ሕይወት በውል የማናውቃቸው ነገሮች የተሞላች ናት። የዛሬን ሁሉንም ነገር በእርግጠኝነት ማወቅ አንችልም፤ የነገን ደግሞ እንዲያውም እንጃ። ግን እኛን እጅግ በሚወደው እና ለማዳናችን የአንድያ ልጁን ሕይወት በሰጠው በእግዚአብሔር ተስፋዎች ላይ መጣበቅ አለብን። እርሱ በሰማይ ስፍራ ያዘጋጅልናል፤ ማንም ወይም ምንም ከፍቅሩ ሊለየን አይችልም። (መዝሙር ፸፩፥፭) "አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ተስፋዬ ነህ፥ ከሕፃንነቴም ጀምሮ መታመኛዬ ነህ።"
በውል የማናውቃቸው ነገሮች በተሞሉበት በዚህ ዓለም፣ እኛ ክርስቲያኖች ተስፋችንን በእግዚአብሔር ላይ እናደርጋለን፤ በማይናወጠው ፍቅሩ ላይ እንረፍባለን። ማዕበሉ ሕይወታችንን ቢያናውጠውም፣ ኢየሱስ ስለሚረዳን በማዕበሉ ውስጥ እንደማንሰጥም እርግጠኞች መሆን እንችላለን።
በየቀኑ በችግሮች እንዳንወድቅ እምነታችንን እንዲያጸናልን መንፈስ ቅዱስን እንለምናለን። ኢየሱስ ሁሉንም ነገር ድል እንዳደረገ እና በስሙ ከድል በላይ እንደሆንን እንድንረዳ እንለምናለን። አስቸጋሪ ጊዜያት እንደሚገጥሙን እውነት ቢሆንም፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ለመፅናት እና ለመቀጠል ብርታት እንደሚሰጠንም እውነት ነው። አሜን!
ፍርሀት በሚይዘኝ ጊዜ፣ መታመኔን በአንተ ላይ አደርጋለሁ። ቃሉን በማመሰግነው አምላክ፣ በእግዚአብሔር ታምኛለሁ፤ አልፈራም፤ ሥጋ ለባሽ ምን ሊያደርገኝ ይችላል?
አምላካችን መጠጊያችንና ኀይላችን፣ በሚደርስብን መከራ ሁሉ የቅርብ ረዳታችን ነው። “ዕረፉ፤ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ ዕወቁ፤ በሕዝቦች ዘንድ ከፍ ከፍ እላለሁ፤ በምድርም ላይ ከፍ ከፍ እላለሁ።” የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ ነው፤ የያዕቆብም አምላክ መጠጊያችን ነው። ሴላ ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ እንኳ፣ ተራሮችም ወደ ባሕር ጥልቅ ቢሰምጡ አንፈራም።
ይህን ተረድቻለሁ፤ ሞትም ይሁን ሕይወት፣ መላእክትም ይሁኑ አጋንንት፣ ያለውም ይሁን የሚመጣው፣ ወይም ማንኛውም ኀይል፣ ከፍታም ይሁን ጥልቀት ወይም የትኛውም ፍጥረት፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ካለው ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን አይችልም።
እኔ ግን ወደ እግዚአብሔር እጣራለሁ፤ እግዚአብሔርም ያድነኛል። በማታ፣ በጧትና በቀትር፣ እጮኻለሁ፤ እቃትታለሁም፤ እርሱም ድምፄን ይሰማል። በተቃውሞ የተነሡብኝ ብዙዎች ናቸውና፣ ከተቃጣብኝ ጦርነት፣ ነፍሴን በሰላም ይቤዣታል።
ነፍሴ ሆይ፤ ዐርፈሽ እግዚአብሔርን ብቻ ጠብቂ፤ ተስፋዬ ከርሱ ዘንድ ነውና። ዐለቴና መድኀኒቴ እርሱ ብቻ ነው፤ መጠጊያዬም እርሱ ነው፤ እኔም አልናወጥም።
ነፍሴ ከዐፈር ተጣበቀች፤ እንደ ቃልህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ። ስለ መንገዴ ገልጬ ነገርሁህ፤ አንተም መለስህልኝ፤ ሥርዐትህን አስተምረኝ።
የሚመክረኝን እግዚአብሔርን እባርካለሁ፤ በሌሊት እንኳ ልቤ ቀናውን ያመላክተኛል። እግዚአብሔርን ሁልጊዜ በፊቴ አድርጌአለሁ፤ እርሱ በቀኜ ስላለ አልናወጥም።
በውሃ ውስጥ በምታልፍበት ጊዜ፣ ከአንተ ጋራ እሆናለሁ፤ ወንዙን ስትሻገረው፣ አያሰጥምህም፤ በእሳት ውስጥ ስትሄድ፣ አያቃጥልህም፤ ነበልባሉም አይፈጅህም።
ለእናንተ ያለኝን ዕቅድ እኔ ዐውቃለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ዕቅዱም ፍጻሜው ያማረና ተስፋ የሚሰጣችሁ፣ የሰላም ሐሳብ እንጂ ለክፉ አይደለም።
በዚህ ብቻ ሳይሆን በመከራችንም ሐሤት እናደርጋለን፤ ምክንያቱም መከራ ትዕግሥትን እንደሚያስገኝ እናውቃለን። ትዕግሥት ጽናትን፣ ጽናት የተፈተነ ባሕርይን፣ የተፈተነ ባሕርይ ተስፋን፤ ይህም ተስፋ ለዕፍረት አይዳርገንም፤ እግዚአብሔር በሰጠን በመንፈስ ቅዱስ ፍቅሩን በልባችን አፍስሷልና።
ስለዚህ ተስፋ አንቈርጥም፤ ውጫዊው ሰውነታችን እየጠፋ ቢሄድም እንኳ፣ ውስጣዊው ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል፤ ምክንያቱም ቀላልና ጊዜያዊ የሆነው መከራችን ወደር የማይገኝለት ዘላለማዊ ክብር ያስገኝልናል። ስለዚህ ዐይናችን የሚያተኵረው በሚታየው ነገር ላይ ሳይሆን በማይታየው ላይ ነው፤ የሚታየው ጊዜያዊ ነውና፤ የማይታየው ግን ዘላለማዊ ነው።
ሆኖም ይህን ዐስባለሁ፤ እንግዲያስ ተስፋ አለኝ፤ ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ታላቅ ፍቅር የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና። ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፤ ታማኝነትህም ብዙ ነው።
“እናንተ ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ በልቤ የዋህና ትሑት ነኝና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ “ይመጣል ተብሎ የሚጠበቀው አንተ ነህ? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ሲል ጠየቀ። ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነውና።”
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባትና አምላክ ይባረክ፤ እርሱ ከታላቅ ምሕረቱ የተነሣ በኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት መነሣት ምክንያት ለሕያው ተስፋ በሚሆን አዲስ ልደት፣
በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ፣ ከምስጋናም ጋራ ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ እንጂ ስለ ማንኛውም ነገር አትጨነቁ። ከማስተዋል በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም፣ ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።
ለእነርሱም እግዚአብሔር የዚህ ምስጢር ክብር ባለጠግነት በአሕዛብ መካከል ምን ያህል እንደ ሆነ ለማሳወቅ መረጠ፤ እርሱም የክብር ተስፋ የሆነው በእናንተ ውስጥ ያለው ክርስቶስ ነው።
እንግዲህ በእኛ ውስጥ እንደሚሠራው እንደ ኀይሉ መጠን፣ ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ እጅግ አብልጦ ማድረግ ለሚቻለው፣ በቤተ ክርስቲያን እንዲሁም በክርስቶስ ኢየሱስ፣ በዘመናት ሁሉ ከዘላለም እስከ ዘላለም ለርሱ ክብር ይሁን! አሜን።
የእግዚአብሔርን ቸርነት በሕያዋን ምድር እንደማይ ሙሉ እምነቴ ነው። እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ አይዞህ፣ በርታ፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ።