ወላጆቻችንም እንደኛው ሰው ናቸው፤ ጥሩ ጎናቸውም መጥፎ ጎናቸውም አላቸው። በህይወታችን ብዙ አስቸጋሪ ጊዜያትን እንደ ቤተሰብ አሳልፈናል። ከአስርቱ ትእዛዛት አንዱ ወላጆቻችንን ማክበር ነው። እግዚአብሔር ከእነሱ ጋር ጥሩ ግንኙነት ባይኖረንም እንኳ ትእዛዛቱን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንድንጠብቅ ይፈልጋል። ስለዚህ፣ ለግል ፍላጎቶቻቸውና ከእግዚአብሔር ጋር ስላላቸው ግንኙነት ከመጸለይ ባሻገር፣ ከእነሱ ጋር ስላለን ግንኙነትም መጸለይ አለብን። («አባትህንና እናትህን አክብር፤ እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ እንዲረዝም።» (ዘጸአት 20:12))። ሁልጊዜም ወላጆቻችንን መባረክ እና በህይወታቸው መልካም የሆነውን ከማድረግ ወደ ኋላ ማለት የለብንም።
ልጄ ሆይ፤ የአባትህን ምክር አድምጥ፤ የእናትህንም ትምህርት አትተው። ለራስህ ሞገስን የሚያጐናጽፍ አክሊል፣ ዐንገትህን የሚያስውብ ድሪ ይሆንልሃል።
ልጆቼ ሆይ፤ የአባትን ምክር አድምጡ፤ ልብ ብላችሁ ስሙ፤ ማስተዋልንም ገንዘብ አድርጉ። ልጄ ሆይ፤ አድምጠኝ፤ ቃሌንም ልብ በል፤ የሕይወት ዘመንህም ትበዛለች። በጥበብ ጐዳና አስተምርሃለሁ፤ ቀጥተኛውንም መንገድ አሳይሃለሁ። ስትሄድ ርምጃህ አይሰናከልም፤ ስትሮጥም አትደናቀፍም። ምክርን አጥብቀህ ያዛት፤ አትልቀቃት፤ ጠብቃት፤ ሕይወትህ ናትና። ወደ ኃጥኣን ጐዳና እግርህን አታንሣ፤ በክፉ ሰዎች መንገድ አትሂድ፤ ከዚያ አትድረስ፤ አትጓዝበት፤ ሽሸው፤ መንገድህን ይዘህ ሂድ፤ ክፉ ካላደረጉ አይተኙምና፤ ሰውን ካላሰናከሉ እንቅልፍ በዐይናቸው አይዞርም። የክፋት እንጀራ ይበላሉ፤ የዐመፅ ወይን ጠጅ ይጠጣሉ። የጻድቃን መንገድ ሙሉ ቀን እስኪሆን ድረስ፣ ብርሃኑ እየጐላ እንደሚሄድ የማለዳ ውጋጋን ነው። የክፉዎች መንገድ ግን እንደ ድቅድቅ ጨለማ ነው፤ ምን እንደሚያሰናክላቸውም አያውቁም። በጎ ትምህርት እሰጣችኋለሁ፤ ስለዚህ ትምህርቴን አትተዉ።
እነሆ፤ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው፤ የማሕፀንም ፍሬ ከቸርነቱ የሚገኝ ነው። በወጣትነት የተገኙ ወንዶች ልጆች፣ በጦረኛ እጅ እንዳሉ ፍላጾች ናቸው። ብፁዕ ነው፤ ኰረጆዎቹ በእነዚህ የተሞሉ ሰው፤ ከጠላቶቻቸው ጋራ በአደባባይ በሚሟገቱበት ጊዜ፣ አይዋረዱም።
ብፁዓን ናቸው፤ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሁሉ፣ በመንገዱም የሚሄዱ፤ የድካምህን ፍሬ ትበላለህ፤ ብፅዕና እና ብልጽግና የአንተ ይሆናሉ። ሚስትህ በቤትህ፣ እንደሚያፈራ ወይን ናት፤ ወንዶች ልጆችህ በማእድህ ዙሪያ፣ እንደ ወይራ ተክል ናቸው። እነሆ፤ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው፣ እንዲህ ይባረካል።
ልጆች ሆይ፤ በጌታ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ፤ ይህ ተገቢ ነውና። በተረፈ በጌታና ብርቱ በሆነው ኀይሉ ጠንክሩ። የዲያብሎስን የተንኰል ሥራ መቋቋም ትችሉ ዘንድ፣ የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ዕቃ ልበሱ። ምክንያቱም ተጋድሏችን ከሥጋና ከደም ጋራ ሳይሆን ከዚህ ከጨለማ ዓለም ገዦች፣ ከሥልጣናትና ከኀይላት እንዲሁም በሰማያዊ ስፍራ ካሉ ከርኩሳን መናፍስት ሰራዊት ጋራ ነው። ክፉው ቀን ሲመጣ መቋቋም ትችሉ ዘንድ የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ዕቃ ልበሱ፤ ሁሉን ከፈጸማችሁ በኋላ ጸንታችሁ መቆም ትችላላችሁና። እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ዝናር ታጥቃችሁ፣ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ፣ በሰላም ወንጌል ዝግጁነት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ። ከእነዚህም ሁሉ ጋራ፣ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤ የመዳንን ራስ ቍር አድርጉ፤ የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ፤ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው። በሁሉ ዐይነት ጸሎትና ልመና፣ በማንኛውም ሁኔታ በመንፈስ ጸልዩ፤ ይህንም በማሰብ ንቁ፤ ስለ ቅዱሳንም ሁሉ በትጋት ልመና አቅርቡ። የወንጌልን ምስጢር ለመግለጥ አፌን በምከፍትበት ጊዜ ሁሉ በድፍረት እንድናገር ቃል ይሰጠኝ ዘንድ ጸልዩልኝ። “አባትህንና እናትህን አክብር” በሚለው ቀዳሚ ትእዛዝ ውስጥ ያለው ተስፋ፣ በሰንሰለት የታሰረ መልእክተኛ የሆንሁት ለዚሁ ነውና። ስለዚህ መናገር የሚገባኝን ያለ ፍርሀት እንድናገር ጸልዩልኝ። በምን ሁኔታ እንዳለሁና ምን እንደማደርግ ታውቁ ዘንድ ተወዳጅ ወንድምና በጌታ ታማኝ አገልጋይ የሆነው ቲኪቆስ ሁሉንም ነገር ይነግራችኋል። የእኛን ሁኔታ እንድታውቁና ልባችሁን እንዲያበረታ ለዚሁ ስል ወደ እናንተ እልከዋለሁ። ከእግዚአብሔር አብ፣ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም፣ ፍቅርም ከእምነት ጋራ ለወንድሞች ይሁን። ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወድዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን። “መልካም እንዲሆንልህ፣ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም” የሚል ነው።
አንዲት መበለት ግን ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ቢኖሯት፣ እነዚህ ልጆች የራሳቸውን ቤተ ሰብ በመርዳትና ለወላጆቻቸውም ብድራትን በመመለስ ከሁሉ በፊት እምነታቸውን በተግባር ለማሳየት መማር ይገባቸዋል፤ ይህ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነውና።
ሃሌ ሉያ። ብፁዕ ነው፤ እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ በትእዛዙም እጅግ ደስ የሚሰኝ፤ ክፉ ሰው ይህን በማየት ይበሳጫል፤ ጥርሱን ያፋጫል፤ እየመነመነም ይጠፋል፤ የክፉዎችም ምኞት ትጠፋለች። ዘሩ በምድር ላይ ኀያል ይሆናል፤ የቅኖች ትውልድ ትባረካለች።
ዛሬ የምሰጥህን እነዚህን ትእዛዞች በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስጠናቸው፤ በቤትህ ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛና ስትነሣም ስለ እነርሱ ተናገር።
እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳለ፣ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታን መስጠት ካወቃችሁበት፣ የሰማዩ አባታችሁ ታዲያ ለሚለምኑት መልካም ስጦታን እንዴት አብልጦ አይሰጥ?
