መንፈስ ቅዱስ ይህ ሁሉ ብቻ ሳይሆን ከዚህም በላይ ነው፡፡ እውነተኛ አጽናኝ፣ ታማኝ ወዳጅ፣ በማዕበል መካከል አስተማማኝ መጠጊያ፣ ፍጹም መሪ፣ የፍጹም ጥበብ ምንጭ እና ማለቂያ የሌለው አብሮኝ ነው፡፡ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲያርግ የሰጠን ታላቅ ስጦታ ነው፡፡ ያለ ቅድመ ሁኔታ መውደድ፣ ወሰን የሌለው ደግነትና ርኅራኄ ማሳየት፡፡ ይህ ነው መንፈስ ቅዱስ፡፡ ከእርሱ ጋር ያለን ግንኙነት በሕይወታችን እጅግ አስፈላጊ ነው፣ ምክንያቱም ስለ እግዚአብሔር የምናውቀው በእርሱ በኩል ነው፡፡
መንፈስ ቅዱስ ወደ እውነት ሁሉ ይመራናል፣ የወደፊት ሕይወታችንንም በግልጽ ያሳየናል፡፡ ፈጽሞ አይሳሳትም አያታልልምም፤ ስለዚህ የእርሱን ውብ መገኘት መጠበቅና ማክበር አለብን፡፡ በዓመፅ ያዝናል፣ ክፉ ስናደርግም ያዝናል፤ ነገር ግን ከልባችን ንስሐ ከገባን ሁልጊዜ ከጎናችን ይሆናል፡፡ ከሥጋ ሥራዎች በመራቅ የእርሱን ፍቅር እናሳያለን፡፡
መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ቃል የሚጠብቁትን ይወዳል፣ ስሙን የሚሰድቡትን ግን አይምራቸውም፡፡ የሚፈልገው የሚያጠፉትንና የሚያዝዙትን ቤተ ክርስቲያን አይደለም፣ ነገር ግን የሚወዱትንና ፈቃዱን የሚያደርጉትን ሕዝቦች ነው፡፡ በዚህ ዘመን፣ መገኘቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ በሚናፍቁትና በሚጠብቁት ላይ ይታያል፡፡ በእርሱ ከተያያዝን፣ አንጠፋም አንሳለቅበትም፣ ምክንያቱም ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን፣ ወደ አብ የሚያደርሰውን መንገድ ሊያሳየን የሚችለው እርሱ ብቻ ነው፡፡ ለቤዛ ቀን በእርሱ የታተምንበትን የእግዚአብሔርን መንፈስ ቅዱስ አናሳዝነው፡፡
እኔ አብን እለምናለሁ፤ እርሱም ከእናንተ ጋራ ለዘላለም የሚኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ እርሱም የእውነት መንፈስ ነው፤ ዓለም ስለማያየውና ስለማያውቀው ሊቀበለው አይችልም። እናንተ ግን፣ ዐብሯችሁ ስለሚኖርና በውስጣችሁ ስለሚሆን ታውቁታላችሁ።
የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል። እርሱ ከራሱ አይናገርም፤ የሚሰማውን ብቻ ይናገራል፤ እንዲሁም ወደ ፊት ስለሚሆነው ይነግራችኋል፤
እናንተ ግን፣ የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጣችሁ የሚኖር ከሆነ፣ በሥጋ ሳይሆን በመንፈስ ናችሁ። ማንም የክርስቶስ መንፈስ ከሌለው፣ እርሱ የክርስቶስ አይደለም።
ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው፤ “ንስሓ ግቡ፤ ኀጢአታችሁም እንዲሰረይላችሁ፣ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ።
ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኀይልን ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳና በሰማርያ ሁሉ፣ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ።”
አሁን ከሰማይ በተላከ መንፈስ ቅዱስ ወንጌልን ያበሠሩላችሁ ሰዎች የነገሯችሁን ነገር ባወሩላችሁ ጊዜ፣ እናንተን እንጂ ራሳቸውን እንዳላገለገሉ ተገለጠላቸው። መላእክትም እንኳ ሳይቀሩ እነዚህን ነገሮች ይመኛሉ።
ጴጥሮስ ይህን እየተናገረ ሳለ፣ ቃሉን በሰሙት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው። ከጴጥሮስ ጋራ የመጡት፣ ከተገረዙት ወገን የሆኑት አማኞች፣ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ በአሕዛብም ላይ ደግሞ መፍሰሱን ሲያዩ ተገረሙ። ይኸውም በልሳን ሲናገሩና እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ ስለ ሰሟቸው ነው። በዚያ ጊዜ ጴጥሮስ እንዲህ አለ፤
ማንም ሰው በሰው ልጅ ላይ የሚናገረው ክፉ ቃል ይቅር ይባላል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚናገረው ክፉ ቃል ግን በዚህም ሆነ በወዲያኛው ዓለም ይቅር አይባልም።
“ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀበላችሁን?” አላቸው። እነርሱም፣ “አልተቀበልንም፤ እንዲያውም መንፈስ ቅዱስ መኖሩን እንኳ አልሰማንም” አሉት።
ለመሆኑ፣ ሰውነታችሁ በውስጣችሁ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? ይህም መንፈስ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት ነው። እናንተም የራሳችሁ አይደላችሁም፤
የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድኾች ወንጌልን እንድሰብክ፣ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና። ልባቸው የተሰበረውን እንድጠግን፣ ለምርኮኞች ነጻነትን፣ ለእስረኞች መፈታትን እንዳውጅ ልኮኛል።
