የመጽሐፍ ቅዱስ ቀን ለእግዚአብሔር ቃል ትልቅ ቦታ የምንሰጥበት እና የትርጉምና የህትመት ሥራውን ለማስፋፋት የምንችልበት ወሳኝ አጋጣሚ ነው። እንደ አንድ የእምነት ቤተሰብ በፍቅር ተስማምተን እንድንኖር፣ በክርስቶስ አገልግሎት ተጠናክረን በወንጌል አማካኝነት የእምነት ማህበረሰቦችን እንድንገነባ ቅዱስ ጳውሎስ ያሳስበናል። "የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል" (ዕብ. 4:12)። ይህንን ልዩ ቀን ለማክበር ከሁሉ የተሻለው መንገድ እኛ አማኞች በሙሉ በአንድነት ለማህበረሰባችን መጽሐፍ ቅዱስ በማድረስ እነዚህ ሰዎች በክርስቶስ እውነት እንዲታነጹና እንዲመሩ መርዳት ነው።
የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው፤ ነፍስንም መልሶ ያለመልማል፤ የእግዚአብሔር ሥርዐት የታመነ ነው፤ አላዋቂውን ጥበበኛ ያደርጋል። የእግዚአብሔር ሕግጋት ትክክል ናቸው፤ ልብን ደስ ያሰኛሉ። የእግዚአብሔር ትእዛዝ ብሩህ ነው፤ ዐይንን ያበራል።
ይህ የሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፤ በውስጡ የተጻፈውን ሁሉ በጥንቃቄ እንድትፈጽመውም ቀንም ሆነ ሌት ከሐሳብህ አትለየው፤ ይህን ካደረግህ ያሰብኸው ይቃናል፤ ይሳካልም፤
ኢየሱስም በርሱ ያመኑትን አይሁድ እንዲህ አላቸው፤ “በትምህርቴ ብትጸኑ እናንተ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነጻ ያወጣችኋል።”
የክርስቶስ ቃል በሙላት ይኑርባችሁ፤ እርስ በርሳችሁ በጥበብ ሁሉ ተማማሩ፤ ተመካከሩ፤ በመዝሙርና በማሕሌት፣ በመንፈሳዊም ቅኔ በማመስገን በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ።
ነገር ግን ደስ የሚሠኘው በእግዚአብሔር ሕግ ነው፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያሰላስለዋል። እርሱም በወራጅ ውሃ ዳር እንደ ተተከለች፣ ፍሬዋን በየወቅቱ እንደምትሰጥ፣ ቅጠሏም እንደማይጠወልግ ዛፍ ነው፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።
ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር ሳይሆን፣ ሕያው በሆነና ጸንቶ በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል አማካይነት ከማይጠፋ ዘር ነው። ምክንያቱም መጽሐፍ እንደሚል፣ “ሥጋ ለባሽ ሁሉ እንደ ሣር ነው፤ ክብሩም ሁሉ እንደ ሜዳ አበባ ነው። ሣሩ ይጠወልጋል፤ አበባውም ይረግፋል፤ የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።” የተሰበከላችሁም የምሥራች ቃል ይህ ነው።
ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው በእያንዳንዱ ቃል እንጂ፣ በእንጀራ ብቻ እንደማይኖር ሊያስተምርህ አስራበህ፤ አንተም ሆንህ አባቶችህ የማታውቁትን መና መገበህ፤
ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር ይጠቅማሉ፤ ይኸውም የእግዚአብሔር ሰው ለመልካም ሥራ ሁሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ነው።
የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነውና፤ በሁለት በኩል ስለት ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፤ ነፍስንና መንፈስን፣ ጅማትንና ቅልጥምን እስኪለያይ ድረስ ዘልቆ ይወጋል፤ የልብንም ሐሳብና ምኞት ይመረምራል።