1 ቆሮንቶስ 12:10 ለአንዱ ታምራትን የማድረግ፣ ለሌላው ትንቢትን የመናገር፣ ለሌላው ደግሞ መናፍስትን የመለየት፣ ለአንዱ በልዩ ልዩ ልሳን የመናገር፣ ለሌላው ደግሞ በልዩ ልዩ ልሳን የተነገረውን የመተርጐም ስጦታ ይሰጠዋል።
1 ቆሮንቶስ 14:1 ፍቅርን ተከታተሉ፤ መንፈሳዊ ስጦታዎችን፣ በተለይም ትንቢት የመናገርን ስጦታ በብርቱ ፈልጉ።
1 ቆሮንቶስ 14:3 ትንቢትን የሚናገር ግን ለማነጽ፣ ለማበረታታትና ለማጽናናት ለሰው ይናገራል።
1 ቆሮንቶስ 14:4 በልሳን የሚናገር ራሱን ያንጻል፤ ትንቢትን የሚናገር ግን ቤተ ክርስቲያንን ያንጻል።
1 ቆሮንቶስ 14:5 ሁላችሁም በልሳን ብትናገሩ እወድዳለሁ፤ ከዚህ ይልቅ ግን ትንቢትን ብትናገሩ እወድዳለሁ። ቤተ ክርስቲያን እንድትታነጽ በልሳን የሚናገር ሰው የተናገረውን ካልተረጐመ፣ በልሳን ከሚናገር ይልቅ ትንቢትን የሚናገር ይበልጣል።
1 ቆሮንቶስ 14:22 ስለዚህ በልሳን መናገር ለማያምኑ የሚሆን ምልክት እንጂ ለሚያምኑ አይደለም፤ ትንቢት ግን ለሚያምኑ እንጂ ለማያምኑ አይደለም።
1 ቆሮንቶስ 14:24-25 ነገር ግን ሁሉም ትንቢት በመናገር ላይ ሳሉ፣ እንግዳ ወይም የማያምን ሰው ቢገባ፣ በሁሉ ይወቀሣል፤ በሁሉ ይመረመራል፤ በልቡም የተሰወረው ነገር ይገለጣል፤ እንዲሁም፣ “እግዚአብሔር በርግጥ በመካከላችሁ ነው” በማለት በግንባሩ ተደፍቶ ለእግዚአብሔር ይሰግዳል።
1 ቆሮንቶስ 14:31 እያንዳንዳችሁ እንድትማሩና እያንዳንዳችሁ እንድትበረታቱ፣ ሁላችሁ በየተራ ትንቢት መናገር ትችላላችሁ።
1 ቆሮንቶስ 14:39 ስለዚህ፣ ወንድሞች ሆይ፤ ትንቢት ለመናገር በብርቱ ፈልጉ፤ በልሳን መናገርንም አትከልክሉ፤
ኤፌሶን 4:11 አንዳንዶቹ ሐዋርያት፣ አንዳንዶቹ ነቢያት፣ አንዳንዶቹም ወንጌል ሰባኪዎች፣ ሌሎቹ ደግሞ እረኞችና አስተማሪዎች ይሆኑ ዘንድ የሰጠ እርሱ ነው፤
ሮሜ 12:6 እንደ ተሰጠን ጸጋ የተለያዩ ስጦታዎች አሉን፤ ለአንዱ የተሰጠው ስጦታ ትንቢት መናገር ከሆነ፣ እንደ እምነቱ መጠን ይናገር።
ሐዋርያት ሥራ 2:17 “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በመጨረሻው ቀን፣ መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈስሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤ ጕልማሶቻችሁም ራእይ ያያሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ።
ሐዋርያት ሥራ 2:18 በእነዚያ ቀናት በወንዶችና በሴቶች ባሮቼም ላይ፣ መንፈሴን አፈስሳለሁ፤ እነርሱም ትንቢት ይናገራሉ።
ሐዋርያት ሥራ 11:27-28 በዚህ ጊዜ አንዳንድ ነቢያት ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ወረዱ። ከእነርሱም አንዱ አጋቦስ የተባለው ተነሥቶ በዓለም ሁሉ ታላቅ ራብ እንደሚሆን መንፈስ ቅዱስ አስመልክቶት ተናገረ፤ ይህም በቀላውዴዎስ ቄሳር ዘመን ተፈጸመ።
ሐዋርያት ሥራ 13:1 በአንጾኪያ ባለችው ቤተ ክርስቲያን ነቢያትና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም፦ በርናባስ፣ ኔጌር የተባለው ስምዖን፣ የቀሬናው ሉክዮስ፣ የአራተኛው ክፍል ገዥ የሄሮድስ ዐብሮ አደግ የነበረው ምናሔ እና ሳውል ነበሩ።
ሐዋርያት ሥራ 19:6 ጳውሎስም እጁን በላያቸው በጫነ ጊዜ፣ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው፤ በሌሎች ቋንቋዎች ተናገሩ፤ ትንቢትም ተናገሩ።
አሞጽ 3:7 በእውነት ጌታ እግዚአብሔር ምስጢሩን ለአገልጋዮቹ ለነቢያት ሳይገልጥ፣ ምንም ነገር አያደርግም።
ኤርምያስ 1:9 እግዚአብሔርም እጁን ዘርግቶ አፌን ዳሰሰና እንዲህ አለኝ፤ “እነሆ፤ ቃሌን በአፍህ አኑሬአለሁ፤