ጳውሎስና ባልደረቦቹ ቃሉን በእስያ እንዳይሰብኩ መንፈስ ቅዱስ ስለ ከለከላቸው፣ በፍርግያና በገላትያ አገር ዐልፈው ሄዱ። ወደ ሚስያም በተቃረቡ ጊዜ፣ ወደ ቢታንያ ሊገቡ ሞከሩ፤ ነገር ግን የኢየሱስ መንፈስ አልፈቀደላቸውም።
እናንተ ግን ከርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በውስጣችሁ ይኖራልና ማንም እንዲያስተምራችሁ አያስፈልግም፤ ነገር ግን የርሱ ቅባት ስለ ሁሉም ነገር፣ እውነተኛ የሆነውን እና ሐሰት ያልሆነው እናንተን እንደሚያስተምር፣ እናንተንም እንዳስተማራችሁ በርሱ ኑሩ።
“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በመጨረሻው ቀን፣ መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈስሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤ ጕልማሶቻችሁም ራእይ ያያሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ። በእነዚያ ቀናት በወንዶችና በሴቶች ባሮቼም ላይ፣ መንፈሴን አፈስሳለሁ፤ እነርሱም ትንቢት ይናገራሉ።
እግዚአብሔር ግን ይህን በመንፈሱ አማካይነት ለእኛ ገልጦልናል። መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር እንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራል። በውስጡ ካለው ከራሱ መንፈስ በቀር ከሰው መካከል የአንድን ሰው ሐሳብ የሚያውቅ ማን አለ? እንደዚሁም ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር፣ የእግዚአብሔርን ሐሳብ የሚያውቅ ማንም የለም።
በውሃና በደም የመጣው ይህ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ በውሃና በደም እንጂ በውሃ ብቻ አልመጣም። የሚመሰክረውም መንፈስ ነው፤ መንፈስ እውነት ነውና።
እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስና በኀይል ቀባው፤ እርሱም እግዚአብሔር ከርሱ ጋራ ስለ ነበረ በደረሰበት ሁሉ መልካም እያደረገ በዲያብሎስ ሥልጣን ሥር የነበሩትን ሁሉ ፈወሰ።
የክርስቶስ ቃል በሙላት ይኑርባችሁ፤ እርስ በርሳችሁ በጥበብ ሁሉ ተማማሩ፤ ተመካከሩ፤ በመዝሙርና በማሕሌት፣ በመንፈሳዊም ቅኔ በማመስገን በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ።
አይሁድ ወይም የግሪክ ሰዎች ብንሆን፣ ባሪያ ወይም ነጻ ሰዎች ብንሆን፣ እኛ ሁላችን አንድ አካል እንድንሆን በአንድ መንፈስ ተጠምቀናልና፤ ሁላችንም አንዱን መንፈስ እንድንጠጣ ተሰጥቶናል።
“በእኔ በኩል፣ ከእነርሱ ጋራ የምገባው ኪዳኔ ይህ ነው” ይላል እግዚአብሔር፤ “በአንተም ላይ ያለው መንፈሴ፣ በአፍህ ያኖርሁት ቃሌ ከአፍህ፣ ከልጆችህ አፍ፣ ከዘር ዘሮቻቸውም አፍ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም አይለይም” ይላል እግዚአብሔር።
ይህን ተረድቻለሁ፤ ሞትም ይሁን ሕይወት፣ መላእክትም ይሁኑ አጋንንት፣ ያለውም ይሁን የሚመጣው፣ ወይም ማንኛውም ኀይል፣ ከፍታም ይሁን ጥልቀት ወይም የትኛውም ፍጥረት፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ካለው ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን አይችልም።
ከእነርሱም ጋራ በማእድ ተቀምጦ ሳለ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “ከኢየሩሳሌም አትውጡ፤ ነገር ግን እኔ ስናገር የሰማችሁትን፣ አብ የሰጠውን ተስፋ ጠብቁ፤ ዮሐንስ በውሃ አጥምቆ ነበርና፣ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ።”
መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፤ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑልም ኀይል ይጸልልሻል፤ ስለዚህ የሚወለደው ቅዱሱ ሕፃን፣ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል።
ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የርሱ መንፈስ በእናንተ የሚኖር ከሆነ፣ ክርስቶስን ከሙታን ያስነሣው፣ በውስጣችሁ በሚኖረው በመንፈሱ ሟች ለሆነው ሰውነታችሁ ሕይወትን ይሰጣል።
ሕግ ከሥጋ ባሕርይ የተነሣ ደክሞ ሊፈጽም ያልቻለውን፣ እግዚአብሔር የገዛ ልጁን በኀጢአተኛ ሰው አምሳል፣ የኀጢአት መሥዋዕት እንዲሆን በመላክ ፈጸመው፤ በዚህም ኀጢአትን በሥጋ ኰነነ፤
ከዚያም እንዲህ አለኝ፤ “ለዘሩባቤል የተላከው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፤ ‘በመንፈሴ እንጂ በኀይልና በብርታት አይደለም’ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳለ፣ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታን መስጠት ካወቃችሁበት፣ በሰማይ ያለው አባት ታዲያ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጥ?”