ለደከመው ብርታት ይሰጣል፤ ለዛለው ጕልበት ይጨምራል። የዐዋጅ ነጋሪ ድምፅ እንዲህ ይላል፤ “በምድረ በዳ የጌታን መንገድ፣ አዘጋጁ፤ ለአምላካችን አውራ ጐዳና፣ በበረሓ አስተካክሉ። ወጣቶች እንኳ ይደክማሉ፤ ይታክታሉም፤ ጐበዛዝትም ተሰናክለው ይወድቃሉ። እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን፣ ኀይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፤ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፤ አይደክሙም።
ጕልማሳ ነበርሁ፤ አሁን አርጅቻለሁ፤ ነገር ግን ጻድቅ ሲጣል፣ ዘሩም እንጀራ ሲለምን አላየሁም። ሁልጊዜ ቸር ነው፤ ያበድራልም፤ ልጆቹም የተባረኩ ይሆናሉ።
እርስ በርሳችንም ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንዴት እንደምንነቃቃ እናስብ። አንዳንዶች ማድረጉን እንደተዉት መሰብሰባችንን አንተው፤ ይልቁንም ቀኑ እየተቃረበ መምጣቱን ስታዩ እርስ በርሳችን እንበረታታ።
ሌሎች ከእናንተ እንደሚሻሉ በትሕትና ቍጠሩ እንጂ፣ በራስ ወዳድነት ምኞት ወይም ከንቱ ውዳሴ ለማግኘት አንዳች አታድርጉ። እርሱም እናንተ ልትሰጡኝ ያልቻላችሁትን አገልግሎት ለማሟላት ሲል ለሕይወቱ እንኳ ሳይሣሣ፣ ለክርስቶስ ሥራ ከሞት አፋፍ ደርሶ ነበርና። እያንዳንዳችሁ ሌሎችን የሚጠቅመውንም እንጂ፣ ራሳችሁን የሚጠቅመውን ብቻ አትመልከቱ።
የርኅራኄ አባት፣ የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። እኛ ራሳችን ከእግዚአብሔር በተቀበልነው መጽናናት፣ በመከራ ያሉትን ማጽናናት እንድንችል፣ እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል።
“እናንተ ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ በልቤ የዋህና ትሑት ነኝና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ “ይመጣል ተብሎ የሚጠበቀው አንተ ነህ? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ሲል ጠየቀ። ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነውና።”
እግዚአብሔር ሆይ፤ ጩኸቴን ስማ፤ ጸሎቴንም አድምጥ። ልቤ በዛለ ጊዜ፣ ከምድር ዳርቻ ወደ አንተ እጣራለሁ፤ ከእኔ ይልቅ ከፍ ወዳለው ዐለት ምራኝ። አንተ መጠጊያዬ፣ ከጠላትም የምተገንብህ ጽኑ ግንብ ሆነኸኛልና።
የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ታማኝነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት ነው። እንደነዚህ ያሉትንም የሚከለክል ሕግ የለም።
እናንተን ባስታወስሁ ቍጥር አምላኬን አመሰግናለሁ። ቀድሞ እንዳያችሁትና አሁንም በእኔ እንዳለ በምትሰሙት በዚያው ዐይነት ተጋድሎ እናንተም እያለፋችሁ ነውና። ሁልጊዜ ስለ ሁላችሁ ስጸልይ፣ በደስታ እጸልያለሁ፤ ከመጀመሪያው ቀን አንሥቶ እስካሁን ድረስ በወንጌል አገልግሎት ተካፋይ ሆናችኋልና።
