ሕይወታችን ከዲግሪና ከማዕረግ እጅግ የላቀ ትርጉም አለው። እንደ አማኝ፣ ዋና ዓላማችን እግዚአብሔርን ማምለክ ነው። ይህንንም ለማድረግ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር በመሰብሰብ የምስጋናና የእጅ መስጠት መሠዊያ በእርሱ ፊት እናቆማለን።
ትሕትናን፣ ተወስኖ መገኘትንና ልባዊ አምልኮን ስናሳይ እግዚአብሔርን እናወድሳለን። ሰማይንና ምድርን የፈጠረ፣ የሕይወት እስትንፋስ የሰጠን፣ ያዳነን፣ የምሕረት እጁን የዘረጋልን፣ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የመንግሥተ ሰማያትን ተስፋ የሰጠንን ሕያው እግዚአብሔርን በማምለክ ረገድ ቅዱስ ሩሑ ይመራናል።
እንደ ዮሐንስ ወንጌል 4:23 እውነተኛ አምላኪዎች አብን በመንፈስና በእውነት የሚያመልኩበት ጊዜ ደርሷል፤ አብም እንደነዚህ ያሉትን አምላኪዎች ይፈልጋል።
ዋይታዬን ወደ ሽብሸባ ለወጥህልኝ፤ ማቄን አውልቀህ ፍሥሓን አለበስኸኝ፤ እንግዲህ ነፍሴ ታመስግንህ፤ ዝምም አትበል፤ እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ ለዘላለም አመሰግንሃለሁ።
ነፍሴ ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኪ፤ የውስጥ ሰውነቴም ሁሉ ቅዱስ ስሙን ባርኪ። እንደ ኀጢአታችን አልመለሰልንም፤ እንደ በደላችንም አልከፈለንም። ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፣ እንዲሁ ለሚፈሩት ምሕረቱ ታላቅ ናት። ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፣ መተላለፋችንን በዚያው መጠን ከእኛ አስወገደ። አባት ለልጆቹ እንደሚራራ፣ እግዚአብሔር ለሚፈሩት እንዲሁ ይራራል። እርሱ አፈጣጠራችንን ያውቃልና፤ ትቢያ መሆናችንንም ያስባል። ሰው እኮ ዘመኑ እንደ ሣር ነው፤ እንደ ዱር አበባ ያቈጠቍጣል፤ ነፋስ በነፈሰበት ጊዜ ግን ድራሹ ይጠፋል፤ ምልክቱም በቦታው አይገኝም። የእግዚአብሔር ምሕረት ግን፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም በሚፈሩት ላይ ነው፤ ጽድቁም እስከ ልጅ ልጅ ድረስ በላያቸው ይሆናል፤ ኪዳኑን በሚጠብቁት ላይ፣ ትእዛዙንም ለመፈጸም በሚተጕት ላይ ይሆናል። እግዚአብሔር ዙፋኑን በሰማይ አጽንቷል፤ መንግሥቱም ሁሉን ትገዛለች። ነፍሴ ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኪ፤ ውለታውንም ሁሉ አትርሺ፤
ምድር ሁሉ ለእግዚአብሔር እልል በሉ፤ እግዚአብሔርን በደስታ አገልግሉት፤ በፍሥሓ ዝማሬ ፊቱ ቅረቡ። እግዚአብሔር አምላክ መሆኑን ዕወቁ፤ እርሱ ፈጠረን፤ እኛም የርሱ ነን፤ እኛ ሕዝቡ የማሰማሪያው በጎች ነን። በምስጋና ወደ ደጆቹ፣ በውዳሴም ወደ አደባባዮቹ ግቡ፤ አመስግኑት፤ ስሙንም ባርኩ፤ እግዚአብሔር ቸር፣ ምሕረቱም ለዘላለም ነውና፤ ታማኝነቱም ከትውልድ እስከ ትውልድ ነው።