የበዓሉ መጨረሻ በሆነው በታላቁ ቀን፣ ኢየሱስ ቆሞ ከፍ ባለ ድምፅ እንዲህ አለ፤ “ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ፤ በእኔ የሚያምን፣ መጽሐፍ እንዳለ የሕይወት ውሃ ምንጭ ከውስጡ ይፈልቃል።” ይህን ያለው በርሱ የሚያምኑ ስለሚቀበሉት መንፈስ ነበር፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ አልተሰጠም ነበር።
“እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ፣ ከአብ የሚወጣው አጽናኙ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፣ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል። እናንተም ደግሞ፣ ከመጀመሪያው ከእኔ ጋራ ስለ ነበራችሁ፣ ትመሰክራላችሁ።
ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው፤ “ንስሓ ግቡ፤ ኀጢአታችሁም እንዲሰረይላችሁ፣ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ። የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ እንዲሁም ጌታ አምላካችን ወደ ራሱ ለሚጠራቸው፣ በሩቅ ላሉትም ሁሉ ነውና።”
ስለዚህ በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም፤ ነገር ግን ክርስቶስ በውስጣችሁ ካለ፣ ሰውነታችሁ ከኀጢአት የተነሣ የሞተ ቢሆንም፣ መንፈሳችሁ ከጽድቅ የተነሣ ሕያው ነው። ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የርሱ መንፈስ በእናንተ የሚኖር ከሆነ፣ ክርስቶስን ከሙታን ያስነሣው፣ በውስጣችሁ በሚኖረው በመንፈሱ ሟች ለሆነው ሰውነታችሁ ሕይወትን ይሰጣል። ስለዚህ ወንድሞች ሆይ፤ ግዴታ አለብን፤ ይሁን እንጂ እንደ ሥጋ እንድንኖር ለሥጋ አይደለም። እንደ ሥጋ ብትኖሩ ትሞታላችሁና፤ ክፉ የሆነውን የሥጋ ሥራ በመንፈስ ብትገድሉ ግን፣ በሕይወት ትኖራላችሁ። በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና። እንደ ገና የፍርሀት ባሪያ የሚያደርጋችሁን መንፈስ ሳይሆን፣ “አባ፣ አባት” ብለን የምንጠራበትን የልጅነት መንፈስ ተቀብላችኋልና፤ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋራ ሆኖ ይመሰክርልናል። ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ የክብሩ ተካፋዮች እንሆን ዘንድ በርግጥ የመከራው ተካፋዮች ብንሆን፣ የእግዚአብሔር ወራሾች፣ ከክርስቶስ ጋራ ዐብረን ወራሾች ነን። የአሁኑ ዘመን ሥቃያችን ወደ ፊት ሊገለጥ ካለው፣ ለእኛ ከተጠበቀልን ክብር ጋራ ሲነጻጸር ምንም እንዳይደለ እቈጥራለሁ። ፍጥረት ሁሉ የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ በናፍቆት ይጠባበቃል። ምክንያቱም የሕይወት መንፈስ ሕግ በክርስቶስ ኢየሱስ ከኀጢአትና ከሞት ሕግ ነጻ አውጥቷችኋል።
እንዲሁም ደግሞ መንፈስ በድካማችን ያግዘናል፤ እንዴት መጸለይ እንደሚገባን አናውቅም፤ መንፈስ ግን በቃላት ሊገለጥ በማይችል መቃተት ለእኛ ይማልድልናል።
እንግዲህ፣ እኛንም እናንተንም በክርስቶስ ጸንተን እንድንቆም የሚያደርገን እግዚአብሔር ነው፤ የቀባንም እርሱ ነው፤ የርሱ ለመሆናችን ማኅተሙን ያተመብን ደግሞም ወደ ፊት ለምናገኘው ነገር የመንፈሱን ዋስትና በልባችን ያኖረ እርሱ ነው።
የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ታማኝነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት ነው። እንደነዚህ ያሉትንም የሚከለክል ሕግ የለም።
እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል፣ ይህም የድነታችሁን ወንጌል በሰማችሁ ጊዜ ወደ ክርስቶስ ተጨምራችኋል። አምናችሁም በርሱ በመሆን፣ ተስፋ ሆኖ በተሰጠው በመንፈስ ቅዱስ ማኅተም ታትማችኋል። ለክብሩ ምስጋና ለመሆን የእግዚአብሔር የሆኑት እስኪዋጁ ድረስ፣ እርሱ ለርስታችን ዋስትና የሚሆን መያዣ ነው።