1 ቆሮንቶስ 12:8 ለአንዱ በመንፈስ የጥበብን ቃል መናገር ይሰጠዋል፤ ለሌላው ደግሞ በዚያው መንፈስ የዕውቀትን ቃል መናገር ይሰጠዋል፤
ምሳሌ 2:6 እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከአንደበቱም ዕውቀትና ማስተዋል ይወጣል።
ያዕቆብ 1:5 ከእናንተ ማንም ጥበብ ቢጐድለው፣ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉም የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፤ ለርሱም ይሰጠዋል።
1 ቆሮንቶስ 2:10-11 እግዚአብሔር ግን ይህን በመንፈሱ አማካይነት ለእኛ ገልጦልናል። መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር እንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራል። በውስጡ ካለው ከራሱ መንፈስ በቀር ከሰው መካከል የአንድን ሰው ሐሳብ የሚያውቅ ማን አለ? እንደዚሁም ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር፣ የእግዚአብሔርን ሐሳብ የሚያውቅ ማንም የለም።
ኤፌሶን 1:17-18 የክብር አባት የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክ ይበልጥ እንድታውቁት፣ የጥበብና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ ያለ ማቋረጥ እለምናለሁ። እንዲሁም በርሱ የተጠራችሁለት ተስፋ፣ ይህም በቅዱሳኑ ዘንድ ያለውን ክቡር የሆነውን የርስቱን ባለጠግነት ምን እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ የልባችሁ ዐይኖች እንዲበሩ
ቈላስይስ 2:3 የተሰወረ የጥበብና የዕውቀት ሀብት ሁሉ የሚገኘው በርሱ ዘንድ ነውና።
ዳንኤል 2:21 ጊዜንና ወቅትን ይለውጣል፤ ነገሥታትን በዙፋን ያስቀምጣል፣ ደግሞም ያወርዳቸዋል፤ ጥበብን ለጠቢባን፣ ዕውቀትንም ለሚያስተውሉ ይሰጣል።
ምሳሌ 1:7 እግዚአብሔርን መፍራት የዕውቀት መጀመሪያ ነው፤ ቂሎች ግን ጥበብንና ተግሣጽን ይንቃሉ።
ምሳሌ 3:13-14 ብፁዕ ነው፤ ጥበብን የሚያገኛት፣ ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርጋት ሰው፤ እርሷ ከብር ይልቅ ትርፍ የምታመጣ፣ ከወርቅም ይልቅ ጥቅም የምታስገኝ ናትና።
ያዕቆብ 3:17 ከሰማይ የሆነችው ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፤ በኋላም ሰላም ወዳድ፣ ታጋሽ፣ ዕሺ ባይ፣ ምሕረትና መልካም ፍሬ የሞላባት፣ አድልዎና ግብዝነት የሌለባት ናት።
ኢሳይያስ 11:2 የእግዚአብሔር መንፈስ፣ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፣ የምክርና የኀይል መንፈስ፣ የዕውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል።
ኢዮብ 12:13 “ጥበብና ኀይል የእግዚአብሔር ናቸው፤ ምክርና ማስተዋልም በርሱ ዘንድ ይገኛሉ።
ሮሜ 11:33 የእግዚአብሔር የጥበቡና የዕውቀቱ ባለጠግነት እንዴት ጥልቅ ነው! ፍርዱ አይመረመርም፤ ለመንገዱም ፈለግ የለውም!
