ማሕልየ መሓልይ 4 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ወዳጄ ሆይ፥ እነሆ፥ ውብ ነሽ፤ እነሆ፥ አንቺ ውብ ነሽ፤ ከዝምታሽ በቀር ዐይኖችሽ እንደ ርግቦች ናቸው፤ ጠጕርሽ በገለዓድ ተራራ እንደሚታይ እንደ ፍየል መንጋ ነው። 2 ጥርሶችሽ ከመታጠቢያ ወጥተው እንደ ተሸለቱ ሁሉም መንታ መንታ እንደ ወለዱ ከእነርሱም መካን እንደሌለባቸው መንጎች ናቸው። 3 ከንፈሮችሽ እንደ ቀይ ሐር ፈትል ናቸው፥ ቃልሽም ያማረ ነው፤ ከዝምታሽ በቀር ጕንጮችሽ እንደ ተከፈለ ሮማን ናቸው። 4 አንገትሽ ለሰልፍ ዕቃ መስቀያ እንደ ተሠራ እንደ ዳዊት ግንብ ነው፤ በውስጡም ሺህ የጦር ዕቃና የኀያላን መሣሪያ ሁሉ ተሰቅሎበታል። 5 ሁለቱ ጡቶችሽ መንታ እንደ ተወለዱ፥ በሱፍ አበባ መካከል እንደሚሰማሩ እንደ ሚዳቋ ግልገሎች ናቸው። 6 ቀኑ እስኪነፍስ ጥላውም እስኪያልፍ ድረስ፥ ወደ ከርቤው ተራራ ወደ ዕጣኑም ኰረብታ እሄዳለሁ። 7 ወዳጄ ሆይ፥ ሁለንተናሽ ውብ ነው፥ ምንም ነውር የለብሽም። 8 ሙሽሪት ሆይ፥ ከሊባኖስ ነዪ፤ ከሊባኖስ ነዪ፤ ከሃይማኖት ራስ ከሳኔርና ከኤርሞን ራስ፥ ከአንበሶች ጕድጓድ፥ ከነብሮችም ተራራ ተመልከቺ። 9 እኅቴ ሙሽሪት ሆይ፥ ልቤን ማረክሽው፤ አንድ ጊዜ በዐይኖችሽ፥ ከአንገትሽም ድሪ በአንዱ፥ ልቤን ማረክሽው። 10 እኅቴ ሙሽሪት ሆይ፥ ጡቶችሽ እንዴት ያማሩ ናቸው? ጡቶችሽ ከወይን ይልቅ እጅግ ያማሩ ናቸው። የሽቱሽም መዓዛው ከሽቱ ሁሉ ይልቅ እጅግ ያማረ ነው። 11 ሙሽሪት ሆይ፥ ከከንፈሮችሽ የማር ወለላ ይንጠባጠባል፤ ከምላስሽም በታች ማርና ወተት አለ፥ የልብስሽም መዓዛ እንደ ዕጣን መዓዛ ነው። 12 እኅቴ ሙሽሪት የተቈለፈች ገነት፥ የተዘጋች ገነት፥ የታተመችም ጕድጓድ ናት። 13 መንገድሽም ሮማንና የተመረጠ ፍሬ፥ ቆዕ ከናርዶስ ጋር ያለበት ገነት ነው፥ 14 ናርዶስ ከቀጋ ጋር፥ የሽቱ ሣርና ቀረፋም፥ ከሊባኖስ እንጨቶች ጋር፥ ከርቤና እሬት ከክቡር ሽቱ ሁሉ ጋር። 15 አንቺ የገነት ምንጭ፥ የሕይወት ውኃ ጕድጓድ፥ ከሊባኖስም የሚፈስስ ወንዝ ነሽ። 16 የሰሜን ነፋስ ሆይ፥ ተነሥ፥ የደቡብም ነፋስ ና፤ በገነቴ ላይ ንፈስ፥ ሽቱዬም ይፍሰስ፤ ልጅ ወንድሜ ወደ ገነቱ ይውረድ፥ መልካሙንም ፍሬ ይብላ። |