ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ጦቢት 5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)መልአኩ ሩፋኤል ከጦብያ ጋር እንደ ሄደ 1 ጦብያም መለሰ እንዲህም አለ፥ “አባቴ! ያዘዝኸኝን ሁሉ አደርጋለሁ። 2 ነገር ግን ከማላውቀው ሰው ያን ብር መቀበል እንዴት እችላለሁ?” 3 እርሱም ደብዳቤ ሰጠው፤ እንዲህም አለው፥ “ከአንተ ጋር የሚሄድ ሰው ፈልግ፤ እኔም በሕይወት ሳለሁ ደመወዙን እሰጠዋለሁ፤ ሄደህም ያንን ብር ተቀበል።” 4 እርሱም ሰውን ሊፈልግ ሄዶ መልአኩን ሩፋኤልን አገኘው፤ ነገር ግን መልአክ እንደ ሆነ አላወቀም። 5 እርሱም አለው፥ “ሀገሩን ታውቅ እንደ ሆነ ወደ ሜዶን ክፍል ወደ ራጊስ ከኔ ጋራ መሄድ ትችላለህን?” 6 መልአኩም እንዲህ አለው፥ “ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፤ መንገዱንም ዐውቃለሁ፤ በገባኤልም ዘንድ ነበርሁ።” 7 ጦብያም፥ “ላባቴ እስክነግረው ድረስ ቈየኝ” አለው። 8 እርሱም፥ “ሂድ፤ አትቈይ” አለው፤ ለአባቱም፥ “ከእኔ ጋር የሚሄድ እነሆ አገኘሁ” አለው። እርሱም፥ “ከማን ወገን እንደ ሆነ፥ ካንተም ጋራ ለመሄድ የታመነ እንደ ሆነ ዐውቅ ዘንድ ወደ እኔ ጥራው” አለው። 9 ጠራውና ገባ፤ እርስ በርሳቸውም እጅ ተነሣሡ። 10 ጦቢትም፥ “አንተ ወንድሜ! ከማን ወገን ነህ? ከወዴትስ ሀገር ነህ?” አለው። 11 መልአኩም፥ “ወገኔንና ሀገሬን ትመረምር? ወይስ ከልጅህ ጋራ የምሄድበትን ዋጋ ትሰጠኝ?” አለው። ጦቢትም፥ “አንተ ወንድሜ ዘመድህንና ስምህን ዐውቅ ዘንድ እወዳለሁ” አለው። 12 እርሱም፥ “እኔስ የወንድምህ የታላቁ አናንያ ዘመድ አዛርያ ነኝ” አለው። 13 ጦቢትም አለው፥ “አንተ ወንድሜ ደኅና ነህን? ወገንህንና ሀገርህን ዐውቅ ዘንድ መርምሬአለሁና አትንቀፈኝ፤ ነገር ግን አንተ በእውነቱ ከደግና ከተባረከ ወገን ነህ፤ እኔም የታላቁ የሴምዩን ልጆች አናንያንና ኢታያንን ዐውቃቸዋለሁ፤ እንሰግድ ዘንድ ከእነርሱ ጋር አብረን ወደ ኢየሩሳሌም ሄደን ነበር፤ በኵራቱንና የእህላችንን ዐሥራት ወስደን ነበር፤ ነገር ግን በአባቶቻችን በደል አልበደልንም። 14 ወንድሜ አንተ ግን ከደግ ቤተ ሰብ ነህ፤ ነገር ግን ንገረኝ፤ ደመወዝህን ምን እንስጥህ? በየቀኑ አንድ ድራህማ እንስጥህን? ምግብህስ ከልጄ ጋር ይሁን? 15 በደኅና ከተመለሳችሁ በደመወዝህ ላይ እጨምርልሃለሁ፤” እንደዚህም ጨረሱ። 16 ጦብያንም አለው፥ “ትሄዱ ዘንድ፥ ትከናወኑም ዘንድ ተዘጋጁ።” ልጁም ለመንገድ ስንቃቸውን አዘጋጀ፤ አባቱም አለው፥ “ከዚህ ሰው ጋር ሂድ፤ በሰማያት የሚኖር እግዚአብሔር መንገዳችሁን ያቅናላችሁ፤ መልአኩም አብሮአችሁ ይሂድ፤” ሁለቱም ወጥተው ሄዱ፤ ሌላው ልጃቸውም ተከተላቸው። 17 እናቱ ሐናም አለቀሰች፤ ጦቢትንም እንዲህ አለችው፥ “ልጄን ለምን ላክኸው? እርሱ በፊታችን የሚወጣና የሚገባ፥ በእጃችን ያለ ምርኩዛችን አይደለምን? 18 ብሩስ ይጥፋ የልጄም ቤዛ ይሁን! 19 የምንኖርበት እግዚአብሔር የሰጠን ይበቃናልና።” 20 ጦቢትም አላት፥ “እኅቴ አትጨነቂ፤ በደኅና ይመለሳል፤ በዐይኖችሽም ታይዋለሽ። 21 ቸር መልአክ በፊቱ ይሄዳልና፥ ጎዳናውንም ያቃናለታልና፥ በደኅናም ይመለሳልና።” 22 ሐናም ልቅሶዋን ተወች። |