙላት ይሰጣችኋል። ስለዚህ ምንም እንኳ እነዚህን ነገሮች ብታውቋቸውና በያዛችሁት እውነት ብትጸኑም፣ ስለ እነዚህ ነገሮች እናንተን ዘወትር ከማሳሰብ ቸል አልልም። በዚህ ምድራዊ ድንኳን ውስጥ እስካለሁ ድረስ እናንተን መጐትጐት ትክክል ሆኖ ይታየኛል፤ ምክንያቱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ገለጠልኝ ይህን ምድራዊ ድንኳን ቶሎ ጥዬ እንደምሄድ ዐውቃለሁ፤ እነዚህን ነገሮች ከተለየኋችሁም በኋላ ዘወትር ታስቡ ዘንድ እተጋለሁ። ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኀይልና ስለ መምጣቱ የነገርናችሁ የርሱን ግርማ በዐይናችን አይተን እንጂ፣ በሰዎች ጥበብ የተፈጠረውን ተረት ተከትለን አይደለም፤ ምክንያቱም ከግርማዊው ክብር “በርሱ ደስ የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይህ ነው” የሚል ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርና ሞገስ ተቀብሏል፤ እኛም ከርሱ ጋራ በቅዱሱ ተራራ ላይ በነበርንበት ጊዜ ይህ ድምፅ ከሰማይ ሲመጣ ሰምተናል። እንግዲያስ ትንቢታዊው ቃል ይበልጥ ተረጋግጦልናል፤ ሌሊቱ እስኪነጋና የንጋት ኮከብ በልባችሁ እስኪበራ ድረስ፣ በጨለማ ስፍራ ለሚበራ መብራት ጥንቃቄ እንደሚደረግ እናንተም ለዚህ ቃል ብትጠነቀቁ መልካም ታደርጋላችሁ። እግዚአብሔርንና ጌታችን ኢየሱስን በማወቅ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።
“በሎዶቅያ ላለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤ አሜን የሆነው፣ ደግሞም ታማኝና እውነተኛ ምስክር የሆነው፣ የእግዚአብሔርም ፍጥረት ምንጭ የሆነው እንዲህ ይላል።
ከዚያም በሰማይና በምድር፣ ከምድር በታችና በባሕር፣ በእነርሱ ውስጥ ያሉ ፍጥረታትም ሁሉ እንዲህ ብለው ሲዘምሩ ሰማሁ፤ “በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠውና ለበጉ፣ ምስጋናና ሞገስ፣ ክብርና ኀይል፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን።”
ከዚያም እግዚአብሔር አምላክ፣ “ሰው መልካምንና ክፉውን ለይቶ በማወቅ ረገድ አሁን ከእኛ እንደ አንዱ ሆኗል፤ አሁን ደግሞ እጁን ዘርግቶ ከሕይወት ዛፍ ቀጥፎ እንዳይበላ፣ ለዘላለምም እንዳይኖር ይከልከል” አለ።
ሕፃን ተወልዶልናል፤ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል። ስሙም፣ ድንቅ መካር፣ ኀያል አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም ልዑል ይባላል።
“የእስራኤል ንጉሥና ቤዛ እግዚአብሔር፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የፊተኛውም እኔ ነኝ፤ የኋለኛውም እኔ ነኝ፤ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም።
አባቶችም የእነርሱ ናቸው፤ ክርስቶስም በሥጋ የትውልድ ሐረጉ የሚቈጠረው ከእነርሱ ነው፤ እርሱም፣ ከሁሉ በላይ የሆነ ለዘላለም የተመሰገነ አምላክ ነው! አሜን።
ባየሁት ጊዜ እንደ ሞተ ሰው ሆኜ በእግሩ ሥር ወደቅሁ። እርሱም ቀኝ እጁን በላዬ ጭኖ እንዲህ አለኝ፤ “አትፍራ፤ የመጀመሪያውም የመጨረሻውም እኔ ነኝ፤ እኔ ሕያው ነኝ፤ ሞቼ ነበር፤ እነሆ፤ አሁን ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፤ የሞትና የሲኦል መክፈቻም በእጄ ነው።