ምሳሌ 4:7 ጥበብ ታላቅ ነገር ናት፤ ስለዚህ ጥበብን አግኛት፤ ያለህን ሁሉ ብታስከፍልህም ማስተዋልን ገንዘብህ አድርጋት።
1 ቆሮንቶስ 2:6-7 በበሰሉ ሰዎች መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን፤ ይሁን እንጂ የዚህችን ዓለም ጥበብ ወይም የሚጠፉትን የዚህችን ዓለም ገዦች ጥበብ አይደለም። ነገር ግን ተሰውሮ የነበረውን የእግዚአብሔርን ምስጢር ጥበብ ነው፤ ይህም ጥበብ እግዚአብሔር ከዘመናት በፊት ለክብራችን አስቀድሞ የወሰነው ነው።
ማቴዎስ 13:11 እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማይን ምስጢር ማወቅ ተሰጥቷችኋል፤ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም።
ኤርምያስ 33:3 ‘ወደ እኔ ጩኽ፤ እኔም እመልስልሃለሁ፤ አንተም የማታውቀውን ታላቅና የማይመረመር ነገር እገልጥልሃለሁ።’
ምሳሌ 8:10-11 ከብር ይልቅ ምክሬን፣ ከንጹሕ ወርቅ ይልቅ ዕውቀትን ምረጡ፤ ጥበብ ከቀይ ዕንቍ ይበልጥ ውድ ናትና፤ ከምትመኙት ነገር ሁሉ አንዳች የሚስተካከላት የለም።
ኤፌሶን 3:4-5 እንግዲህ ይህን ስታነብቡ፣ የክርስቶስን ምስጢር እንዴት እንደማስተውል ለመረዳት ትችላላችሁ። ይህም ምስጢር በመንፈስ አሁን ለቅዱሳኑ ሐዋርያትና ነቢያት የተገለጠውን ያህል ባለፉት ዘመናት ለነበሩ ሰዎች አልተገለጠም ነበር።
ምሳሌ 9:10 “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ቅዱሱንም ማወቅ ማስተዋል ነው።
1 ዮሐንስ 5:20 የእግዚአብሔር ልጅ እንደ መጣ፣ እውነተኛ የሆነውን እርሱን እንድናውቅ ማስተዋልን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እኛም እውነተኛ በሆነው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አለን። እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው።
ቈላስይስ 3:16 የክርስቶስ ቃል በሙላት ይኑርባችሁ፤ እርስ በርሳችሁ በጥበብ ሁሉ ተማማሩ፤ ተመካከሩ፤ በመዝሙርና በማሕሌት፣ በመንፈሳዊም ቅኔ በማመስገን በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ።
ዳንኤል 1:17 እግዚአብሔር ለእነዚህ አራት ወጣቶች በማንኛውም ሥነ ጽሑፍና ትምህርት ዕውቀትንና ማስተዋልን ሰጣቸው፤ ዳንኤልም ማንኛውንም ራእይና ሕልም የመረዳት ችሎታ ነበረው።
ሉቃስ 21:15 ተቃዋሚዎቻችሁ ሁሉ ሊቋቋሙትና ሊያስተባብሉት የማይችሉትን ቃልና ጥበብ እሰጣችኋለሁና።
ኢሳይያስ 33:6 እርሱ ለዘመንህ የሚያስተማምን መሠረት፣ የድነት፣ የዕውቀትና የጥበብ መዝገብ ይሆናል፤ እግዚአብሔርንም መፍራት የዚህ ሀብት ቍልፍ ነው።
ሐዋርያት ሥራ 4:13 ሰዎቹም፣ ጴጥሮስና ዮሐንስ እንዲህ በድፍረት ሲናገሩ ባዩአቸው ጊዜ፣ ያልተማሩ ተራ ሰዎች መሆናቸውን ተረድተው ተደነቁ፤ ከኢየሱስ ጋራ እንደ ነበሩም ተገነዘቡ።
ምሳሌ 16:16 ከወርቅ ይልቅ ጥበብን ማግኘት፣ ከብርም ማስተዋልን መምረጥ ምንኛ ይበልጣል!
1 ቆሮንቶስ 14:6 እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜ፣ በመግለጥ ወይም በዕውቀት ወይም በትንቢት ወይም በትምህርት ካልነገርኋችሁ በልሳን ብናገር ምን እጠቅማችኋለሁ?