ኤርምያስ 23:28 ሕልመኛ ነቢይ ሕልሙን ያውራ፤ ቃሌ ያለው ግን በታማኝነት ይናገር፤ ገለባና እህል ምን አንድ አድርጓቸው!” ይላል እግዚአብሔር።
ሕዝቅኤል 2:7 እነርሱ ዐመፀኛ ቤት ስለ ሆኑ፣ ቢሰሙም ባይሰሙም አንተ ቃሌን ንገራቸው።
ኢዩኤል 2:28 “ከዚህም በኋላ፣ መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈስሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ፤ ጕልማሶቻችሁም ራእይ ያያሉ።
ሚክያስ 3:8 እኔ ግን፣ ለያዕቆብ በደሉን፣ ለእስራኤልም ኀጢአቱን እነግር ዘንድ፣ ኀይልን በእግዚአብሔር መንፈስ፣ ፍትሕና ብርታትም ተሞልቻለሁ።
2 ጴጥሮስ 1:21 ምክንያቱም ትንቢት ከእግዚአብሔር የተላኩ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው የተናገሩት እንጂ ከቶ በሰው ፈቃድ የመጣ አይደለም።
ራእይ 1:3 ዘመኑ ቀርቧል፤ እንግዲህ ይህን የትንቢት ቃል የሚያነብብ፣ የሚሰሙትና የተጻፈውንም የሚጠብቁ ብፁዓን ናቸው።
ራእይ 19:10 እኔም ልሰግድለት በእግሩ ሥር ተደፋሁ፤ እርሱ ግን፣ “ተው! ይህን አታድርግ! እኔም ከአንተና የኢየሱስን ምስክር ከያዙት ወንድሞችህ ጋራ አገልጋይ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ የኢየሱስ ምስክር የትንቢት መንፈስ ነውና” አለኝ።
ኤርምያስ 28:9 ነገር ግን ስለ ሰላም ትንቢት የተናገረ ነቢይ እግዚአብሔር በእውነት እንደ ላከው የሚታወቀው የተናገረው ትንቢት ሲፈጸም ነው።”
ዘኍል 12:6 እንዲህ አላቸው፤ “ቃሌን ስሙ፤ “የእግዚአብሔር ነቢይ በመካከላችሁ ቢኖር፣ በራእይ እገለጥለታለሁ፤ በሕልምም እናገረዋለሁ።
2 ነገሥት 20:1 ሕዝቅያስ በጠና ታምሞ፤ ሊሞት ተቃርቦ ነበር። የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስም ወደ እርሱ መጥቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ከሕመምህ አትድንም፤ ትሞታለህና ቤትህን አስተካክል’ ” አለው።
1 ሳሙኤል 3:20 ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ያሉ እስራኤላውያን በሙሉ ሳሙኤል በርግጥ የእግዚአብሔር ነቢይ መሆኑን ዐወቁ።
ኢሳይያስ 6:8 ከዚያም የጌታ ድምፅ፣ “ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል?” ሲል ሰማሁት። እኔም፣ “እነሆኝ፤ እኔን ላከኝ!” አልሁ።
ኤርምያስ 23:16 የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነዚህ ነቢያት የሚተነብዩላችሁን አትስሙ፤ በባዶ ተስፋ ይሞሏችኋል፤ ከእግዚአብሔር አፍ የወጣ ሳይሆን፣ ከገዛ ልባቸው የሆነውን ራእይ ይናገራሉ።
ኢሳይያስ 30:10 ባለራእዮችን፣ “ከእንግዲህ ራእይን አትዩ!” ይላሉ፤ ነቢያትንም እንዲህ ይላሉ፤ “እውነተኛውን ትንቢት ከእንግዲህ አትንገሩን፤ ደስ የሚያሠኘውን ንገሩን፤ የሚያማልለውን ተንብዩልን።
1 ነገሥት 22:14 ሚክያስ ግን፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! እግዚአብሔር የነገረኝን ብቻ እነግረዋለሁ” አለ።
ዘካርያስ 1:6 ለባሪያዎቼ ለነቢያት ያዘዝኋቸው ቃልና ሥርዐት በአባቶቻችሁ ላይ አልደረሰምን? “እነርሱም ንስሓ ገብተው እንዲህ አሉ፤ ‘የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በወሰነው መሠረት፣ ለሥራችንና ለመንገዳችን የሚገባውን አድርጎብናል።’ ”
ማቴዎስ 7:15 “በውስጣቸው ነጣቂ ተኵላዎች ሆነው ሳሉ የበግ ለምድ ለብሰው መካከላችሁ በመግባት ከሚያሸምቁ ሐሰተኛ ነቢያት ተጠንቀቁ።
