እኔም ልሰግድለት በእግሩ ሥር ተደፋሁ፤ እርሱ ግን፣ “ተው! ይህን አታድርግ! እኔም ከአንተና የኢየሱስን ምስክር ከያዙት ወንድሞችህ ጋራ አገልጋይ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ የኢየሱስ ምስክር የትንቢት መንፈስ ነውና” አለኝ።
“ማንም ሰው ሁለት ጌቶችን ማገልገል አይችልም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወድዳል፤ ወይም አንዱን አክብሮ ሌላውን ይንቃል። እግዚአብሔርንና ገንዘብን በአንድነት ማገልገል አይቻልም።
ሳሙኤልም የእስራኤልን ቤት ሁሉ፣ “በፍጹም ልባችሁ ወደ እግዚአብሔር የምትመለሱ ከሆነ፣ ሌሎችን አማልክትና አስታሮትን ከመካከላችሁ አስወግዱ፤ ራሳችሁንም ለእግዚአብሔር አሳልፋችሁ ስጡ፤ እርሱንም ብቻ አምልኩ፤ እርሱም ከፍልስጥኤማውያን እጅ ይታደጋችኋል።” አላቸው።
እግዚአብሔርን ማምለክ የማያስፈልግ መስሎ ከታያችሁ ግን፣ የቀድሞ አባቶቻችሁ ከወንዙ ማዶ ካመለኳቸው አማልክት ወይም በምድራቸው የምትኖሩባቸው አሞራውያን ከሚያመልኳቸው አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ የምታመልኩትን ዛሬውኑ ምረጡ፤ እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን።”
ከዚያም የእግዚአብሔርን ታቦት አምጥተው ዳዊት በተከለለት ድንኳን ውስጥ አኖሩት፤ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕትም በእግዚአብሔር ፊት አቀረቡ።
እግዚአብሔር ግን እውነተኛ አምላክ ነው፤ እርሱ ሕያው አምላክ፣ ዘላለማዊም ንጉሥ ነው፤ በሚቈጣበት ጊዜ ምድር ትንቀጠቀጣለች፤ መንግሥታትም ቍጣውን ሊቋቋሙ አይችሉም።
“አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩ፤ በፍጹም ታማኝነትም ተገዙለት። የቀድሞ አባቶቻችሁ ከወንዙ ማዶና በግብጽ ያመለኳቸውን አማልክት ከእናንተ አርቁ፤ እግዚአብሔርን ብቻ አምልኩ። እግዚአብሔርን ማምለክ የማያስፈልግ መስሎ ከታያችሁ ግን፣ የቀድሞ አባቶቻችሁ ከወንዙ ማዶ ካመለኳቸው አማልክት ወይም በምድራቸው የምትኖሩባቸው አሞራውያን ከሚያመልኳቸው አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ የምታመልኩትን ዛሬውኑ ምረጡ፤ እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን።”
የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ፣ አምላካችሁን እግዚአብሔርን እንድትወድዱ፣ በመንገዱ ሁሉ እንድትሄዱ፣ ትእዛዙን እንድትፈጽሙ፣ እርሱንም አጥብቃችሁ እንድትይዙት እንዲሁም በፍጹም ልባችሁ፣ በፍጹም ነፍሳችሁ እንድታገለግሉት የሰጣችሁን ትእዛዙንና ሕጉን ነቅታችሁ ጠብቁ።”
ስለዚህ ከቶ የማይናወጥ መንግሥት ስለምንቀበል እግዚአብሔርን እናመስግን፤ ደግሞም ደስ በሚያሠኘው መንገድ በአክብሮትና በፍርሀት እናምልከው፤