ኢዮብ 28:28 ከዚያም ሰውን፣ ‘እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብ ነው፤ ከክፋትም መራቅ ማስተዋል ነው’ አለው።”
ሮሜ 15:14 ወንድሞቼ ሆይ፤ እናንተ ራሳችሁ በበጎነት የተሞላችሁ፣ በዕውቀትም ሁሉ የተሞላችሁና አንዱ ሌላውን ለመምከር ችሎታ ያላችሁ መሆናችሁን እኔ ራሴ ርግጠኛ ሆኛለሁ።
ምሳሌ 2:10-11 ጥበብ ልብህ ውስጥ ትገባለችና፤ ዕውቀትም ነፍስህን ደስ ታሰኛለች፤ የመለየት ችሎታ ይጋርድሃል፤ ማስተዋልም ይጠብቅሃል።
ምሳሌ 24:3-4 ቤት በጥበብ ይሠራል፤ በማስተዋልም ይጸናል፤ በሰነፍ ሰው ዕርሻ በኩል ዐለፍሁ፤ በልበ ቢስ ሰው የወይን ቦታ ዐልፌ ሄድሁ፤ በያለበት እሾኽ በቅሎበታል፤ መሬቱም ዐረም ለብሷል፤ ቅጥሩም ፈራርሷል። ያየሁትን ነገር አወጣሁ፣ አወረድሁ፤ ካስተዋልሁትም ትምህርት አገኘሁ፤ ጥቂት ማንቀላፋት፤ ጥቂት ማንጐላጀት፤ እጅን አጣጥፎ ጥቂት ጋደም ማለት፤ ድኽነት እንደ ወንበዴ፣ ዕጦትም መሣሪያ እንደ ታጠቀ ሰው ይመጣብሃል። በዕውቀትም ውድና ውብ በሆነ ንብረት፣ ክፍሎቹ ይሞላሉ።
1 ቆሮንቶስ 1:5 ምክንያቱም በማናቸውም ነገር ይኸውም በንግግር ሁሉ፣ በዕውቀትም ሁሉ በርሱ በልጽጋችኋል፤
ዳንኤል 2:23 የአባቶቼ አምላክ ሆይ፤ አመሰግንሃለሁ፤ አከብርሃለሁም፤ ጥበብንና ኀይልን ሰጥተኸኛልና፤ ከአንተ የጠየቅነውን ነገር አሳውቀኸኛል፤ የንጉሡን ሕልም አሳውቀኸናል።”
2 ጴጥሮስ 1:3 በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን እርሱን በማወቅ ለሕይወትና ለእውነተኛ መንፈሳዊነት የሚያስፈልገንን ሁሉ የመለኮቱ ኀይል ሰጥቶናል።
ፊልጵስዩስ 1:9 ጸሎቴ ይህ ነው፤ ፍቅራችሁ በጥልቅ ዕውቀትና በማስተዋል ሁሉ በዝቶ እንዲትረፈረፍ፣
መዝሙር 25:4-5 እግዚአብሔር ሆይ፤ አካሄድህን እንዳውቅ አድርገኝ፤ መንገድህንም አስተምረኝ። አንተ አዳኜ፣ አምላኬም ነህና፣ በእውነትህ ምራኝ፤ አስተምረኝም፤ ቀኑን ሙሉ አንተን ተስፋ አድርጌአለሁ።
ቈላስይስ 2:2-3 ደግሞም ልባቸው እንዲጽናናና በፍቅር እንዲተሳሰሩ፣ ፍጹም የሆነውን የመረዳት ብልጽግና አግኝተው የእግዚአብሔር ምስጢር የሆነውን ክርስቶስን እንዲያውቁ እተጋለሁ፤ ለዚህ ዓለም መርሕ ከክርስቶስ ጋራ ከሞታችሁ፣ ታዲያ በዚህ ዓለም እንደሚኖር ለምን ትገዙላቸዋላችሁ? “አትያዝ! አትቅመስ! አትንካ!” እንደሚሉት ዐይነት፣ እነዚህ ሁሉ በሰው ትእዛዝና ትምህርት ላይ የተመሠረቱ ስለ ሆኑ በተግባር ላይ ሲውሉ ጠፊ ናቸው። እነዚህ ነገሮች በገዛ ራስ ላይ ከሚፈጥሩት የአምልኮ ስሜት፣ ከዐጕል ትሕትናና ሰውነትን ከመጨቈን አንጻር በርግጥ ጥበብ ያለባቸው ይመስላሉ፤ ነገር ግን የሥጋን ልቅነት ለመቈጣጠር አንዳች ፋይዳ የላቸውም። የተሰወረ የጥበብና የዕውቀት ሀብት ሁሉ የሚገኘው በርሱ ዘንድ ነውና።
ማቴዎስ 16:17 ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፣ ምስጉን ነህ፤ ይህን የገለጠልህ በሰማይ ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም አይደለም።
መዝሙር 111:10 እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ ነው፤ ትእዛዙንም የሚፈጽሙ ጥሩ ማስተዋል አላቸው፤ ምስጋናውም ለዘላለም ይኖራል።
ምሳሌ 14:6 ፌዘኛ ጥበብን ይሻል፤ ሆኖም አያገኛትም፤ ዕውቀት ግን ለአስተዋዮች በቀላሉ ትገኛለች።
ምሳሌ 8:14 ምክርና ትክክለኛ ጥበብ የእኔ ናቸው፤ ማስተዋል አለኝ፤ ብርታት አለኝ።
2 ጢሞቴዎስ 3:16-17 ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር ይጠቅማሉ፤ ይኸውም የእግዚአብሔር ሰው ለመልካም ሥራ ሁሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ነው።
ዘፀአት 31:3 በጥበብ፣ በብልኀት፣ ዕውቀትና ማንኛውንም ዐይነት ሙያ እንዲኖረው የእግዚአብሔርን መንፈስ ሞልቼዋለሁ።
ኤፌሶን 1:9 በክርስቶስ ያቀደውንም የፈቃዱን ምስጢር እንደ በጎ ሐሳቡ እንድናውቅ አደረገ።
መዝሙር 139:17-18 አምላክ ሆይ፤ ለእኔ ያለህ ሐሳብ እንዴት ክቡር ነው! ቍጥሩስ ምንኛ ብዙ ነው! ልቍጠራቸው ብል፣ ከአሸዋ ይልቅ ይበዙ ነበር። ተኛሁም ነቃሁም፣ ገና ከአንተው ጋራ ነኝ።
ምሳሌ 15:14 አስተዋይ ልብ ዕውቀትን ይሻል፤ የሞኝ አፍ ግን ቂልነትን ያመነዥካል።
1 ነገሥት 4:29-30 አምላክ ለሰሎሞን ጥበብንና እጅግ ታላቅ ማስተዋልን እንዲሁም በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ የልብ ስፋትን ሰጠው። የሺሻ ልጆች ኤሊሖሬፍና አኪያ፣ ጸሓፊዎች፤ የአሒሉድ ልጅ ኢዮሣፍጥ፣ ታሪክ ጸሓፊ፤ የሰሎሞን ጥበብ ከምሥራቅ ሰዎች ሁሉ ጥበብ በጣም የላቀ ከግብጽም ጥበብ ሁሉ የበለጠ ነበር፤
1 ቆሮንቶስ 12:11 እነዚህ ሁሉ የዚያው የአንዱ መንፈስ ስጦታዎች ሲሆኑ፣ ለእያንዳንዱ ሰው እርሱ ራሱ እንደ ፈቀደ ይሰጠዋል።
ሐዋርያት ሥራ 6:3 ስለዚህ ወንድሞች ሆይ፤ ከእናንተ መካከል በመንፈስ ቅዱስና በጥበብ የተሞሉ ለመሆናቸው የተመሰከረላቸውን ሰባት ሰዎች ምረጡ፤ ይህን ኀላፊነት ለእነርሱ እንሰጣለን፤
ዳንኤል 5:12 ንጉሡ ብልጣሶር ብሎ የጠራው ይህ ዳንኤል መልካም መንፈስ፣ ዕውቀትና ማስተዋል ያለው ሆኖ ተገኘ፤ ሕልምን የመተርጐም፣ ዕንቈቅልሽን የመፍታትና የተሰወረውን የመግለጥ ልዩ ችሎታም ነበረው። ስለዚህ ዳንኤልን አስጠራ፤ እርሱም የጽሕፈቱን ትርጕም ይነግርሃል።”
2 ሳሙኤል 14:20 አገልጋይህ ኢዮአብ ይህን ያደረገውም ያለውን ሁኔታ ለመለወጥ ሲል ነው፤ ነገር ግን ጌታዬ የእግዚአብሔርን መልአክ ጥበብ የመሰለ ጥበብ ስላለው፣ በምድሪቱ ላይ የሚሆነውን ነገር ሁሉ ያውቃል።”
ኤፌሶን 5:15-17 እንግዲህ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኞች እንዴት እንደምትኖሩ ተጠንቀቁ። ቀኖቹ ክፉ ናቸውና ዘመኑን በሚገባ ዋጁ። ስለዚህ ሞኞች አትሁኑ፤ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ።
መዝሙር 37:30 የጻድቅ አፍ ጥበብን ይናገራል፤ አንደበቱም ፍትሓዊ ነገር ያወራል።
1 ጴጥሮስ 3:15 ክርስቶስን ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት። እናንተ ስላላችሁ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሁልጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በትሕትናና በአክብሮት አድርጉት፤
መዝሙር 94:10 ሕዝቦችን በተግሣጽ ወደ መንገድ የሚመልስ፣ ዕውቀትንስ ለሰው ልጆች የሚያስተምር አይቀጣምን?