ምድር ሁሉ ለእግዚአብሔር እልል ይበል! አምላክ ሆይ፤ አንተ ፈተንኸን፤ እንደ ብርም አነጠርኸን። ወደ ወጥመድ አገባኸን፤ በጀርባችንም ሸክም ጫንህብን። ሰዎች በራሳችን ላይ እንዲፈነጩ አደረግህ፤ በእሳትና በውሃ መካከል ዐለፍን፤ የኋላ ኋላ ግን ወደ በረከት አመጣኸን። የሚቃጠል መሥዋዕት ይዤ ወደ መቅደስህ እገባለሁ፤ ስእለቴንም ለአንተ እፈጽማለሁ፤ በመከራ ጊዜ ከአፌ የወጣ፣ በከንፈሬም የተናገርሁት ስእለት ነው። ፍሪዳዎችን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጌ፣ አውራ በጎችንም የሚጤስ ቍርባን አድርጌ አቀርብልሃለሁ፤ ኰርማዎችንና ፍየሎችንም እሠዋልሃለሁ። ሴላ እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሁሉ፤ ኑና ስሙ፤ ለነፍሴ ያደረገላትን ልንገራችሁ። በአፌ ወደ እርሱ ጮኽሁ፤ በአንደበቴም አመሰገንሁት። ኀጢአትን በልቤ አስተናግጄ ቢሆን ኖሮ፣ ጌታ ባልሰማኝ ነበር። አሁን ግን እግዚአብሔር በርግጥ ሰምቶኛል፤ ጸሎቴንም አድምጧል። ለስሙ ክብር ዘምሩ፤ ውዳሴውንም አድምቁ።
ለመሪዎቻችሁ ታዘዙ፤ ተገዙላቸውም፤ ምክንያቱም እነርሱ በብርቱ የሚያስጠይቃቸው ነገር ስላለባቸው፣ ስለ ነፍሳችሁ ጕዳይ ይተጋሉ። ስለዚህ ሥራቸውን በሐዘን ሳይሆን በደስታ ማከናወን እንዲችሉ ታዘዟቸው፤ አለዚያ አይበጃችሁም።
በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ ይህ ባይሆንማ ኖሮ እነግራችሁ ነበር፤ የምሄደውም ስፍራ ላዘጋጅላችሁ ነው። እኔ በአባቴ እንዳለሁ፣ እናንተም በእኔ እንዳላችሁ፣ እኔም ደግሞ በእናንተ እንዳለሁ በዚያ ቀን ትረዳላችሁ። የሚወድደኝ ትእዛዜን ተቀብሎ የሚጠብቅ ነው፤ የሚወድደኝንም አባቴ ይወድደዋል፤ እኔም እወድደዋለሁ፤ ራሴንም እገልጥለታለሁ።” ከዚያም የአስቆሮቱ ያልሆነው ይሁዳ፣ “ጌታ ሆይ፤ ታዲያ፣ ለዓለም ሳይሆን ራስህን ለእኛ የምትገልጠው እንዴት ነው?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “የሚወድደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወድደዋል፤ ወደ እርሱ እንመጣለን፤ ከርሱም ጋራ እንኖራለን። የማይወድደኝ ቃሌን አይጠብቅም። ይህ የምትሰሙት ቃል የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም። “አሁን ከእናንተ ጋራ እያለሁ ይህን ሁሉ ነግሬአችኋለሁ፤ አብ በስሜ የሚልከው አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ ግን ሁሉን ነገር ያስተምራችኋል፤ እኔ የነገርኋችሁንም ሁሉ ያሳስባችኋል። ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጣችሁ አይደለም። ልባችሁ አይጨነቅ፤ አይፍራም። “ ‘እሄዳለሁ፤ ተመልሼም ወደ እናንተ እመጣለሁ’ ማለቴን ሰምታችኋል፤ ብትወድዱኝስ አብ ከእኔ ስለሚበልጥ ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር፤ የተናገርሁት ሲፈጸም እንድታምኑ፣ ከመሆኑ በፊት አሁን ነግሬአችኋለሁ። ሄጄም ስፍራ ካዘጋጀሁላችሁ በኋላ፣ እኔ ባለሁበት እናንተም ከእኔ ጋራ እንድትሆኑ ልወስዳችሁ ዳግመኛ እመጣለሁ።
በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል፤ አሁንም መጥቷል፤ አብም እንደዚህ በእውነት የሚሰግዱለትን ይፈልጋል። እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ይገባል።”
እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ በእናንተ መካከል በትጋት የሚሠሩትን፣ በጌታም የበላዮቻችሁና መካሪዎቻችሁ የሆኑትን እንድታከብሯቸው እንለምናችኋለን፤ ስለ ሥራቸውም በፍቅር እጅግ አክብሯቸው። እርስ በርሳችሁም በሰላም ኑሩ።