ማቴዎስ 24:24 ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት ይነሣሉና፤ ቢቻል የተመረጡትን ለማሳት ሲሉ ታላላቅ ምልክቶችንና ታምራትን ያደርጋሉ።
ሉቃስ 1:70 ይህም ጥንት በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ እንደ ተናገረው፣
ሐዋርያት ሥራ 3:18 እግዚአብሔር ግን የርሱ የሆነው ክርስቶስ መከራን እንዲቀበል አስቀድሞ በነቢያቱ ሁሉ አፍ የተናገረውን ፈጽሟል።
2 ነገሥት 17:13 ይህም ሆኖ እግዚአብሔር፣ “ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ አባቶቻችሁ እንዲፈጽሙት ባዘዝኋቸው ሕግ ሁሉ መሠረት እንዲሁም በአገልጋዮቼ በነቢያት አማካይነት ለእናንተ ባስተላለፍሁት ሕግ መሠረት፣ ትእዛዜንና ሥርዐቴን ጠብቁ” ብሎ በነቢያቱና በባለራእዮች ሁሉ እስራኤልንና ይሁዳን አስጠንቅቆ ነበር።
ኤርምያስ 14:14 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “ነቢያቱ በስሜ የሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፤ እኔ አልላክኋቸውም፤ አላዘዝኋቸውም፤ አልተናገርኋቸውምም። የሐሰት ራእይ፣ ሟርት፣ ከንቱ ነገርንና የልባቸውን ሽንገላ ይተነብዩላችኋል።
ሕዝቅኤል 13:3 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ አንዳች ነገር ሳያዩ የራሳቸውን መንፈስ ለሚከተሉ ሞኞች ነቢያት ወዮላቸው!
ኤርምያስ 23:21 እኔ እነዚህን ነቢያት አልላክኋቸውም፤ እነርሱ ግን ለራሳቸው መልእክታቸውን ይዘው ሮጡ፣ ሳልናገራቸውም፣ ትንቢት ተናገሩ።
ኤርምያስ 23:29 “ቃሌ እንደ እሳት፣ ድንጋይንም እንደሚያደቅቅ መዶሻ አይደለምን?” ይላል እግዚአብሔር።
ማቴዎስ 10:41 ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ያገኛል፤ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቅን ዋጋ ያገኛል።
ራእይ 22:18 የዚህን መጽሐፍ የትንቢት ቃል የሚሰማውን ሁሉ አስጠነቅቃለሁ፤ ማንም በዚህ ቃል ላይ አንዳች ቢጨምር፣ እግዚአብሔር በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን መቅሠፍቶች ይጨምርበታል፤
ራእይ 10:11 ከዚያም፣ “ስለ ብዙ ሕዝቦች፣ ወገኖች፣ ቋንቋዎችና ነገሥታት እንደ ገና ትንቢት ልትናገር ይገባሃል” ተባልሁ።
1 ነገሥት 18:22 ከዚያም ኤልያስ እንዲህ አላቸው፤ “ከእግዚአብሔር ነቢያት የተረፍሁ እኔ ብቻ ነኝ፤ በኣል ግን አራት መቶ ዐምሳ ነቢያት አሉት።
2 ነገሥት 2:15 ከኢያሪኮም መጥተው ይህን ያዩ የነበሩት የነቢያት ወገኖች፣ “የኤልያስ መንፈስ በኤልሳዕ ላይ ዐርፏል” አሉ፤ ሊያገኙትም ሄደው በፊቱ ወደ መሬት ዝቅ ብለው እጅ ነሡ።
ሐዋርያት ሥራ 13:2 እነዚህም ጌታን እያመለኩና እየጾሙ ሳሉ፣ መንፈስ ቅዱስ፣ “በርናባስንና ሳውልን እኔ ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ” አለ።
አሞጽ 7:15 እግዚአብሔር ግን የበግ መንጋ ከምጠብቅበት ቦታ ወስዶ፣ ‘ሂድና ለሕዝቤ ለእስራኤል ትንቢት ተናገር’ አለኝ፤
ዮናስ 3:4 ዮናስም ወደ ከተማዪቱ ገብቶ የመጀመሪያውን ቀን ከተጓዘ በኋላ “ነነዌ በአርባ ቀን ውስጥ ትገለበጣለች” ብሎ ዐወጀ።
ሕዝቅኤል 37:4 ከዚያም እንዲህ አለኝ፤ “ለእነዚህ ዐጥንቶች ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘እናንተ ደረቅ ዐጥንቶች፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ!
