ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ጦቢት 2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ወደ ሀገሬም በተመለስሁ ጊዜ ሚስቴን ሐናንና ልጄን ጦብያን መለሰልኝ። በሰባተኛው ሱባኤ በተቀደሰችው የበዓለ ኀምሳ ዕለት ለእኔ መልካም ነገር አደረጉልኝ፤ እበላም ዘንድ ተቀመጥሁ። 2 ምግቡም እጅግ ብዙ እንደ ሆነ ባየሁ ጊዜ ልጄን እንዲህ አልሁት፥ “ሄደህ ከወንድሞቻችን ያገኘሃቸውን ድኆች ባልንጀሮችን አምጣ። እግዚአብሔርን አስቤዋለሁና። እነሆ እኔም እጠብቅሃለሁ።” 3 በተመለሰ ጊዜም እንዲህ አለኝ፥ “አባቴ! ከወገኖቻችን የተገደለ አንድ ሰው አገኘሁ፤ ሬሳውም በገበያ ወድቆአል።” 4 እኔም እህል ሳልቀምስ ተነሣሁ፤ ፀሐይም እስኪገባ ድረስ ወደ አንዱ ቤት አገባሁት። 5 ወደ ቤቴም ተመልሼ ታጥቤ ምግቤን በኀዘን በላሁ። 6 አሞፅም፥ “በዓላችሁ ወደ ኀዘን፥ ደስታችሁም ወደ ልቅሶ ይመለሳል” ያለውን አስታወስሁ። 7 ከዚህም በኋላ አለቀስሁ፤ ፀሐይም በገባ ጊዜ ሄጄ መቃብር ቆፍሬ ቀበርሁት። 8 ጎረቤቶችም ሳቁብኝ፤ እንዲህም አሉ፥ “ይህ ሰው ስለዚህ ሥራ እገደላለሁ ብሎ አይፈራምን? ንጉሥ የገደላቸውን ይቀብራልና።” የጦቢት ዐይን እንዴት እንደ ታወረ 9 በዚያችም ሌሊት ከቀብር ተመለስሁ፤ ረክሼም ስለነበር በዕድሞው ሥር አደርሁ፤ ዓይኖች ግን ተገልጠው ነበር። 10 በዕድሞው ላይም ወፎች እንዳሉ አላወቅሁም፤ ፊቴም ተገልጦ ሳለ እነዚያ ወፎች በዐይኔ ላይ የሚያቃጥል ኩስ ጣሉብኝ፤ በዐይኔም ብልዝ ወጣብኝ፤ እኔም ወደ ባለ መድኀኒት ሄድሁ፥ ነገር ግን የጠቀመኝ የለም፤ ብቻዬን ወደ ኤልማድያ እስክሄድ ድረስ አኪአክሮስ ይመግበኝ ነበር። 11 ሐናም በሴቶች ቤት ታገለግል ነበር። 12 ወደ እመቤቶችዋም ላከች፤ እነርሱም ደመወዟን ሰጧት፤ የበግ ጠቦትም ጨመሩላት። 13 ወደ እኔም በመጣች ጊዜ ትጮህ ጀመር፤ እኔም እንዲህ አልኋት፥ “ይቺ ጠቦት ከወዴት ናት? የሰረቅሻት ከሆነችም ወደ ጌቶችዋ መልሻት። የተሰረቀ መብላት አግባብ አይደለምና።” 14 እርሷም አለችኝ፥ “በደመወዜ ላይ ሰጡኝ፤” እኔ ግን አላመንኋትም፤ ለባለቤቶቹም መልሺ ብዬ ከእርሷ ጋር ተከራከርሁ፤ እርሷም መልሳ፥ “ጸሎትህና ምጽዋትህ ወዴት ነው? እነሆ በላይህ ያለው ሁሉ ታወቀ” አለችኝ። |