ምሳሌ 15:2 የጠቢብ አንደበት ዕውቀትን ታወድሳለች፤ የሞኞች አንደበት ግን ቂልነትን ያፈልቃል።
ዳንኤል 1:20 ንጉሡ በጠየቃቸው በማንኛውም የጥበብና የማስተዋል ጕዳይ በመላ ግዛቱ ካሉት አስማተኞችና ድግምተኞች ሁሉ ዐሥር እጅ በልጠው አገኛቸው።
ምሳሌ 22:17 የጠቢባንን ቃል ልብ ብለህ ስማ፤ ልብህም ወደ ትምህርቴ ያዘንብል፤
ኢሳይያስ 50:4 ልዑል እግዚአብሔር የተባ አንደበት ሰጥቶኛል፤ ስለዚህ ደካሞችን ብርቱ ለማድረግ ምን ማለት እንዳለብኝ ዐውቃለሁ፤ በየማለዳው ያነቃኛል፤ በመማር ላይ እንዳለ ተማሪ ለመስማት ጆሮዬን ያነቃዋል።
ኢዮብ 32:8 ነገር ግን በሰው ያለው መንፈስ፣ ሁሉን ቻይ አምላክ እስትንፋስ፣ ማስተዋልን ይሰጣል።
ምሳሌ 20:15 ወርቁም አለ፤ ቀዩም ዕንቍ ተትረፍርፏል፤ ዕውቀት የሚናገሩ ከንፈሮች ግን ብርቅ ጌጦች ናቸው።
2 ጢሞቴዎስ 1:7 እግዚአብሔር የኀይልና የፍቅር፣ ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሀት መንፈስ አልሰጠንምና።
ሮሜ 12:2 መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በአእምሯችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።
መዝሙር 119:99 ምስክርነትህን አሰላስላለሁና፣ ከአስተማሪዎቼ ሁሉ የላቀ አስተዋይ ልብ አገኘሁ።
ምሳሌ 23:23 እውነትን ግዛት እንጂ አትሽጣት፤ ጥበብን፣ ተግሣጽንና ማስተዋልን ገንዘብህ አድርግ።
መዝሙር 143:10 አንተ አምላኬ ነህና፣ ፈቃድህን እንድፈጽም አስተምረኝ፤ መልካሙ መንፈስህም፣ በቀናችው መንገድ ይምራኝ።
ምሳሌ 1:5 ጥበበኞች ያድምጡ፤ ትምህርታቸውንም ያዳብሩ፤ አስተዋዮችም መመሪያ ያግኙበት፤
ኤፌሶን 1:3 በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ በክርስቶስ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፤
ምሳሌ 3:5-6 በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል።
ቈላስይስ 1:26-27 ይህም ቃል ከዘመናትና ከትውልዶች ተሰውሮ ምስጢር ሆኖ ቈይቶ ነበር፤ አሁን ግን ለቅዱሳኑ ተገልጧል። ለእነርሱም እግዚአብሔር የዚህ ምስጢር ክብር ባለጠግነት በአሕዛብ መካከል ምን ያህል እንደ ሆነ ለማሳወቅ መረጠ፤ እርሱም የክብር ተስፋ የሆነው በእናንተ ውስጥ ያለው ክርስቶስ ነው።
ሮሜ 16:25-26 በዘላለማዊ አምላክ ትእዛዝ ሕዝቦች ሁሉ አምነው እንዲታዘዙ፣ በነቢያት መጻሕፍት አሁን በተገለጠው፣ ላለፉት ረዥም ዘመናት ተሰውሮ በነበረው ምስጢር መገለጥ መሠረት፣ በአስተማርሁት ወንጌልና በኢየሱስ ክርስቶስ መሰበክ ሊያጸናችሁ ለሚችለው፣
ፊልጵስዩስ 3:8 ከዚህም በላይ ለርሱ ብዬ ሁሉን ነገር የተውሁለትን፣ ወደር የሌለውን ጌታዬን ክርስቶስ ኢየሱስን ከማወቅ ታላቅነት ጋራ ሳነጻጽር፣ ሁሉንም ነገር እንደ ጕድለት እቈጥረዋለሁ፤ ለርሱ ስል ሁሉን ዐጥቻለሁ፤ ክርስቶስን አገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቈጥራለሁ፤
መዝሙር 32:8 አስተምርሃለሁ፤ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ እመክርሃለሁ፤ በዐይኔም እከታተልሃለሁ።