1 ቆሮንቶስ 12:7 ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ሰው የሚሰጠው ለጋራ ጥቅም ነው።
ዳንኤል 9:24 “ዐመፃን ለማስቆም፣ ኀጢአትን ለማስወገድ፣ በደልን ለማስተስረይ፣ ዘላለማዊ ጽድቅን ለማምጣት፣ ራእይንና ትንቢትን ለማተምና፣ እጅግ ቅዱስ የሆነውን ለመቀባት ስለ ሕዝብህና ስለ ተቀደሰችው ከተማህ ሰባ ሱባዔ ታውጇል።
ሶፎንያስ 3:17 እግዚአብሔር አምላክሽ በመካከልሽ አለ፤ እርሱ ብርቱ ታዳጊ ነው፤ በአንቺ እጅግ ደስ ይለዋል፤ በፍቅሩ ያሳርፍሻል፤ በዝማሬም በአንቺ ላይ ከብሮ ደስ ይሰኛል።”
ዘካርያስ 8:9 የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሠረት ሲጣል፣ በዚያ የነበሩ ነቢያት የተናገሩትን ቃል አሁን የምትሰሙ ሁሉ፣ ለመገንባት እጃችሁን አበርቱ።
ሆሴዕ 12:10 ለነቢያት ተናገርሁ፤ ራእይንም አበዛሁላቸው፤ በእነርሱም በኩል በምሳሌ ተናገርሁ።”
ሕዝቅኤል 13:9 እጄ የሐሰት ራእይ በሚያዩና በሚያሟርቱ ነቢያት ላይ ተነሥቷል። የሕዝቤ ጉባኤ ተካፋይ አይሆኑም፤ በእስራኤል ቤት መዝገብ አይጻፉም፤ ወደ እስራኤልም ምድር አይገቡም። በዚያ ጊዜ እኔ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
2 ዜና መዋዕል 20:20 በማግስቱም ጧት በማለዳ ተነሥተው ወደ ቴቁሔ ምድረ በዳ ሄዱ። መንገድ እንደ ጀመሩም ኢዮሣፍጥ ቆሞ፣ “ይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ፣ ስሙኝ! በአምላካችሁ በእግዚአብሔር እመኑ፤ ትጸኑማላችሁ። በነቢያቱም እመኑ፤ ይሳካላችሁማል” አላቸው።
1 ሳሙኤል 10:5-6 “ከዚያ በኋላ የፍልስጥኤማውያን ጦር ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወደ ጊብዓ ትሄዳለህ። ወደ ከተማዪቱ እንደ ደረስህም የነቢያት ጉባኤ በመሰንቆ፣ በከበሮ፣ በእንቢልታና በበገና ታጅበው ትንቢት እየተናገሩ ከማምለኪያው ኰረብታ ላይ ሲወርዱ ታገኛቸዋለህ። የእግዚአብሔር መንፈስ በኀይል ይወርድብሃል፤ ከእነርሱ ጋራ ትንቢት ትናገራለህ፤ እንደ ሌላ ሰውም ሆነህ ትለወጣለህ።
1 ነገሥት 19:16 እንዲሁም የናሜሲን ልጅ ኢዩን በእስራኤል ላይ እንዲነግሥ ቅባው፤ ደግሞም ነቢይ ሆኖ በእግርህ እንዲተካ የአቤልምሖላን ሰው የሣፋጥን ልጅ ኤልሳዕን ቅባው።