ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ጦቢት 1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ከንፍታሌም ነገድ ከአሳሄል ወገን የገባኤል ልጅ የጦብኤል ልጅ የጦቢት የነገሩ መጽሓፍ ይህ ነው። 2 እርሱም፦ ከአሴር በላይ ካለች ከገሊላ ንፍታሌም ክፍል ከቄዴዎስ በስተቀኝ ካለችው ከታስቢ በአሦር ንጉሥ በአሜኔሴር ዘመን የተማረከው ነው። የጦቢት መልካም ሕይወት 3 እኔ ጦቢት በሕይወቴ ዘመን በጽድቅና በቅንነት መንገድ ሄድሁ፤ ወደ አሶር ከተማ ወደ ነነዌ ከእኔ ጋር ለመጡ ወንድሞችና ወገኖች ብዙ ምጽዋትን አደረግሁ። 4 እኔም ሕፃን ሆኜ ከእስራኤል ልጆች ጋር በሀገሬ ሳለሁ የአባቴ የንፍታሌም ወገኖች ሁሉ፥ እስራኤልም ሁሉ በእርሷ ይሠዉ ዘንድ እግዚአብሔር ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ከመረጣት የልዑል ቤተ መቅደስ ለትውልድ ሁሉ ለዘለዓለም ከታነጸባትና ከተቀደሰባት ከኢየሩሳሌም ወጥተው ካዱ። 5 የካዱ ሰዎችም ሁሉ ደማሊ ለሚባል ጣዖት ሠዉ፤ የአባቴም የንፍታሌም ወገኖች ሁሉ ከእነርሱ ጋር ተባበሩ። 6 እኔ ግን በዘለዓለማዊ ትእዛዝ ለእስራኤል ሁሉ እንደ ተጻፈ በበዓላት ቀን ብቻዬን ብዙ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም እሄድ ነበር፤ በመጀመሪያም ከሸለትሁት ከበጎች ፀጕር ለአሮን ልጆች ለካህናቱ ወደ መሠዊያው እወስድላቸው ነበር። 7 እህሉንና መጀመሪያውን ዐሥራት ሁሉ በኢየሩሳሌም ለሚያገለግሉ ለአሮን ልጆች እሰጣቸው ነበር፤ ሁለተኛውን እጅ ዐሥራት ግን እሸጠው ነበር፤ ምጽዋቱንም አውጣጥቼ በየዓመቱ ወደ ኢየሩሳሌም እሄድ ነበር። 8 ሦስተኛውንም እጅ ዐሥራት የአባቴ እናት ዲቦራ እንዳዘዘች ለድሆች እሰጥ ነበር። አባቴና እናቴ በድኃአደግነት ትተውኛልና፤ 9 አካለ መጠን ባደረስሁም ጊዜ ከዘመዶች ዘር ሚስት አገባሁ፤ ከርስዋም ጦብያን ወለድሁ። የጦቢት ወደ ነነዌ መማረክ 10 ወንድሞችና ዘመዶች ሁሉ ወደ ነነዌ በተማረኩ ጊዜ ከአሕዛብ እህል በሉ። 11 እኔ ግን የአሕዛብን እህል እንዳልበላ ሰውነቴን ጠበቅሁ፤ 12 እግዚአብሔርን በፍጹም ልቡናዬ አስበዋለሁና። 13 እግዚአብሔርም በአሜኔሴር ፊት ክብርንና ባለሟልነትን ሰጠኝ፤ እርሱም መጋቢ አድርጎ ሾመኝ። 14 ወደ ምድያምም ሄድሁ፤ በምድያም ክፍል በራጊስ ያለ የጋብርያስ ወንድም ገባኤልንም ዐሥር መክሊት አደራ አስጠበቅሁት። 15 አሚኔሴርም በሞተ ጊዜ በእርሱ ፋንታ ልጁ ሰናክሬም ነገሠ፤ ሥራውም ክፉ ነበር፤ ከሹመቴም ሻረኝ፤ እንግዲህም ወዲህ ወደ ምድያም መሄድን አልቻልሁም። የጦቢት መልካም ሥራ 16 በአሚኔሴርም ዘመን ለወንድሞች ብዙ ምጽዋትን አደረግሁ። 17 እህሌንም ለተራቡ፥ ልብሴንም ለተራቆቱ ሰጠሁ። ከወገኖችም የሞተ ሰውን በነነዌ ግንብ ሥር ወድቆ ባየሁ ጊዜ እቀብረው ነበር። 18 ንጉሥ ሰናክሬም ከይሁዳ ሸሽቶ በተመለሰ ጊዜ የገደላቸውን ሰዎች እኔ በስውር እቀብራቸው ነበር። እርሱ ተቈጥቶ ብዙዎችን ገድሎ ነበርና። ንጉሡም ሬሳቸውን አስፈለገ፥ አላገኘምም። 19 ከነነዌ ሰዎችም አንዱ ሰው ሄዶ እንደ ቀበርኋቸው ነገር ሠርቶ ከንጉሡ ጋር አጣላኝ፤ እኔም ተሰወርሁ፤ ሊገድሉኝ እንደሚፈልጉኝም ባወቅሁ ጊዜ ፈርቼ ገለል አልሁ። 20 ባጡኝም ጊዜ ገንዘቤን ሁሉ ዘረፉኝ፤ ከሚስቴ ሐናና ከልጄ ጦብያ በቀር ያስቀሩልኝ የለም። 21 ሁለቱ ልጆቹ እስኪገድሉት ድረስ፥ ሸሽተውም ወደ አራራት ተራራ እስኪሄዱ ድረስ አምሳ አምስት ቀን ከቤቴ አልወጣሁም። ልጁ አስራዶንም በእርሱ ፋንታ ነገሠ፤ የወንድሜ ልጅ የአናሔል ልጅ አኪአኪሮስንም በአባቱ ቤት ሁሉና በሥራታቸው ሁሉ ላይ ሾመው። 22 አኪአኪሮስም ማለደልኝ፤ ወደ ነነዌም መለሰኝ። አኪአኪሮስም የማኅተምና የቤቱ ንብረት ጠባቂ ነበር። አስራዶንም ዳግመኛ ሾመው። |