ወንድሞቼ ሆይ፤ ልዩ ልዩ መከራ ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት፤ የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አያመጣምና። ስለዚህ ርኩሰትንና ተንሰራፍቶ የሚገኘውን ክፋትን አስወግዳችሁ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን፣ በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በትሕትና ተቀበሉ። ቃሉ የሚናገረውን አድርጉ እንጂ ሰሚዎች ብቻ ሆናችሁ ራሳችሁን አታታልሉ። ቃሉን የሚሰማ፣ ነገር ግን የሚለውን የማይፈጽም ሰው ፊቱን በመስተዋት እንደሚያይ ሰው ነው፤ ራሱንም አይቶ ይሄዳል፤ ወዲያውም ምን እንደሚመስል ይረሳል፤ ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹም ሕግ ተመልክቶ የሚጸና፣ የሰማውን የሚያደርግና የማይረሳ ሰው በሥራው ብሩክ ይሆናል። አንደበቱን ሳይገታ፣ ልቡን እያሳተ ሃይማኖተኛ ነኝ የሚል ሰው፣ ራሱን ያታልላል፤ ሃይማኖቱም ከንቱ ነው። በእግዚአብሔር አብ ፊት ንጹሕና ነውር የሌለበት ሃይማኖት ይህ ነው፤ ወላጆቻቸው የሞቱባቸውን ልጆችና ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች በችግራቸው መርዳትና ከዓለም ርኩሰት ራስን መጠበቅ ነው። ምክንያቱም የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንደሚያስገኝ ታውቃላችሁ። ምንም የማይጐድላችሁ ፍጹማንና ምሉኣን እንድትሆኑ ትዕግሥት ሥራውን ይፈጽም።
አሁን በብዙ ዐይነት ፈተና ውስጥ ሆናችሁ ለጥቂት ጊዜ መከራን ብትቀበሉም እንኳ በዚህ እጅግ ደስ ይላችኋል። እነዚህ ነገሮች በእናንተ ላይ የደረሱት፣ በእሳት ተፈትኖ ቢጠራም፣ ጠፊ ከሆነው ወርቅ ይልቅ እጅግ የከበረው እምነታችሁ፣ እውነተኛ መሆኑ እንዲረጋገጥና ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ምስጋናን፣ ክብርንና ውዳሴን እንዲያስገኝላችሁ ነው።
ምክንያቱም ቀላልና ጊዜያዊ የሆነው መከራችን ወደር የማይገኝለት ዘላለማዊ ክብር ያስገኝልናል። ስለዚህ ዐይናችን የሚያተኵረው በሚታየው ነገር ላይ ሳይሆን በማይታየው ላይ ነው፤ የሚታየው ጊዜያዊ ነውና፤ የማይታየው ግን ዘላለማዊ ነው።
በዚህ ብቻ ሳይሆን በመከራችንም ሐሤት እናደርጋለን፤ ምክንያቱም መከራ ትዕግሥትን እንደሚያስገኝ እናውቃለን። ትዕግሥት ጽናትን፣ ጽናት የተፈተነ ባሕርይን፣ የተፈተነ ባሕርይ ተስፋን፤ ይህም ተስፋ ለዕፍረት አይዳርገንም፤ እግዚአብሔር በሰጠን በመንፈስ ቅዱስ ፍቅሩን በልባችን አፍስሷልና።
በሰዎች ሁሉ ላይ ከደረሰው የተለየ ፈተና አልደረሰባችሁም፤ እግዚአብሔር ታማኝ ነው፤ ስለዚህ ከምትችሉት በላይ እንድትፈተኑ አይተዋችሁም፤ ነገር ግን በምትፈተኑበት ጊዜ ፈተናውን መታገሥ እንድትችሉ፣ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል።
አምላክ ሆይ፤ አንተ ፈተንኸን፤ እንደ ብርም አነጠርኸን። ወደ ወጥመድ አገባኸን፤ በጀርባችንም ሸክም ጫንህብን። ሰዎች በራሳችን ላይ እንዲፈነጩ አደረግህ፤ በእሳትና በውሃ መካከል ዐለፍን፤ የኋላ ኋላ ግን ወደ በረከት አመጣኸን።
ወዳጆች ሆይ፤ እንደ እሳት የሚፈትን ብርቱ መከራ በመቀበላችሁ እንግዳ ነገር እንደ ደረሰባችሁ በመቍጠር አትደነቁ፤ ነገር ግን ክብሩ በሚገለጥበት ጊዜ ደስታችሁ ታላቅ እንዲሆን የክርስቶስ መከራ ተካፋዮች በመሆናችሁ ደስ ይበላችሁ።
“ሐሳቤ እንደ ሐሳባችሁ፣ መንገዴ እንደ መንገዳችሁ አይደለምና” ይላል እግዚአብሔር። “ሰማያት ከምድር ከፍ እንደሚሉ፣ መንገዴ ከመንገዳችሁ፣ ሐሳቤም ከሐሳባችሁ እንዲሁ ከፍ ያለ ነው።
