አዲስ ቀን፣ አዲስ ጅምር ተሰጥቶናል። እግዚአብሔርን ለማመስገን፣ ስለቸርነቱና ስለምህረቱ ልናመሰግነው ብዙ ምክንያት አለን።
በየቀኑ ብዙ ፈተናዎች ያጋጥሙናል። አንዳንዴ መቋቋም እንደማንችል እንሰማለን። ግን ይህን ሁሉ መካከል፣ ዛሬ በህይወት መኖራችን በራሱ ከፈጣሪያችን የተሰጠን ስጦታና በረከት መሆኑን አንዘንጋ።
እግዚአብሔር ለፈጠረልን ውብ ፍጥረት እናመስግነው። የፈጠረው ሁሉ መልካም ነው። ይህን ቀን በሚገባ ለመጠቀም የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ እንጠይቅ። ሁልጊዜም በብርሃኑ እንድንመላለስ እንለምነው። በዚህ መልኩ የጌታችንን ቸርነት በሚገባ እናስተውላለን፣ ሁልጊዜም በደስታ እንሞላለን።
ለሰዎች እንደምን አደሩ ከማለትህ በፊት፣ ለመንፈስ ቅዱስ "እንደምን አደርክ" በል። ቀንህን ከእርሱ ጋር ጀምር። ማታም በእርሱ ደስ እያልክ ተኛ።
ስትተኛ አትፈራም፤ ትተኛለህ እንቅልፍህም ጣፋጭ ይሆናል። ድንገተኛን መከራ፣ በክፉዎች ላይ የሚደርሰውንም ጥፋት አትፍራ፤ እግዚአብሔር መታመኛህ ይሆናልና፤ እግርህንም በወጥመድ ከመያዝ ይጠብቃል።
ልዑል እግዚአብሔር የተባ አንደበት ሰጥቶኛል፤ ስለዚህ ደካሞችን ብርቱ ለማድረግ ምን ማለት እንዳለብኝ ዐውቃለሁ፤ በየማለዳው ያነቃኛል፤ በመማር ላይ እንዳለ ተማሪ ለመስማት ጆሮዬን ያነቃዋል።
ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን ፈልጉ፤ እነዚህም ሁሉ ይጨመሩላችኋል። ስለዚህ ለነገ በማሰብ አትጨነቁ፤ የነገ ጭንቀት ለነገ ይደር፤ እያንዳንዱ ዕለት የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለውና።
አምላክ ሆይ፤ ለእኔ ያለህ ሐሳብ እንዴት ክቡር ነው! ቍጥሩስ ምንኛ ብዙ ነው! ልቍጠራቸው ብል፣ ከአሸዋ ይልቅ ይበዙ ነበር። ተኛሁም ነቃሁም፣ ገና ከአንተው ጋራ ነኝ።
“እናንተ ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ በልቤ የዋህና ትሑት ነኝና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ “ይመጣል ተብሎ የሚጠበቀው አንተ ነህ? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ሲል ጠየቀ። ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነውና።”
በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ፣ ከምስጋናም ጋራ ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ እንጂ ስለ ማንኛውም ነገር አትጨነቁ። ከማስተዋል በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም፣ ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።
የምታደርጉትን ሁሉ ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉት ቈጥራችሁ በሙሉ ልባችሁ አድርጉት፤ ከጌታ ዘንድ እንደ ብድራት የምትቀበሉት ርስት እንዳለ ታውቃላችሁና፤ የምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስን ነው።