ኑ፤ ደስ እያለን ለእግዚአብሔር እንዘምር፤ በድነታችንም ዐለት እልል እንበል። ያን ትውልድ አርባ ዓመት ሙሉ ተቈጣሁት፤ እኔም፣ “በልቡ የሳተ ሕዝብ ነው፤ መንገዴንም አላወቀም” አልሁ። ስለዚህ እንዲህ ብዬ በቍጣዬ ማልሁ፣ “ፈጽሞ ወደ ዕረፍቴ አይገቡም።” ምስጋና ይዘን ፊቱ እንቅረብ፤ በዝማሬም እናወድሰው። እግዚአብሔር ታላቅ አምላክ ነውና፤ ከአማልክትም ሁሉ በላይ ታላቅ ንጉሥ ነው። የምድር ጥልቆች በእጁ ናቸው፤ የተራራ ጫፎችም የርሱ ናቸው። እርሱ ፈጥሯታልና ባሕር የርሱ ናት፤ እጁም የብስን አበጀ። ኑ፤ እናምልከው፤ እንስገድለትም፤ በፈጣሪያችን በእግዚአብሔር ፊት እንንበርከክ፤ እርሱ አምላካችን ነውና፤ እኛም በእጁ ጥበቃ ሥር ያለን በጎቹ፣ የመሰማሪያውም ሕዝብ ነን። ዛሬ ድምፁን ብትሰሙ፣
ኑ፤ ደስ እያለን ለእግዚአብሔር እንዘምር፤ በድነታችንም ዐለት እልል እንበል። ያን ትውልድ አርባ ዓመት ሙሉ ተቈጣሁት፤ እኔም፣ “በልቡ የሳተ ሕዝብ ነው፤ መንገዴንም አላወቀም” አልሁ። ስለዚህ እንዲህ ብዬ በቍጣዬ ማልሁ፣ “ፈጽሞ ወደ ዕረፍቴ አይገቡም።” ምስጋና ይዘን ፊቱ እንቅረብ፤ በዝማሬም እናወድሰው። እግዚአብሔር ታላቅ አምላክ ነውና፤ ከአማልክትም ሁሉ በላይ ታላቅ ንጉሥ ነው።
ለራሳችሁና መንፈስ ቅዱስ ኤጲስ ቆጶሳት አድርጎ በላዩ ለሾማችሁ መንጋ ሁሉ ተጠንቀቁ፤ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ጠብቁ።
ሃሌ ሉያ። እግዚአብሔርን በመቅደሱ አመስግኑት፤ በታላቅ ጠፈሩ አመስግኑት። ስለ ብርቱ ሥራው አመስግኑት፤ እጅግ ታላቅ ነውና አመስግኑት። በመለከት ድምፅ አመስግኑት፤ በበገናና በመሰንቆ ወድሱት። በከበሮና በሽብሸባ አመስግኑት፤ በባለአውታር መሣሪያና በእንቢልታ አመስግኑት። ተርገብጋቢ ድምፅ ባለው ጸናጽል አመስግኑት፤ ድምፀ መልካም በሆነ ጸናጽል አመስግኑት። እስትንፋስ ያለው ሁሉ እግዚአብሔርን ያመስግን። ሃሌ ሉያ።
እነርሱም በሐዋርያት ትምህርትና በኅብረት፣ እንጀራውንም በመቍረስና በጸሎት ይተጉ ነበር። በሐዋርያት እጅ ብዙ ድንቅና ታምራት ይደረግ ስለ ነበር፣ ሰው ሁሉ ፍርሀት ዐደረበት። ያመኑት ሁሉ በአንድነት ነበሩ፤ ያላቸውንም ሁሉ የጋራ አደረጉ። ሀብታቸውንና ንብረታቸውንም እየሸጡ ለእያንዳንዱ ሰው የሚያስፈልገውን ያህል ይሰጡት ነበር። በየዕለቱ በቤተ መቅደስ በአንድነት እየተገናኙ፣ በቤታቸውም እንጀራ እየቈረሱ በደስታና በቀና ልብ ይመገቡ ነበር፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፣ በሕዝቡ ሁሉ ፊት ሞገስ ነበራቸው፤ ጌታም የሚድኑትን በቍጥራቸው ላይ ዕለት በዕለት ይጨምር ነበር።
በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን እንጀራ ለመቍረስ ተሰብስበን ሳለን፣ ጳውሎስ በማግስቱም ለመሄድ ስላሰበ፣ ከእነርሱ ጋራ ይነጋገር ነበር፤ ንግግሩንም እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ አራዘመ።