ለእናንተ ያለኝን ዕቅድ እኔ ዐውቃለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ዕቅዱም ፍጻሜው ያማረና ተስፋ የሚሰጣችሁ፣ የሰላም ሐሳብ እንጂ ለክፉ አይደለም።
በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ፣ ለጥቂት ጊዜ መከራ ከተቀበላችሁ በኋላ እርሱ ራሱ መልሶ ያበረታችኋል፤ አጽንቶም ያቆማችኋል።
ራሳችሁን ከፍቅረ ንዋይ ጠብቁ፤ ባላችሁ ነገር ረክታችሁ ኑሩ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር፣ “ከቶ አልተውህም፤ በፍጹም አልጥልህም” ብሏል። ስለዚህ በሙሉ ልብ፣ “ጌታ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም፤ ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” እንላለን።
ምክንያቱም ጌታ የሚወድደውን ይገሥጻል፤ እንደ ልጅ የሚቀበለውንም ይቀጣል።” እግዚአብሔር እንደ ልጆቹ ይዟችኋልና የተግሣጽን ምክር ታገሡ፤ ለመሆኑ አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው?
እንግዲህ በእኛ ውስጥ እንደሚሠራው እንደ ኀይሉ መጠን፣ ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ እጅግ አብልጦ ማድረግ ለሚቻለው፣ በቤተ ክርስቲያን እንዲሁም በክርስቶስ ኢየሱስ፣ በዘመናት ሁሉ ከዘላለም እስከ ዘላለም ለርሱ ክብር ይሁን! አሜን።
የርኅራኄ አባት፣ የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። እኛ ራሳችን ከእግዚአብሔር በተቀበልነው መጽናናት፣ በመከራ ያሉትን ማጽናናት እንድንችል፣ እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል።
በውሃ ውስጥ በምታልፍበት ጊዜ፣ ከአንተ ጋራ እሆናለሁ፤ ወንዙን ስትሻገረው፣ አያሰጥምህም፤ በእሳት ውስጥ ስትሄድ፣ አያቃጥልህም፤ ነበልባሉም አይፈጅህም።
“እናንተ ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ በልቤ የዋህና ትሑት ነኝና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ “ይመጣል ተብሎ የሚጠበቀው አንተ ነህ? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ሲል ጠየቀ። ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነውና።”
በአንተ ላይ ታምናለችና፣ በአንተ የምትደገፈውን ነፍስ ፈጽመህ በሰላም ትጠብቃታለህ። በእግዚአብሔር ለዘላለም ታመኑ፤ ጌታ እግዚአብሔር የዘላለም ዐለት ነውና።
እግዚአብሔርን ደጅ ጠናሁት፤ እርሱም ዘንበል አለልኝ፤ ጩኸቴንም ሰማ። ጽድቅህን በልቤ አልሸሸግሁም፤ ታማኝነትህንና ማዳንህን እናገራለሁ፤ ምሕረትህንና እውነትህን፣ ከታላቅ ጉባኤ አልደበቅሁም። እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህን አትንፈገኝ፤ ቸርነትህና እውነትህ ዘወትር ይጠብቁኝ፤ ስፍር ቍጥር የሌለው ክፋት ከብቦኛልና፤ የኀጢአቴ ብዛት ስለ ያዘኝ ማየት ተስኖኛል፤ ከራሴ ጠጕር ይልቅ በዝቷል፤ ልቤም ከድቶኛል። እግዚአብሔር ሆይ፤ ታድነኝ ዘንድ ፈቃድህ ይሁን፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔን ለመርዳት ፍጠን። ነፍሴን ለመንጠቅ የሚፈልጉ ይፈሩ፤ ይዋረዱም፤ ጕዳቴንም የሚሹ፣ ተዋርደው በመጡበት ይመለሱ። በእኔ ላይ፣ “ዕሠይ! ዕሠይ!” የሚሉ፣ በራሳቸው ዕፍረት ይደንግጡ። አንተን የሚፈልጉ ሁሉ ግን፣ ሐሤት ያድርጉ፤ በአንተም ደስ ይበላቸው፤ ዘወትር የአንተን ማዳን የሚወድዱ፣ “እግዚአብሔር ከፍ ከፍ ይበል!” ይበሉ። እኔ ግን ችግረኛና ድኻ ነኝ፤ ጌታ ግን ያስብልኛል። አንተ ረዳቴና ታዳጊዬም ነህና፤ አምላኬ ሆይ፤ አትዘግይ። ከሚውጥ ጕድጓድ፣ ከሚያዘቅጥ ማጥ አወጣኝ፤ እግሮቼን በዐለት ላይ አቆመ፤ አካሄዴንም አጸና። ለአምላካችን የሚሆን ውዳሴ፣ አዲስ ዝማሬን በአፌ ላይ አኖረ፤ ብዙዎች ያያሉ፤ ይፈራሉም፤ በእግዚአብሔር ይታመናሉ።
ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፤ ጸንታችሁ ቁሙ፤ በምንም ነገር አትናወጡ። ለጌታ ሥራ ዘወትር የምትተጉ ሁኑ፤ ምክንያቱም ለጌታ የምትደክሙት በከንቱ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ።
በትዕግሥት የጸኑትን የተባረኩ አድርገን እንደምንቈጥር ታውቃላችሁ፤ ኢዮብ እንዴት ታግሦ እንደ ጸና ሰምታችኋል፤ ጌታም በመጨረሻ ያደረገለትን አይታችኋል። ጌታ እጅግ ርኅሩኅና መሓሪ ነው።
ስለ ጽድቅ ብለው የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፤ መንግሥተ ሰማይ የእነርሱ ናትና። “ሰዎች በእኔ ምክንያት ቢሰድቧችሁ፣ ቢያሳድዷችሁና ክፉውን ሁሉ በሐሰት ቢያስወሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። በሰማይ የምትቀበሉት ዋጋ ታላቅ ስለ ሆነ ደስ ይበላችሁ፤ ሐሤት አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያት እንደዚሁ አሳድደዋቸዋልና።
በድካማችን የማይራራልን ሊቀ ካህናት የለንምና፤ ነገር ግን እንደ እኛ በማንኛውም ነገር የተፈተነ ሊቀ ካህናት አለን፤ ይሁን እንጂ ምንም ኀጢአት አልሠራም። እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበልና በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ፣ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።
መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በአእምሯችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።
በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ፣ ከምስጋናም ጋራ ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ እንጂ ስለ ማንኛውም ነገር አትጨነቁ። ከማስተዋል በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም፣ ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።
“ነገር ግን በእግዚአብሔር የሚታመን፣ መታመኛውም እግዚአብሔር የሆነ ሰው ቡሩክ ነው። በውሃ ዳር እንደ ተተከለ፣ ሥሩንም ወደ ወንዝ እንደ ሰደደ ዛፍ ነው፣ ሙቀት ሲመጣ አይፈራም፤ ቅጠሉም ዘወትር እንደ ለመለመ ነው፤ በድርቅ ዘመን አይሠጋም፤ ፍሬ ማፍራቱንም አያቋርጥም።”
ምክንያቱም ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋል። ዓለምን የሚያሸንፈውም እምነታችን ነው። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማነው?
አሁን የምናየው በመስተዋት ውስጥ እንደሚታይ በድንግዝግዝ ነው፤ በዚያ ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን። አሁን የማውቀው በከፊል ነው፤ በዚያ ጊዜ እኔ ራሴ ሙሉ በሙሉ የታወቅሁትን ያህል ዐውቃለሁ።
እግዚአብሔር ግን ምሕረት ሊያደርግላችሁ ይታገሣል፤ ርኅራኄም ሊያሳያችሁ ይነሣል። እግዚአብሔር የፍትሕ አምላክ ነውና፣ እርሱን በመተማመን የሚጠባበቁት ብፁዓን ናቸው!
የእግዚአብሔርን ቸርነት በሕያዋን ምድር እንደማይ ሙሉ እምነቴ ነው። እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ አይዞህ፣ በርታ፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ።
እንግዲህ በእምነት ስለ ጸደቅን፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከእግዚአብሔር ጋራ ሰላም አለን። የእግዚአብሔር ጠላቶች ሳለን በልጁ ሞት ከርሱ ጋራ ከታረቅን፣ ዕርቅን ካገኘን በኋላ፣ በሕይወቱማ መዳናችን እንዴት የላቀ አይሆንም! ይህ ብቻ አይደለም። ነገር ግን አሁን ዕርቅን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ ሐሤት እናደርጋለን። ስለዚህ ኀጢአት በአንድ ሰው በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ ሁሉ፣ ሞትም በኀጢአት በኩል ገብቷል፤ በዚሁ መንገድ ሞት ወደ ሰዎች ሁሉ መጣ፤ ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤ ሕግ ከመሰጠቱ በፊት ኀጢአት በዓለም ላይ ነበር፤ ነገር ግን ሕግ በሌለበት ኀጢአት አይቈጠርም። ይሁን እንጂ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ባሉት፣ እንደ አዳም ሕግን በመጣስ ኀጢአት ባልሠሩት ላይ እንኳ ሞት ነገሠ፤ አዳም ይመጣ ዘንድ ላለው አምሳሉ ነበረ። ነገር ግን ስጦታው እንደ በደሉ መጠን አይደለም፤ በአንድ ሰው መተላለፍ ብዙዎቹ ከሞቱ፣ የእግዚአብሔር ጸጋና በአንዱ ሰው፣ ይኸውም በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የመጣው ስጦታ ለብዙዎች እንዴት አብልጦ ይትረፈረፍ! ደግሞም የእግዚአብሔር ስጦታ እንደ አንዱ ሰው የኀጢአት ውጤት አይደለም፤ ምክንያቱም ፍርዱ የአንድን ሰው ኀጢአት ተከትሎ ኵነኔን አመጣ፤ ስጦታው ግን አያሌ መተላለፍን ተከትሎ ጽድቅን አመጣ። በአንድ ሰው መተላለፍ ምክንያት ሞት በዚህ ሰው በኩል የነገሠ ከሆነ፣ የእግዚአብሔርን የተትረፈረፈ ጸጋና የጽድቅ ስጦታ የተቀበሉት፣ በአንዱ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እንዴት አብልጠው በሕይወት አይነግሡ! ከእንግዲህ በአንድ ሰው መተላለፍ የተነሣ ኵነኔ በሁሉ ሰው ላይ እንደ መጣ፣ እንዲሁም በአንዱ የጽድቅ ሥራ ለሰው ሁሉ ሕይወትን የሚሰጥ ጽድቅ ተገኘ። በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኀጢአተኞች እንደ ሆኑ፣ በአንዱ ሰው መታዘዝ ደግሞ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ። በርሱም በኩል አሁን ወደ ቆምንበት ጸጋ በእምነት መግባት ችለናል፤ የእግዚአብሔርንም ክብር ተስፋ በማድረግ ሐሤት እናደርጋለን።
ተራሮች ቢናወጡ፣ ኰረብቶች ከስፍራቸው ቢወገዱ እንኳ፣ ለአንቺ ያለኝ ጽኑ ፍቅር አይናወጥም፤ የገባሁትም የሰላም ቃል ኪዳን አይፈርስም” ይላል መሓሪሽ እግዚአብሔር።
ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማን ነው? ችግር ነው ወይስ ሥቃይ፣ ወይስ ስደት፣ ወይስ ራብ፣ ወይስ ዕራቍትነት፣ ወይስ አደጋ፣ ወይስ ሰይፍ? ይህም፣ “ስለ አንተ ቀኑን ሙሉ እንገደላለን፤ እንደሚታረዱ በጎች ተቈጥረናል” ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። ምንም አይለየንም፤ በዚህ ሁሉ በወደደን በርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን።
በውስጥ ሰውነታችሁ እንድትጠነክሩ፣ ከክብሩ ባለጠግነት በመንፈሱ በኩል ኀይል እንዲሰጣችሁ እጸልያለሁ፤ ይኸውም በእምነት ክርስቶስ በልባችሁ እንዲያድር ነው። ደግሞም ሥር ሰድዳችሁ፣ በፍቅር ታንጻችሁ፣
በእግዚአብሔር የሚታመኑ፣ ሳትናወጥ ለዘላለም እንደምትኖር እንደ ጽዮን ተራራ ናቸው። ተራሮች ኢየሩሳሌምን እንደ ከበቧት፣ ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም፣ እግዚአብሔር በሕዝቡ ዙሪያ ነው።