ሉቃስ 11:49 ስለዚህም የእግዚአብሔር ጥበብ እንዲህ አለች፤ ‘ነቢያትንና ሐዋርያትን እልክላቸዋለሁ፤ እነርሱ አንዳንዶቹን ይገድላሉ፤ ሌሎችንም ያሳድዳሉ።’
ኤፌሶን 3:10 ሐሳቡም በአሁኑ ዘመን በቤተ ክርስቲያን አማካይነት ብዙ ገጽታ ያለው የእግዚአብሔር ጥበብ በሰማያዊ ስፍራ ላሉት ገዦችና ባለሥልጣናት ይታወቅ ዘንድ ነው፤
መዝሙር 19:7 የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው፤ ነፍስንም መልሶ ያለመልማል፤ የእግዚአብሔር ሥርዐት የታመነ ነው፤ አላዋቂውን ጥበበኛ ያደርጋል።
ኤርምያስ 10:12 እርሱ ግን ምድርን በኀይሉ ፈጠረ፤ ዓለምን በጥበቡ መሠረተ፤ ሰማያትንም በማስተዋሉ ዘረጋ።
1 ዮሐንስ 2:27 እናንተ ግን ከርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በውስጣችሁ ይኖራልና ማንም እንዲያስተምራችሁ አያስፈልግም፤ ነገር ግን የርሱ ቅባት ስለ ሁሉም ነገር፣ እውነተኛ የሆነውን እና ሐሰት ያልሆነው እናንተን እንደሚያስተምር፣ እናንተንም እንዳስተማራችሁ በርሱ ኑሩ።
ምሳሌ 25:2 ነገርን መሰወር ለእግዚአብሔር ክብሩ ነው፤ ነገርን ፈልፍሎ ማውጣት ግን ለነገሥታት ክብራቸው ነው።
ኢዮብ 11:7-9 “የእግዚአብሔርን ጥልቅ ምስጢር ልትለካ ትችላለህን? ወይስ ሁሉን ቻዩን አምላክ መርምረህ ትደርስበታለህን? ከሰማይ ይልቅ ከፍ ይላል፤ ምን ልታደርግ ትችላለህ? ከሲኦልም ይጠልቃል፤ ምን ልታውቅ ትችላለህ? መጠኑ ከምድር ይልቅ ይረዝማል፤ ከባሕርም ይልቅ ይሰፋል።
ምሳሌ 8:35 የሚያገኘኝ ሁሉ ሕይወትን ያገኛልና፤ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ሞገስን ይቀበላል።
1 ቆሮንቶስ 2:12 ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ፣ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንምና፤ ይህም እግዚአብሔር በነጻ የሰጠንን እናውቅ ዘንድ ነው።
ማቴዎስ 11:25 በዚያ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፤ ይህን ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ፤
ኢሳይያስ 28:29 ይህ ሁሉ የሚሆነው በምክሩ ድንቅ፣ በጥበቡ ታላቅ ከሆነው፣ ከሰራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።
ምሳሌ 8:12 “እኔ ጥበብ ከማስተዋል ጋራ አብሬ እኖራለሁ፤ ዕውቀትና ልባምነት ገንዘቦቼ ናቸው።
ሐዋርያት ሥራ 1:8 ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኀይልን ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳና በሰማርያ ሁሉ፣ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ።”
መዝሙር 119:144 ምስክርነትህ ለዘላለም የጽድቅ ምስክርነት ነው፤ በሕይወት እኖር ዘንድ ማስተዋልን ስጠኝ።
ኢዮብ 36:22 “እነሆ፤ እግዚአብሔር በኀይሉ ከፍ ከፍ ብሏል፤ እንደ እርሱስ ያለ አስተማሪ ማን ነው?
ኢሳይያስ 55:9 “ሰማያት ከምድር ከፍ እንደሚሉ፣ መንገዴ ከመንገዳችሁ፣ ሐሳቤም ከሐሳባችሁ እንዲሁ ከፍ ያለ ነው።