በእንዴት ያለ አቀባበል እንደ ተቀበላችሁንና ሕያውና እውነተኛ የሆነውን አምላክ ለማገልገል ከጣዖታት ወደ እግዚአብሔር እንዴት እንደ ተመለሳችሁ እነርሱ ራሳቸው ይናገራሉ፤
እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ሰውነታችሁን ቅዱስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕያው መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፤ ይህም እንደ ባለ አእምሮ የምታቀርቡት አምልኳችሁ ነው።
ለእኛ ግን ሁሉም ነገር ከርሱ የሆነ፣ እኛም ለርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን፤ ደግሞም ሁሉም ነገር በርሱ አማካይነት የሆነ፣ እኛም በርሱ አማካይነት የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን።
የምታደርጉትን ሁሉ ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉት ቈጥራችሁ በሙሉ ልባችሁ አድርጉት፤ ከጌታ ዘንድ እንደ ብድራት የምትቀበሉት ርስት እንዳለ ታውቃላችሁና፤ የምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስን ነው።
ኤልያስም በሕዝቡ ፊት ቀርቦ፣ “በሁለት ሐሳብ የምትዋልሉት እስከ መቼ ድረስ ነው? እግዚአብሔር አምላክ ከሆነ እግዚአብሔርን ተከተሉ፤ በኣል አምላክ ከሆነም በኣልን ተከተሉ” አለ። ሕዝቡ ግን አንዲት ቃል አልመለሱም።
ከእናንተ ማንም የሚናገር ቢኖር እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር፤ የሚያገለግልም ቢኖር እግዚአብሔር በሚሰጠው ብርታት ያገልግል፤ ይኸውም እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እንዲከብር ነው። ክብርና ኀይል ለርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን። አሜን።
አሁን እኔ ተቀባይነት ለማግኘት የምሻው በሰዎች ዘንድ ነው ወይስ በእግዚአብሔር ዘንድ? ወይስ ሰዎችን ደስ ለማሠኘት እየተጣጣርሁ ነው? ሰዎችን ደስ ለማሠኘት የምጥር ብሆን ኖሮ፣ የክርስቶስ ባሪያ ባልሆንሁ ነበር።
ነገር ግን ወንጌልን በዐደራ ለመቀበል እግዚአብሔር ብቁ አድርጎ እንደ ቈጠራቸው ሰዎች ሆነን እንናገራለን። ይህንም የምናደርገው ልባችንን የሚመረምረውን እግዚአብሔርን እንጂ ሰዎችን ደስ ለማሠኘት ብለን አይደለም።
ይህም የተባረከ ተስፋችን የሆነውን የታላቁን የአምላካችንንና የአዳኛችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ በመጠባበቅ ነው፤ እርሱም ከክፋት ሊቤዠን፣ መልካም የሆነውን ለማድረግ የሚተጋውን የርሱ የሆነውን ሕዝብም ለራሱ ያነጻ ዘንድ ራሱን ስለ እኛ ሰጥቷል።
በዘላለም መንፈስ አማካይነት ራሱን ነውር አልባ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቀረበው የክርስቶስ ደም፣ ሕያው እግዚአብሔርን እንድናመልክ ኅሊናችንን ከምውት ሥራ እንዴት ይበልጥ ያነጻ ይሆን!