በዚያ ቀን እንዲህ ትላላችሁ፤ “እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ስሙንም ጥሩ፤ ያደረገውንም በአሕዛብ መካከል አስታውቁ፤ ስሙ ከፍ ከፍ ማለቱንም ዐውጁ። ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ታላቅ ሥራ ሠርቷልና፤ ይህም ለዓለም ሁሉ ይታወቅ። የጽዮን ሕዝብ ሆይ፤ እልል በሉ፤ በደስታም ዘምሩ፤ በመካከላችሁ ያለው የእስራኤል ቅዱስ ታላቅ ነውና።”
እግዚአብሔርን ሁልጊዜ እባርከዋለሁ፤ ምስጋናውም ዘወትር ከአፌ አይለይም። አንበሶች ሊያጡ፣ ሊራቡም ይችላሉ፤ እግዚአብሔርን የሚሹ ግን መልካም ነገር አይጐድልባቸውም። ልጆቼ ሆይ፣ ኑ፤ ስሙኝ፤ እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራችኋለሁ። ሕይወትን የሚወድድ፣ በጎውንም ያይ ዘንድ ዕድሜን የሚመኝ ማን ነው? አንደበትህን ከክፉ ነገር ከልክል፤ ከንፈርህንም ከሽንገላ ጠብቅ። ከክፉ ሽሽ፤ መልካሙንም አድርግ፤ ሰላምን ፈልጋት፤ ተከተላትም። የእግዚአብሔር ዐይኖች ወደ ጻድቃን ናቸው፤ ጆሮዎቹም ለጩኸታቸው ክፍት ናቸው። የእግዚአብሔር ፊት ግን፣ መታሰቢያቸውን ከምድር ለማጥፋት በክፉ አድራጊዎች ላይ ነው። ጻድቃን ሲጮኹ፣ እግዚአብሔር ይሰማቸዋል፤ ከመከራቸውም ሁሉ ያድናቸዋል። እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል። የጻድቅ መከራው ብዙ ነው፤ እግዚአብሔር ግን ከሁሉም ያድነዋል። ነፍሴ በእግዚአብሔር ተመካች፤ ትሑታንም ይህን ሰምተው ሐሤት ያደርጋሉ። ዐጥንቶቹን ሁሉ ይጠብቃል፤ ከእነርሱም አንድ አይሰበርም። ኀጢአተኞችን ክፋት ይገድላቸዋል፤ ጻድቃንን የሚጠሉ ይፈረድባቸዋል። እግዚአብሔር የባሪያዎቹን ነፍስ ይቤዣል፤ እርሱንም መጠጊያ ያደረገ አይፈረድበትም። ኑና ከእኔ ጋራ እግዚአብሔርን አክብሩት፤ ስሙንም በአንድነት ከፍ ከፍ እናድርግ።
የክርስቶስ ቃል በሙላት ይኑርባችሁ፤ እርስ በርሳችሁ በጥበብ ሁሉ ተማማሩ፤ ተመካከሩ፤ በመዝሙርና በማሕሌት፣ በመንፈሳዊም ቅኔ በማመስገን በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ።
እርስ በርሳችንም ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንዴት እንደምንነቃቃ እናስብ። አንዳንዶች ማድረጉን እንደተዉት መሰብሰባችንን አንተው፤ ይልቁንም ቀኑ እየተቃረበ መምጣቱን ስታዩ እርስ በርሳችን እንበረታታ።
እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ አንተ ያደረግኸው ድንቅ ነገር ብዙ ነው፤ ለእኛ ያቀድኸውን፣ ሊዘረዝርልህ የሚችል ማንም የለም፤ ላውራው ልናገረው ብል፣ ስፍር ቍጥር አይኖረውም።
ምድር ሁሉ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ማዳኑንም ዕለት ዕለት ዐውጁ። ክብሩን ለአሕዛብ ተናገሩ፤ ድንቅ ሥራዎቹን ለሕዝቦች ሁሉ ንገሩ። እግዚአብሔር ታላቅ ነውና፤ ውዳሴውም ብዙ ነው፤ ከአማልክትም ሁሉ በላይ ሊፈራ ይገባዋል።
ብርታትንና መጽናናትን የሚሰጥ አምላክ፣ ክርስቶስ ኢየሱስን ስትከተሉ፣ በመካከላችሁ አንድ ሐሳብ ይስጣችሁ፤ ይኸውም በአንድ ልብና በአንድ አፍ ሆናችሁ፣ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክና አባት ታከብሩ ዘንድ ነው።
ሕዝቦች ሁላችሁ እጆቻችሁን አጨብጭቡ፤ ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር እልል በሉ። በምድር ሁሉ ላይ ታላቅ የሆነው ንጉሥ፣ ልዑል እግዚአብሔር የሚያስፈራ ነውና።