ብፁዕ ነው፣ በክፉዎች ምክር የማይሄድ፣ በኀጢአተኞች መንገድ የማይቆም፣ በፌዘኞችም ወንበር የማይቀመጥ፤ ነገር ግን ደስ የሚሠኘው በእግዚአብሔር ሕግ ነው፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያሰላስለዋል። እርሱም በወራጅ ውሃ ዳር እንደ ተተከለች፣ ፍሬዋን በየወቅቱ እንደምትሰጥ፣ ቅጠሏም እንደማይጠወልግ ዛፍ ነው፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።
ልጄ ሆይ፤ ትምህርቴን አትርሳ፤ ትእዛዞቼን በልብህ ጠብቅ፤ ይህን ብታደርግ፣ ጐተራህ ሞልቶ ይትረፈረፋል፤ መጥመቂያህም በአዲስ የወይን ጠጅ ቲፍ ብሎ ይሞላል። ልጄ ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ተግሣጽ አትናቅ፤ በዘለፋውም አትመረር፤ አባት ደስ የሚሰኝበትን ልጁን እንደሚቀጣ ሁሉ፣ እግዚአብሔርም የሚወድደውን ይገሥጻልና። ብፁዕ ነው፤ ጥበብን የሚያገኛት፣ ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርጋት ሰው፤ እርሷ ከብር ይልቅ ትርፍ የምታመጣ፣ ከወርቅም ይልቅ ጥቅም የምታስገኝ ናትና። ከቀይ ዕንቍ ይበልጥ ውድ ናት፤ አንተ ከምትመኘውም ሁሉ የሚስተካከላት የለም። በቀኝ እጇ ረዥም ዕድሜ አለ፤ በግራ እጇም ሀብትና ክብር ይዛለች። መንገዷ ደስ የሚያሰኝ ነው፤ ጐዳናዋም ሁሉ ሰላም ነው። ለሚያቅፏት የሕይወት ዛፍ ናት፤ የሚይዟትም ይባረካሉ። እግዚአብሔር በጥበብ ምድርን መሠረተ፤ በማስተዋል ሰማያትን በየስፍራቸው አጸና፤ ቀኖችን ይጨምሩልሃል፤ ዓመቶችንም ያረዝሙልሃል፤ ሕይወት፣ ሀብትንና ሰላምን ያበዙልሃል።
ቤት በጥበብ ይሠራል፤ በማስተዋልም ይጸናል፤ በሰነፍ ሰው ዕርሻ በኩል ዐለፍሁ፤ በልበ ቢስ ሰው የወይን ቦታ ዐልፌ ሄድሁ፤ በያለበት እሾኽ በቅሎበታል፤ መሬቱም ዐረም ለብሷል፤ ቅጥሩም ፈራርሷል። ያየሁትን ነገር አወጣሁ፣ አወረድሁ፤ ካስተዋልሁትም ትምህርት አገኘሁ፤ ጥቂት ማንቀላፋት፤ ጥቂት ማንጐላጀት፤ እጅን አጣጥፎ ጥቂት ጋደም ማለት፤ ድኽነት እንደ ወንበዴ፣ ዕጦትም መሣሪያ እንደ ታጠቀ ሰው ይመጣብሃል። በዕውቀትም ውድና ውብ በሆነ ንብረት፣ ክፍሎቹ ይሞላሉ።
እግዚአብሔር ሁልጊዜ ይመራሃል፤ ፀሓይ ባቃጠለው ምድር ፍላጎትህን ያሟላል፤ ዐጥንትህን ያበረታል፤ በውሃ እንደ ረካ የአትክልት ቦታ፣ እንደማይቋርጥም ምንጭ ትሆናለህ።
በመጨረሻም ወንድሞች ሆይ፤ እውነት የሆነውን ሁሉ፣ ክቡር የሆነውን ሁሉ፣ ትክክል የሆነውን ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ሁሉ፣ ተወዳጅ የሆነውን ሁሉ፣ መልካም የሆነውን ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን ወይም ምስጋና እንደ እነዚህ ስላሉት ነገሮች አስቡ።
በጸሎቴ እያስታወስኋችሁ ስለ እናንተ ምስጋና ማቅረብን አላቋረጥሁም። የክብር አባት የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክ ይበልጥ እንድታውቁት፣ የጥበብና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ ያለ ማቋረጥ እለምናለሁ። እንዲሁም በርሱ የተጠራችሁለት ተስፋ፣ ይህም በቅዱሳኑ ዘንድ ያለውን ክቡር የሆነውን የርስቱን ባለጠግነት ምን እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ የልባችሁ ዐይኖች እንዲበሩ
እግዚአብሔርን ደጅ ጠናሁት፤ እርሱም ዘንበል አለልኝ፤ ጩኸቴንም ሰማ። ጽድቅህን በልቤ አልሸሸግሁም፤ ታማኝነትህንና ማዳንህን እናገራለሁ፤ ምሕረትህንና እውነትህን፣ ከታላቅ ጉባኤ አልደበቅሁም። እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህን አትንፈገኝ፤ ቸርነትህና እውነትህ ዘወትር ይጠብቁኝ፤ ስፍር ቍጥር የሌለው ክፋት ከብቦኛልና፤ የኀጢአቴ ብዛት ስለ ያዘኝ ማየት ተስኖኛል፤ ከራሴ ጠጕር ይልቅ በዝቷል፤ ልቤም ከድቶኛል። እግዚአብሔር ሆይ፤ ታድነኝ ዘንድ ፈቃድህ ይሁን፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔን ለመርዳት ፍጠን። ነፍሴን ለመንጠቅ የሚፈልጉ ይፈሩ፤ ይዋረዱም፤ ጕዳቴንም የሚሹ፣ ተዋርደው በመጡበት ይመለሱ። በእኔ ላይ፣ “ዕሠይ! ዕሠይ!” የሚሉ፣ በራሳቸው ዕፍረት ይደንግጡ። አንተን የሚፈልጉ ሁሉ ግን፣ ሐሤት ያድርጉ፤ በአንተም ደስ ይበላቸው፤ ዘወትር የአንተን ማዳን የሚወድዱ፣ “እግዚአብሔር ከፍ ከፍ ይበል!” ይበሉ። እኔ ግን ችግረኛና ድኻ ነኝ፤ ጌታ ግን ያስብልኛል። አንተ ረዳቴና ታዳጊዬም ነህና፤ አምላኬ ሆይ፤ አትዘግይ። ከሚውጥ ጕድጓድ፣ ከሚያዘቅጥ ማጥ አወጣኝ፤ እግሮቼን በዐለት ላይ አቆመ፤ አካሄዴንም አጸና።
ፍቅር ታጋሽ ነው፤ ደግሞም ቸር ነው። ፍቅር አይመቀኝም፤ አይመካም፤ አይታበይም፤ ተገቢ ያልሆነ ነገር አያደርግም፤ ራስ ወዳድ አይደለም፤ አይበሳጭም፤ በደልን አይቈጥርም። ፍቅር ከእውነት ጋራ እንጂ በዐመፅ ደስ አይሰኝም። ፍቅር ሁልጊዜ ይታገሣል፤ ሁልጊዜ ያምናል፤ ሁልጊዜ ተስፋ ያደርጋል፤ ሁልጊዜ ጸንቶ ይቆማል።
ማድረግ እየቻልህ ለሚገባቸው መልካም ነገር ከማድረግ አትቈጠብ። አሁን በእጅህ እያለ፣ ጎረቤትህን፣ “ቈይተህ ተመለስ፤ ነገ እሰጥሃለሁ” አትበለው።
እግዚአብሔር ሆይ፤ አካሄድህን እንዳውቅ አድርገኝ፤ መንገድህንም አስተምረኝ። አንተ አዳኜ፣ አምላኬም ነህና፣ በእውነትህ ምራኝ፤ አስተምረኝም፤ ቀኑን ሙሉ አንተን ተስፋ አድርጌአለሁ።
በዚህ ብቻ ሳይሆን በመከራችንም ሐሤት እናደርጋለን፤ ምክንያቱም መከራ ትዕግሥትን እንደሚያስገኝ እናውቃለን። ትዕግሥት ጽናትን፣ ጽናት የተፈተነ ባሕርይን፣ የተፈተነ ባሕርይ ተስፋን፤
ማንኛውንም ነገር ሳታጕረመርሙና ሳትከራከሩ አድርጉ፤ ይኸውም በጠማማና በክፉ ትውልድ መካከል ንጹሓንና ያለ ነቀፋ፣ ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች ሆናችሁ፣ እንደ ከዋክብት በዓለም ሁሉ ታበሩ ዘንድ ነው።
በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው። ከእግዚአብሔር ቤት ባረክናችሁ። እግዚአብሔር አምላክ ነው፤ ብርሃኑንም በላያችን አበራ፤ እስከ መሠዊያው ቀንዶች ድረስ በመውጣት፣ ዝንጣፊ ይዛችሁ በዓሉን ከሚያከብሩት ጋራ ተቀላቀሉ።