እናንተ ግን ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ እንድታውጁ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ የተቀደሰ ሕዝብ፣ እግዚአብሔር ገንዘቡ ያደረገው ሕዝብ ናችሁ።
ከዚያም በሰማይና በምድር፣ ከምድር በታችና በባሕር፣ በእነርሱ ውስጥ ያሉ ፍጥረታትም ሁሉ እንዲህ ብለው ሲዘምሩ ሰማሁ፤ “በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠውና ለበጉ፣ ምስጋናና ሞገስ፣ ክብርና ኀይል፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን።”
እርሱ ግን፣ “ተው፤ ይህን አታድርግ እኔ ከአንተና ከወንድሞችህ ከነቢያት እንዲሁም የዚህን መጽሐፍ ቃል ከሚጠብቁት ሁሉ ጋራ አገልጋይ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ” አለኝ።
“አንተም ልጄ ሰሎሞን ሆይ፤ እግዚአብሔር ልብን ሁሉ ስለሚመረምርና ሐሳብን ሁሉ ስለሚያውቅ፣ የአባትህን አምላክ ዕወቅ፤ በፍጹም ልብና በበጎ ፈቃድ አገልግለው። ከፈለግኸው ታገኘዋለህ፤ ከተውኸው ግን እርሱም ለዘላለም ይተውሃል።
“ማንም ባሪያ ሁለት ጌቶችን ማገልገል አይችልም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወድዳል፤ ወይም አንዱን አክብሮ ሌላውን ይንቃል። እግዚአብሔርንና ገንዘብን በአንድነት ማገልገል አይቻልም።”
እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ጋራ ኪዳን ሲገባ እንዲህ ሲል አዝዟቸው ነበር፤ “ሌሎችን አማልክት አትፍሯቸው፤ አትስገዱላቸው፤ አታገልግሏቸው፤ አትሠዉላቸውም፤
ሳሙኤልም እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “አትፍሩ፤ ይህን ሁሉ ክፋት አድርጋችኋል፤ ሆኖም እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችሁ አምልኩት እንጂ እግዚአብሔርን ከመከተል ፈቀቅ አትበሉ። ሊጠቅሟችሁ ወይም ሊያድኗችሁ የማይችሉ ምናምንቴ ነገሮችን አትከተሉ፤ ከንቱ ናቸውና።
ዛሬ እኔ የምሰጣችሁን ትእዛዞች በታማኝነት ብትጠብቁ፣ ይኸውም አምላካችሁን እግዚአብሔርን ብትወድዱና በፍጹም ልባችሁ፣ በፍጹም ነፍሳችሁም እርሱን በማገልገል በታማኝነት ብትጠብቁ፣
እስራኤል ሆይ ስማ፤ እግዚአብሔር አምላካችን፣ እግዚአብሔር አንድ ነው። አንተም እግዚአብሔር አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህ ውደድ።
አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ ከአማልክት መካከል፣ እንደ አንተ ማን አለ? በቅድስናው የከበረ፣ በክብሩ የሚያስፈራ፣ ድንቆችን የሚያደርግ፣ እንደ አንተ ማን አለ?
በሌላ ስፍራ ሺሕ ቀን ከመኖር፣ በአደባባይህ አንዲት ቀን መዋል ይሻላል፤ በክፉዎች ድንኳን ከመቀመጥ ይልቅ፣ በአምላኬ ቤት ደጅ መቆም እመርጣለሁ።
አምላኬና ንጉሤ ሆይ፤ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፤ ስምህን ከዘላለም እስከ ዘላለም እባርካለሁ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ፍጥረትህ ሁሉ ያመሰግንሃል፤ ቅዱሳንህም ይባርኩሃል። ስለ መንግሥትህ ክብር ይናገራሉ፤ ስለ ኀይልህም ይነጋገራሉ፤ በዚህም ለሰው ልጆች ብርቱ ሥራህን፣ የመንግሥትህንም ግርማ ክብር ያስታውቃሉ። መንግሥትህ የዘላለም መንግሥት ናት፤ ግዛትህም ለትውልድ ሁሉ ጸንቶ ይኖራል። እግዚአብሔር ቃሉን ሁሉ ይጠብቃል፤ በሥራውም ሁሉ ቸር ነው። እግዚአብሔር የሚንገዳገዱትን ሁሉ ይደግፋል፤ የወደቁትንም ሁሉ ያነሣል። የሁሉ ዐይን አንተን በተስፋ ይጠብቃል፤ አንተም ምግባቸውን በወቅቱ ትሰጣቸዋለህ። አንተ እጅህን ትዘረጋለህ፤ የሕያዋን ፍጥረታትንም ሁሉ ፍላጎት ታረካለህ። እግዚአብሔር በመንገዱ ሁሉ ጻድቅ፣ በሥራውም ሁሉ ቸር ነው። እግዚአብሔር ለሚጠሩት ሁሉ፣ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው። ለሚፈሩት ፍላጎታቸውን ይፈጽማል፤ ጩኸታቸውን ይሰማል፤ ያድናቸዋልም። በየቀኑ እባርክሃለሁ፤ ስምህንም ከዘላለም እስከ ዘላለም አመሰግናለሁ።