የእምነታችን ጀማሪና ፍጹም አድራጊ የሆነውን ኢየሱስን እንመልከት፤ እርሱ በፊቱ ስላለው ደስታ መስቀሉን ታግሦ፣ የመስቀሉንም ውርደት ንቆ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጧል።
በልዑል መጠጊያ የሚኖር፣ በሁሉን ቻይ አምላክ ጥላ ሥር ያድራል። ክፉ ነገር አያገኝህም፤ መቅሠፍትም ወደ ድንኳንህ አይገባም፤ በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ፣ እግርህም ከድንጋይ ጋራ እንዳይሰናከል፤ በእጆቻቸው ያነሡህ ዘንድ፣ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዝልሃል። በአንበሳና በእፉኝት ላይ ትጫማለህ፤ ደቦሉን አንበሳና ዘንዶውን ትረግጣለህ። “ወድዶኛልና እታደገዋለሁ፤ ስሜን ዐውቋልና እከልለዋለሁ። ይጠራኛል፤ እመልስለታለሁ፤ በመከራው ጊዜ ከርሱ ጋራ እሆናለሁ፤ አድነዋለሁ፤ አከብረዋለሁ። ረዥም ዕድሜን አጠግበዋለሁ፤ ማዳኔንም አሳየዋለሁ።” እግዚአብሔርን፣ “መጠጊያዬ፣ ምሽጌ፣ የምታመንብህ አምላኬ” እለዋለሁ።
ኢየሱስም እንዲህ አላት፤ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ በሕይወት ይኖራል፤ በእኔ የሚኖር፣ የሚያምንብኝም ከቶ አይሞትም፤ ይህን ታምኛለሽን?”
ይህን ተረድቻለሁ፤ ሞትም ይሁን ሕይወት፣ መላእክትም ይሁኑ አጋንንት፣ ያለውም ይሁን የሚመጣው፣ ወይም ማንኛውም ኀይል፣ ከፍታም ይሁን ጥልቀት ወይም የትኛውም ፍጥረት፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ካለው ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን አይችልም።
የእግዚአብሔር ምሕረት ግን፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም በሚፈሩት ላይ ነው፤ ጽድቁም እስከ ልጅ ልጅ ድረስ በላያቸው ይሆናል፤ ኪዳኑን በሚጠብቁት ላይ፣ ትእዛዙንም ለመፈጸም በሚተጕት ላይ ይሆናል።
ምክንያቱም፣ እግዚአብሔር አስቀድሞ እንድንመላለስባቸው ያዘጋጀልንን መልካም የሆኑትን ሥራዎች እንድንሠራ በክርስቶስ ኢየሱስ የተፈጠርን የእግዚአብሔር እጅ ሥራዎች ነን።
ደግሞም ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሠኘት አይቻልም፤ ምክንያቱም ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሁሉ እግዚአብሔር መኖሩንና ከልብ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጥ ማመን አለበት።
የምንጸልየውም ለጌታ እንደሚገባ እንድትኖሩና በሁሉም ደስ እንድታሰኙት ነው፤ ይኸውም በመልካም ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ እግዚአብሔርን በማወቅ እያደጋችሁ፣ ታላቅ ጽናትና ትዕግሥት ይኖራችሁ ዘንድ፣ እንደ ክቡር ጕልበቱ መጠን በኀይል ሁሉ እየበረታችሁ፣ ደስ እየተሰኛችሁ፣
ዕውሮችን በማያወቁት መንገድ እመራቸዋለሁ፤ ባልተለመደ ጐዳና እወስዳቸዋለሁ። ጨለማውን በፊታቸው ብርሃን አደርጋለሁ፤ ጐርባጣውን ስፍራ አስተካክላለሁ። ይህን አደርጋለሁ፤ አልተዋቸውም።
ወንድሞች ሆይ፤ እኔ ገና እንደ ያዝሁት አድርጌ ራሴን አልቈጥርም፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ ከኋላዬ ያለውን እየረሳሁ ከፊቴ ወዳለው እዘረጋለሁ። እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ላይ ስለ ጠራኝ፣ ሽልማት ለመቀዳጀት ወደ ግቡ እፈጥናለሁ።
ስለዚህ ከቶ የማይናወጥ መንግሥት ስለምንቀበል እግዚአብሔርን እናመስግን፤ ደግሞም ደስ በሚያሠኘው መንገድ በአክብሮትና በፍርሀት እናምልከው፤
ስለዚህ እርሱ በወሰነው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከእግዚአብሔር ብርቱ እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤ እርሱ ስለ እናንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በርሱ ላይ ጣሉት።
