ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ጦቢት 4 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ጦቢት ለልጁ የሰጠው ምክር 1 በዚያችም ቀን ጦቢት በሜዶን ክፍል በራጌስ ለገባኤል አደራ ስላስጠበቀው ብር አሰበ። 2 አስቦም እንዲህ አለ፥ “እነሆ ልሙት ብዬ ለመንሁ፤ እንግዲህ ልጄን ጦብያን ጠርቼ ሳልሞት የማልነግረው ለምንድን ነው?” 3 ጠርቶም እንዲህ አለው፥ “ልጄ በሞትሁ ጊዜ በመልካሙ ቅበረኝ፤ እናትህንም ጠብቃት፤ በሕይወትህም ዘመን ሁሉ አክብራት፤ የወደደችውንም አድርግላት፤ አታሳዝናትም። 4 ልጄ፥ በማኅፀን ባንተ ብዙ መከራ እንደ ተቀበለች አስብ፤ በሞተችም ጊዜ በእኔ ዘንድ ባንድ መቃብር ቅበራት። 5 ልጄ ሆይ! በዘመኑ ሁሉ ፈጣሪህ እግዚአብሔርን አስበው፤ በደልንና ትእዛዙን መካድን አትውደድ፤ በሕይወትህም ዘመን ሁሉ ጽድቅን ሥራ፤ በዐመፅ መንገድም አትሂድ። 6 ጽድቅን ከሠራሃት በመንገድህ ሁሉና በሠራኸው ሥራ ሁሉ ትከናወናለህ፤ ጽድቅንም ለሚሠሩዋት ሁሉ ይከናወንላቸዋል። 7 ከገንዘብህ ምጽዋት ስጥ፤ ምጽዋትንም በምትመጸውት ጊዜ በገንዘብህ አትንፈግ፤ ከድኃም ፊትህን አትመልስ። እግዚአብሔርም ፊቱን ከአንተ አይመልስም። 8 ባለህ መጠን የሚቻልህን ያህል ምጽዋት አድርግ። 9 ጥቂትም ቢሆን ለመስጠት አትፈር፤ ምጽዋት መስጠት መልካም ድልብን ታደልብልሃለችና። 10 ምጽዋት በመከራ ቀን ከሞት ታድናለችና፤ ወደ ጨለማም ከመሄድ ትጠብቅሃለችና። 11 ምጽዋትም ለሚያደርጋት ሁሉ በልዑል ፊት መልካም ስጦታ ናት። 12 “ልጄ! ራስህን ከዝሙት ጠብቅ፤ ከአባቶችህ ዘር ሁሉ አስቀድመህ ሚስት አግባ። ከዘመዶችህ ካልሆነች ከባዕድ ወገን ግን አታግባ። እኛ ከጥንት ጀምረው ከነበሩ ከነቢያት ከኖኅና ከአብርሃም ፥ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ልጆች ወገን ነንና፤ ልጄ ሆይ፥ ሁሉም ከአባቶቻቸው ትውልድ ሚስት እንዳገቡ አስብ፤ በልጆቻቸውም እንደ ተባረኩ፥ ዘሮቻቸውም ምድርን እንደ ወረሷት አስብ። 13 አሁንም ልጄ ሆይ፥ ባልንጀራህን ውደድ፤ በባልንጀራህ፥ በወገኖችህ ወንዶች ልጆችና በወገኖችህ ሴቶች ልጆች ልብህን አታስታብይ፤ ከእነርሱም ወገን ሚስት አግባ። ትዕቢት ባለችበት ዘንድ ውርደት አለችና፥ ብዙ ሁከትም አለና፤ ስንፍናም ባለችበት ዘንድ ችግር አለች፤ ታላቅ ድህነትም አለ፤ ስንፍና የረኃብ እናት ናትና። 14 የተገዛልህ ሁሉ ደመወዝ ባንተ ዘንድ አይደር፤ በጊዜው ስጠው እንጂ። ለእግዚአብሔር ብትገዛ ዋጋህ ይበዛልሃልና፤ ራስህን ዕወቅ፤ በሥራህና በጠባይህ ሁሉ ጠቢብ ሁን። 15 ለራስህ የምትጠላውን ለማንም አታድርግ፤ ለመስከርም ወይንን አትጠጣ፤ ከሰካራሞችም ጋር በጎዳና አትሂድ። 16 ከእህልህም ለተራበ፥ ከልብስህም ለተራቈተ ስጥ፤ ከተረፈህም ሁሉ ለምጽዋት አድርግ። 17 እህልህንም በጻድቃን መቃብር ላይ ዝራ፤ ለኀጥኣን ግን አትስጥ። 18 በጠቢባን ዘንድ ምክርን ፈልግ፤ የምትረባህንም ምክር አታቃል። 19 በየጊዜውም ፈጣሪህ እግዚአብሔርን አመስግነው፤ ጎዳናህም የቀና ይሆን ዘንድ ወደ እርሱ ጸልይ፤ በሥራህ ሁሉና በጎዳናህ ሁሉ ያከናውንልሃል። በጎውን ሁሉ ከሚሰጥ ከእርሱ ከእግዚአብሔር በቀር ከእግዚአብሔር ያልሆነ አሕዛብ ሁሉ የሚመክሩት ምክር ከንቱ ነውና። የወደደውን ያዋርደዋል፤ እርሱም እንደ ወደደ ይሆናል። አሁንም ልጄ ሆይ ትእዛዜን አስብ፤ ከልብህም አይጥፋ። ጦቢት ለገባኤል አደራ ስለ ሰጠው ገንዘብ 20 “አሁንም በሜዶን ክፍል በራጊስ ሰው በግብርያል ልጅ በገባኤል ዘንድ አደራ ስላስጠበቅሁት ስለ ዐሥሩ የብር መክሊት እነግርሃለሁ። 21 ልጄ ሆይ! ከድህነት የተነሣ አትፍራ። ድሆች ባንተ ዘንድ ብዙ በረከትን ይቀበላሉና፥ እግዚአብሔርን ብትፈራው ከኀጢአትም ሁሉ ብትርቅ እግዚአብሔርንም ደስ የሚያሰኘውን ሥራ በፊቱ ብታደርግ ብዙ በረከት ባንተ ዘንድ ይኖራል።” |