ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ጦቢት 3 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የጦቢት ጸሎት 1 ከዚህም በኋላ በልብ ጭንቀት ተከዝሁ፤ አልቅሼም ጸለይሁ። 2 እንዲህም አልሁ፥ “አቤቱ በሥራህ ሁሉ በቸርነትና በፍርድ፥ በሚገባ ጽድቅም አንተ እውነተኛ ነህ፤ አቤቱ አንተ በሚገባ ዓለምን ትገዛለህ። 3 አስበኝ፤ ተመልከተኝም፤ በራሴ ኀጢአትና አንተን በበደሉ፥ ትእዛዝህንም ባልሰሙ በአባቶች ኀጢአት አትበቀለኝ። 4 ለመበርበርና ለመማረክ፥ ለመገደልም አደረግኸን፤ በዓለሙ ሁሉና በውስጣቸው በተበተንባቸው በአሕዛብም ዘንድ መተረቻና መዘባበቻ ሆንን። 5 አሁንም እውነተኛ ፍርድህ ብዙ ነው፤ የእኔ ኀጢአትና የአባቶች ኀጢአትም እንዲሰረይ አድርግልኝ፤ ትእዛዝህን አላደረግንምና፥ በፊትህም በእውነት አልሄድንምና። 6 አሁንም በፊትህ ደስ የሚያሰኝህን በእኔ አድርግ፤ ከመኖር መሞት ይሻለኛልና በሞት እሰናበት ዘንድ፥ መሬትም እሆን ዘንድ ነፍሴን የሚቀበላትን እዘዝልኝ። በሐሰትና በውርደት ተግዳሮትን ሰምቻለሁና፥ ኀዘንም በእኔ ላይ በዝትዋልና ከመከራዬ እሰናበት ዘንድ፥ ወደ ዘለዓለማዊ ቦታም እሄድ ዘንድ እዘዝ፤ ፊትህንም ከእኔ አትመልስ።” 7 በዚያችም ቀን በሜዶን ክፍል በጣኔስ የራጉኤል ልጅ ሣራን ከአባትዋ ሴቶች አገልጋዮች ተግዳሮት አገኛት። 8 ለሰባት ወንዶች አጋብተዋት እንደ ወንድና ሴት ሳይቃረቡ አስማንድዮስ የሚባል ክፉ ጋኔን ገድሏቸዋልና፤ እንዲህም አሏት፥ “ባሎችሽ እየታነቁ እንደሚሞቱ አታውቂምን፦ እነሆ ሰባቱ አገቡሽ፤ ከእነርሱም አንዱ ስንኳ አልተከተለሽም። 9 እንግዲህ ስለ እነርሱ ምን አሳዘነን? እነርሱ ሞተዋልና ከእነርሱ ጋር ሂጂ፤ ከአንቺ ወንድ ወይም ሴት ልጅ እስከ ዘለዓለሙ ድረስ አንይ።” 10 ይህንም በሰማች ጊዜ ለመታነቅ እስከምትመኝ ድረስ እጅግ አዘነች። እንዲህም አለች፥ “እኔ ለአባቴና ለእናቴ አንዲት ነኝ፤ እንደዚህም ባደርግ ተግዳሮት እሆንበታለሁ፤ ሽምግልናውንም፥ ሰውነቱንም በጭንቅ ወደ መቃብር አወርዳታለሁ።” የሣራ ጸሎት 11 በመስኮቱም በኩል ጸለየች፤ እንዲህም አለች፥ “አቤቱ አንተ ፈጣሪዬ ቡሩክ ነህ፤ ቅዱስና ክቡር ስምህም ለዘለዓለም ይመስገን፤ ሥራህም ሁሉ ለዘለዓለሙ ክቡር ነው። 12 አቤቱ አሁንም ዐይኖችንና ፊቴን ለአንተ ሰጠሁ። 13 እንግዲህ ወዲህ ተግዳሮትን እንዳልሰማ ከዚህ ዓለም አሰናብተኝ አልኹህ። 14 ከወንድ ጋር ከሚሠራው ኀጢአት ሁሉ እኔ ንጽሕት እንደ ሆንኹ አቤቱ አንተ ታውቃለህ። 15 በተማረክሁበትም ሀገር ስሜንና ያባቴን ስም አላሳደፍሁም፤ እኔም ለአባቴ አንዲት ነኝ። ወንድም የለኝም፤ ሚስት እሆንለት ዘንድ የምጠብቀው የቅርብ ዘመድም የለኝም፤ ሰባቱ ባሎች ሙተውብኛልና እንግዲህ ለምን እኖራለሁ? ልትገድለኝ ባትወድ ግን ወደ እኔ ተመልክተህ ራራልኝ፤ ተግዳሮትንም እንዳልሰማ እዘዝልኝ።” 16 የሁለቱም ጸሎታቸው በእግዚአብሔር በገነነ ጌትነቱ ፊት ተሰማ። 17 ሩፋኤልንም ላከው፤ ሁለቱን ያድናቸው ዘንድ፥ ከጦቢትም ዐይን ብልዙን ያጠፋለት ዘንድ፥ የራጉኤል ልጅ ሳራንም ሚስት ልትሆነው ለጦቢት ልጅ ለጦብያ ይሰጣት ዘንድ፥ ክፉ ጋኔን አስማንድዮስንም ይሽረው ዘንድ፥ ጦብያ ይወርሳታልና። በዚያም ወራት ጦቢት ተመልሶ ወደ ቤቱ ገባ፤ የራጉኤል ልጅ ሳራም ከሰገነቷ ወረደች። |