አምላክ ሆይ፤ ለእኔ ያለህ ሐሳብ እንዴት ክቡር ነው! ቍጥሩስ ምንኛ ብዙ ነው! ልቍጠራቸው ብል፣ ከአሸዋ ይልቅ ይበዙ ነበር። ተኛሁም ነቃሁም፣ ገና ከአንተው ጋራ ነኝ።
የሰላም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁ፣ ነፍሳችሁና ሥጋችሁ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜ ያለ ነቀፋ ይጠበቁ። የጠራችሁ የታመነ ነው፤ እርሱም ያደርገዋል።
በመጨረሻም ወንድሞች ሆይ፤ እውነት የሆነውን ሁሉ፣ ክቡር የሆነውን ሁሉ፣ ትክክል የሆነውን ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ሁሉ፣ ተወዳጅ የሆነውን ሁሉ፣ መልካም የሆነውን ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን ወይም ምስጋና እንደ እነዚህ ስላሉት ነገሮች አስቡ። ከእኔ የተማራችሁትን ወይም የተቀበላችሁትን፣ የሰማችሁትን ወይም ያያችሁትን ማንኛውንም ነገር አድርጉ፤ የሰላም አምላክም ከእናንተ ጋራ ይሆናል።
እግዚአብሔር አምላክ ፀሓይና ጋሻ ነውና፤ እግዚአብሔር ሞገስንና ክብርን ይሰጣል፤ እግዚአብሔር ያለ ነቀፋ የሚሄዱትን፣ መልካም ነገር አይነፍጋቸውም።
ይህን የምለው ስለ ቸገረኝ አይደለም፤ ምክንያቱም በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ያለኝ ይበቃኛል ማለትን፣ ማጣትን ዐውቀዋለሁ፤ ማግኘትንም ዐውቀዋለሁ። ብጠግብም ሆነ ብራብ፣ ባገኝም ሆነ ባጣ፣ በማንኛውም ሆነ በየትኛውም ሁኔታ ያለኝ ይበቃኛል የማለትን ምስጢር ተምሬአለሁ።
ለመሆኑ፣ ሰውነታችሁ በውስጣችሁ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? ይህም መንፈስ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት ነው። እናንተም የራሳችሁ አይደላችሁም፤ ቅዱሳን በዓለም ላይ እንደሚፈርዱ አታውቁምን? በዓለም ላይ የምትፈርዱ ከሆነ፣ እንግዲያው፣ በትንሹ ነገር ላይ ለመፍረድ አትበቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና፤ ስለዚህ በሰውነታችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።
የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋራ ሆኖ ይመሰክርልናል። ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ የክብሩ ተካፋዮች እንሆን ዘንድ በርግጥ የመከራው ተካፋዮች ብንሆን፣ የእግዚአብሔር ወራሾች፣ ከክርስቶስ ጋራ ዐብረን ወራሾች ነን።
በተረፈ ወንድሞች ሆይ፤ ደኅና ሁኑ፤ ፍጹማን ሁኑ፤ ምክሬን ስሙ፤ አንድ ሐሳብ ይኑራችሁ፤ በሰላምም ኑሩ። የፍቅርና የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋራ ይሆናል።
“ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ አንኳኩ፣ በሩም ይከፈትላችኋል። የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፤ የሚፈልግም ያገኛል፤ ለሚያንኳኳም ይከፈትለታል።
በዘላለም ኪዳን ደም የበጎች ታላቅ እረኛ የሆነውን ጌታችን ኢየሱስን ከሞት ያስነሣው የሰላም አምላክ፣ ፈቃዱን እንድታደርጉ በመልካም ነገር ሁሉ ያስታጥቃችሁ፤ ደስ የሚያሠኘውንም በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእኛ ያድርግ፤ ለርሱ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን። አሜን።
እናንተ ግን ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ እንድታውጁ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ የተቀደሰ ሕዝብ፣ እግዚአብሔር ገንዘቡ ያደረገው ሕዝብ ናችሁ።
በፍቅር ፍርሀት የለም፤ ፍጹም ፍቅር ግን ፍርሀትን አውጥቶ ይጥላል፤ ፍርሀት ከቅጣት ጋራ የተያያዘ ነውና። የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም።