በየቀኑ የእግዚአብሔርን ምሕረት በአዲስ መልክ እናያለን። በእርሱ ፍቅር ብቻ እንጂ በራሳችን ጥበብ ሕያዋን አይደለንም። ለዚህ አዲስ ቀን እግዚአብሔርን እናመስግን፤ በእርሱ ታማኝነትም እንታመን።
ቀኑን ስንጀምር እግዚአብሔርን ማስቀደምና በቃሉ መጽናት በጣም አስፈላጊ ነው። ቃሉ በማንኛውም ፈተና ውስጥ እንድንጸና ያደርገናል።
ብዙ ጊዜ ከእንቅልፋችን ለመነሳት እንቸገራለን። ምናልባት የሚመጣብንን ፈተና ስለማናውቅ ወይም ያሉብንን ችግሮች እንዴት እንደምንፈታቸው ስለማናውቅ ይሆናል። ግን የእግዚአብሔር ጸጋና ሞገስ በየቀኑ ስለሚታደስ ሁሉንም ነገር ማሸነፍ እንችላለን።
ጠዋት ስንነሳ ያሉንን መልካም ነገሮች በማሰብ እንጀምር። ይህን ስናደርግ ለሚመጡብን ፈተናዎች ያለን አመለካከት ይለወጣል። "እግዚአብሔር ይመስገን" እያልን እንጀምር።
እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ግን ዙሪያዬን የምትከልል ጋሻ ነህ፤ ክብሬንና ራሴንም ቀና ቀና የምታደርግ አንተ ነህ። ወደ እግዚአብሔር ድምፄን ከፍ አድርጌ እጮኻለሁ፤ እርሱም ከተቀደሰ ተራራው ይመልስልኛል። ሴላ እተኛለሁ፤ አንቀላፋለሁ፤ እግዚአብሔር ደግፎ ይዞኛልና እነቃለሁ። በየአቅጣጫው የከበበኝን፣ አእላፍ ሕዝብ አልፈራም።
ብፁዕ ነው፣ በክፉዎች ምክር የማይሄድ፣ በኀጢአተኞች መንገድ የማይቆም፣ በፌዘኞችም ወንበር የማይቀመጥ፤ ነገር ግን ደስ የሚሠኘው በእግዚአብሔር ሕግ ነው፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያሰላስለዋል። እርሱም በወራጅ ውሃ ዳር እንደ ተተከለች፣ ፍሬዋን በየወቅቱ እንደምትሰጥ፣ ቅጠሏም እንደማይጠወልግ ዛፍ ነው፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።
ነህምያም፣ “ሂዱ፤ ጥሩ ምግብ በመብላት፣ ጣፋጩን በመጠጣት ደስ ይበላችሁ፤ ምንም የተዘጋጀ ነገር ለሌላቸውም ካላችሁ ላይ ከፍላችሁ ላኩላቸው። ይህች ቀን ለጌታችን የተቀደሰች ናት፤ የእግዚአብሔር ደስታ ብርታታችሁ ስለ ሆነ አትዘኑ” አላቸው።
ማጣትን ዐውቀዋለሁ፤ ማግኘትንም ዐውቀዋለሁ። ብጠግብም ሆነ ብራብ፣ ባገኝም ሆነ ባጣ፣ በማንኛውም ሆነ በየትኛውም ሁኔታ ያለኝ ይበቃኛል የማለትን ምስጢር ተምሬአለሁ። ኀይልን በሚሰጠኝ በርሱ ሁሉን ማድረግ እችላለሁ።
አምላክ ሆይ፤ ለእኔ ያለህ ሐሳብ እንዴት ክቡር ነው! ቍጥሩስ ምንኛ ብዙ ነው! ልቍጠራቸው ብል፣ ከአሸዋ ይልቅ ይበዙ ነበር። ተኛሁም ነቃሁም፣ ገና ከአንተው ጋራ ነኝ።
ምክንያቱም፣ እግዚአብሔር አስቀድሞ እንድንመላለስባቸው ያዘጋጀልንን መልካም የሆኑትን ሥራዎች እንድንሠራ በክርስቶስ ኢየሱስ የተፈጠርን የእግዚአብሔር እጅ ሥራዎች ነን።
በልዑል መጠጊያ የሚኖር፣ በሁሉን ቻይ አምላክ ጥላ ሥር ያድራል። ክፉ ነገር አያገኝህም፤ መቅሠፍትም ወደ ድንኳንህ አይገባም፤ በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ፣ እግርህም ከድንጋይ ጋራ እንዳይሰናከል፤ በእጆቻቸው ያነሡህ ዘንድ፣ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዝልሃል። በአንበሳና በእፉኝት ላይ ትጫማለህ፤ ደቦሉን አንበሳና ዘንዶውን ትረግጣለህ። “ወድዶኛልና እታደገዋለሁ፤ ስሜን ዐውቋልና እከልለዋለሁ። ይጠራኛል፤ እመልስለታለሁ፤ በመከራው ጊዜ ከርሱ ጋራ እሆናለሁ፤ አድነዋለሁ፤ አከብረዋለሁ። ረዥም ዕድሜን አጠግበዋለሁ፤ ማዳኔንም አሳየዋለሁ።” እግዚአብሔርን፣ “መጠጊያዬ፣ ምሽጌ፣ የምታመንብህ አምላኬ” እለዋለሁ።
“እናንተ ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ በልቤ የዋህና ትሑት ነኝና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ “ይመጣል ተብሎ የሚጠበቀው አንተ ነህ? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ሲል ጠየቀ። ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነውና።”
እርስ በርሳችንም ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንዴት እንደምንነቃቃ እናስብ። አንዳንዶች ማድረጉን እንደተዉት መሰብሰባችንን አንተው፤ ይልቁንም ቀኑ እየተቃረበ መምጣቱን ስታዩ እርስ በርሳችን እንበረታታ።
በውሃ ውስጥ በምታልፍበት ጊዜ፣ ከአንተ ጋራ እሆናለሁ፤ ወንዙን ስትሻገረው፣ አያሰጥምህም፤ በእሳት ውስጥ ስትሄድ፣ አያቃጥልህም፤ ነበልባሉም አይፈጅህም።
እግዚአብሔር ከእኔ ጋራ ነው፤ አልፈራም፤ ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል? ይረዳኝ ዘንድ እግዚአብሔር ከእኔ ጋራ ነው፤ የጠላቶቼንም ውድቀት አያለሁ።
እግዚአብሔርን ደጅ ጠናሁት፤ እርሱም ዘንበል አለልኝ፤ ጩኸቴንም ሰማ። ጽድቅህን በልቤ አልሸሸግሁም፤ ታማኝነትህንና ማዳንህን እናገራለሁ፤ ምሕረትህንና እውነትህን፣ ከታላቅ ጉባኤ አልደበቅሁም። እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህን አትንፈገኝ፤ ቸርነትህና እውነትህ ዘወትር ይጠብቁኝ፤ ስፍር ቍጥር የሌለው ክፋት ከብቦኛልና፤ የኀጢአቴ ብዛት ስለ ያዘኝ ማየት ተስኖኛል፤ ከራሴ ጠጕር ይልቅ በዝቷል፤ ልቤም ከድቶኛል። እግዚአብሔር ሆይ፤ ታድነኝ ዘንድ ፈቃድህ ይሁን፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔን ለመርዳት ፍጠን። ነፍሴን ለመንጠቅ የሚፈልጉ ይፈሩ፤ ይዋረዱም፤ ጕዳቴንም የሚሹ፣ ተዋርደው በመጡበት ይመለሱ። በእኔ ላይ፣ “ዕሠይ! ዕሠይ!” የሚሉ፣ በራሳቸው ዕፍረት ይደንግጡ። አንተን የሚፈልጉ ሁሉ ግን፣ ሐሤት ያድርጉ፤ በአንተም ደስ ይበላቸው፤ ዘወትር የአንተን ማዳን የሚወድዱ፣ “እግዚአብሔር ከፍ ከፍ ይበል!” ይበሉ። እኔ ግን ችግረኛና ድኻ ነኝ፤ ጌታ ግን ያስብልኛል። አንተ ረዳቴና ታዳጊዬም ነህና፤ አምላኬ ሆይ፤ አትዘግይ። ከሚውጥ ጕድጓድ፣ ከሚያዘቅጥ ማጥ አወጣኝ፤ እግሮቼን በዐለት ላይ አቆመ፤ አካሄዴንም አጸና። ለአምላካችን የሚሆን ውዳሴ፣ አዲስ ዝማሬን በአፌ ላይ አኖረ፤ ብዙዎች ያያሉ፤ ይፈራሉም፤ በእግዚአብሔር ይታመናሉ።
እግዚአብሔር አምላክ ፀሓይና ጋሻ ነውና፤ እግዚአብሔር ሞገስንና ክብርን ይሰጣል፤ እግዚአብሔር ያለ ነቀፋ የሚሄዱትን፣ መልካም ነገር አይነፍጋቸውም።
እግዚአብሔር ሁልጊዜ ይመራሃል፤ ፀሓይ ባቃጠለው ምድር ፍላጎትህን ያሟላል፤ ዐጥንትህን ያበረታል፤ በውሃ እንደ ረካ የአትክልት ቦታ፣ እንደማይቋርጥም ምንጭ ትሆናለህ።
የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ታማኝነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት ነው። እንደነዚህ ያሉትንም የሚከለክል ሕግ የለም።
“ስለዚህ እላችኋለሁ፣ ስለ ኑሯችሁ ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? በማለት አትጨነቁ። ሕይወት ከምግብ፣ ሰውነትስ ከልብስ አይበልጥምን? እስኪ የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱም፤ በጐተራም አያከማቹም፤ ይሁን እንጂ የሰማዩ አባታችሁ ይመግባቸዋል። እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን? ለመሆኑ፣ ከእናንተ መካከል ተጨንቆ በዕድሜው ላይ አንድ ሰዓት መጨመር የሚችል ማን ነው?
እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፤ አንዳች አይጐድልብኝም። በለመለመ መስክ ያሳርፈኛል፤ በዕረፍት ውሃ ዘንድ ይመራኛል፤ ነፍሴንም ይመልሳታል። ስለ ስሙም፣ በጽድቅ መንገድ ይመራኛል።
እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ሰውነታችሁን ቅዱስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕያው መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፤ ይህም እንደ ባለ አእምሮ የምታቀርቡት አምልኳችሁ ነው።
ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፤ ጸንታችሁ ቁሙ፤ በምንም ነገር አትናወጡ። ለጌታ ሥራ ዘወትር የምትተጉ ሁኑ፤ ምክንያቱም ለጌታ የምትደክሙት በከንቱ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ።
ማንኛውንም ነገር ሳታጕረመርሙና ሳትከራከሩ አድርጉ፤ ይኸውም በጠማማና በክፉ ትውልድ መካከል ንጹሓንና ያለ ነቀፋ፣ ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች ሆናችሁ፣ እንደ ከዋክብት በዓለም ሁሉ ታበሩ ዘንድ ነው።
እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔ ግን በአንተ እታመናለሁ፤ “አንተ አምላኬ ነህ” እልሃለሁም። ዘመኔ ያለው በእጅህ ነው፤ ከጠላቶቼ እጅ ታደገኝ፤ ከሚያሳድዱኝም አድነኝ።
በአንተ ላይ ታምናለችና፣ በአንተ የምትደገፈውን ነፍስ ፈጽመህ በሰላም ትጠብቃታለህ። በእግዚአብሔር ለዘላለም ታመኑ፤ ጌታ እግዚአብሔር የዘላለም ዐለት ነውና።
እርሱ ግን፣ “ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ኀይሌ ፍጹም የሚሆነው በድካም ጊዜ ነውና” አለኝ። ስለዚህ የክርስቶስ ኀይል በእኔ ያድር ዘንድ፣ ይበልጥ ደስ እያለኝ በድካሜ እመካለሁ።
እግዚአብሔር ከክፉ ሁሉ ይጠብቅሃል፤ ነፍስህንም ይንከባከባታል። እግዚአብሔር ከአሁን ጀምሮ እስከ ዘላለም፣ መውጣትህንና መግባትህን ይጠብቃል።
እኛ ለእናንተ ፍቅር እንዳለን ሁሉ እርስ በርስ ያላችሁን ፍቅርና ለሌሎችም ያላችሁን ፍቅር ጌታ ያብዛላችሁ፤ ያትረፍርፍላችሁም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋራ በሚመጣበት ጊዜ በአምላካችንና በአባታችን ፊት ነቀፋ የሌለባችሁና ቅዱሳን ሆናችሁ እንድትገኙ ልባችሁን ያጽና።
አምላክ ሆይ፤ ልቤ ጽኑ ነው፤ እቀኛለሁ፤ በፍጹም ነፍሴም እዘምራለሁ። ወደ ተመሸገችው ከተማ ማን ይወስደኛል? ወደ ኤዶምያስ ማን ይመራኛል? እግዚአብሔር ሆይ፤ የጣልኸን አንተ አይደለህምን? አምላክ ሆይ፤ ከሰራዊታችንም ጋራ አትወጣም። በጠላት ላይ ድልን አቀዳጀን፤ የሰው ርዳታ ከንቱ ነውና። በእግዚአብሔር ክንደ ብርቱ እንሆናለን፤ ጠላቶቻችንን የሚረጋግጥልን እርሱ ነውና። በገናና መሰንቆም ተነሡ፤ እኔም ማልጄ እነሣለሁ።