ከዚያም እኔ በእስራኤል መካከል እንዳለሁ፣ እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ፣ እንደ እኔም ያለ፣ ሌላ እንደሌለ ታውቃላችሁ፤ ሕዝቤም ከእንግዲህ ወዲያ አያፍርም።
በዚያ ቀን እንዲህ ትላላችሁ፤ “እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ስሙንም ጥሩ፤ ያደረገውንም በአሕዛብ መካከል አስታውቁ፤ ስሙ ከፍ ከፍ ማለቱንም ዐውጁ።
ሰውየውም መልሶ፣ “ ‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህና በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ’ ይላል” አለው።
በአንቺ ላይ እንዲደገን የተበጀ መሣሪያ ይከሽፋል፤ የሚከስሽንም አንደበት ሁሉ ትረቺያለሽ፤ እንግዲህ የእግዚአብሔር ባሪያዎች ርስት ይህ ነው፤ ከእኔ የሚያገኙትም ጽድቃቸው ይኸው ነው፤” ይላል እግዚአብሔር።
አሁንም እስራኤል ሆይ፤ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? አምላክህን እግዚአብሔርን እንድትፈራው፣ በመንገዶቹ ሁሉ እንድትሄድ፣ እንድትወድደው፣ በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ እንድታገለግለው፣ መልካም እንዲሆንልህና ዛሬ እኔ የምሰጥህን ትእዛዞችና የእግዚአብሔር ሥርዐቶች እንድትጠብቅ አይደለምን?
ከዚህም በላይ ለርሱ ብዬ ሁሉን ነገር የተውሁለትን፣ ወደር የሌለውን ጌታዬን ክርስቶስ ኢየሱስን ከማወቅ ታላቅነት ጋራ ሳነጻጽር፣ ሁሉንም ነገር እንደ ጕድለት እቈጥረዋለሁ፤ ለርሱ ስል ሁሉን ዐጥቻለሁ፤ ክርስቶስን አገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቈጥራለሁ፤
የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፤ አንተ ግን ከዚህ ሁሉ ሽሽ፤ ጽድቅን፣ እውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወትን፣ እምነትን፣ ፍቅርን፣ ትዕግሥትንና ገርነትን ተከታተል።
“ጌታውም፣ ‘ደግ አድርገሃል፤ አንተ መልካም ታማኝ ባሪያ፤ በትንሽ ነገር ላይ ታማኝ ስለ ሆንህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው።
በእግዚአብሔር ወንጌል የክህነት ተግባር፣ ለአሕዛብ የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ ለመሆን ነው፤ ይኸውም አሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ ተቀድሰው በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት እንዲሆኑ ነው።
ዓለምን ወይም በዓለም ያለውን ማንኛውንም ነገር አትውደዱ፤ ማንም ዓለምን ቢወድድ የአብ ፍቅር በርሱ ዘንድ የለም፤ ምክንያቱም በዓለም ያለው ሁሉ፦ የሥጋ ምኞት፣ የዐይን አምሮትና የኑሮ ትምክሕት ከዓለም እንጂ ከአብ የሚመጣ አይደለም። ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል።
እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፤ አንዳች አይጐድልብኝም። በለመለመ መስክ ያሳርፈኛል፤ በዕረፍት ውሃ ዘንድ ይመራኛል፤ ነፍሴንም ይመልሳታል። ስለ ስሙም፣ በጽድቅ መንገድ ይመራኛል።