በመዝሙርና በውዳሴ፣ በመንፈሳዊም ዝማሬ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ በልባችሁ ለጌታ ተቀኙ፤ አዚሙም። ክርስቶስ እንደ ወደደን ራሱንም ስለ እኛ መልካም መዐዛ ያለው መባና መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር እንደ ሰጠ እናንተም በፍቅር ተመላለሱ። በዚህም እግዚአብሔር አብን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስለ ሁሉ ነገር ሁልጊዜ አመስግኑ።
እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አምላኬ ነህ፤ አንተን ከልብ እሻለሁ፤ ውሃ በሌለበት፣ በደረቅና በተራቈተ ምድር፣ ነፍሴ አንተን ተጠማች፤ ሥጋዬም አንተን ናፈቀች። ለሰይፍ ዐልፈው ይሰጣሉ፤ የቀበሮዎችም ምግብ ይሆናሉ። ንጉሥ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለዋል፤ በእግዚአብሔርም ስም ቃል የሚገቡ ሁሉ ይከብራሉ፤ የሐሰተኞች አንደበትም ትዘጋለች። ስለዚህ በመቅደስ ውስጥ አየሁህ፤ ኀይልህንና ክብርህንም ተመለከትሁ። ምሕረትህ ከሕይወት ይበልጣልና፤ ከንፈሮቼ ያመሰግኑሃል።
ሃሌ ሉያ። የእግዚአብሔር አገልጋዮች ሆይ፤ አመስግኑት፤ የእግዚአብሔርን ስም አወድሱ። ከአሁን እስከ ዘላለም፣ የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን። ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ድረስ፣ የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን።
እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አምላኬ ነህ፤ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፤ ስምህንም አወድሳለሁ፤ አስቀድሞ የታሰበውን፣ ድንቅ ነገር፣ በፍጹም ታማኝነት አድርገሃልና።
እናንተ የምትታመኑት፤ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ቅዱስ ስሙንም አወድሱ። ቍጣው ለዐጭር ጊዜ ነው፤ ቸርነቱ ግን እስከ ዕድሜ ልክ ነውና፤ ሌሊቱን በልቅሶ ቢታደርም፣ በማለዳ ደስታ ይመጣል።
እግዚአብሔርን አንዲት ነገር እለምነዋለሁ፤ እርሷንም እሻለሁ፤ ይኸውም በሕይወቴ ዘመን ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፣ የእግዚአብሔርን ክብር ውበት አይ ዘንድ፣ በመቅደሱም ሆኜ አሰላስል ዘንድ ነው።
እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ሰውነታችሁን ቅዱስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕያው መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፤ ይህም እንደ ባለ አእምሮ የምታቀርቡት አምልኳችሁ ነው።
እናንተ ግን ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ እንድታውጁ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ የተቀደሰ ሕዝብ፣ እግዚአብሔር ገንዘቡ ያደረገው ሕዝብ ናችሁ።