ማሕልየ መሓልይ 2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 እኔ የዱር ጽጌረዳ፥ የቈላም የሱፍ አበባ ነኝ። 2 በእሾህ መካከል እንዳለ የሱፍ አበባ፥ እንዲሁ ወዳጄ በቈነጃጅት መካከል ነሽ። 3 በዱር እንዳለ እንኮይ፥ እንዲሁ ውዴ በወንድሞች መካከል ነው። ከጥላው በታች እጅግ ወድጄ ተቀመጥሁ፥ ፍሬውም ለጕሮሮዬ ጣፋጭ ነው። 4 ወደ ወይን ቤት አገቡኝ፥ በእኔም ላይ ፍቅርን አደረጉ። 5 በሽቱ አጸኑኝ፥ በእንኮይም አበረታቱኝ፥ በፍቅሩ ተነድፌአለሁና። 6 ቀኙ ታቅፈኛለች። ግራውም ከራሴ በታች ናት፥ 7 እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ ወድዶ እስኪነሣ ድረስ፥ ፍቅሬን እንዳትቀሰቅሱትና እንዳታስነሡት፥ በምድረ በዳው ኀይልና ጽናት አምላችኋለሁ። 8 እነሆ፥ የልጅ ወንድሜ ቃል በተራሮች ላይ ሲዘልል፥ በኮረብቶችም ላይ ሲወረወር ይመጣል። 9 ልጅ ወንድሜ በቤቴል ተራሮች ላይ ሚዳቋን ወይም የዋሊያን እንምቦሳ ይመስላል፤ እነሆ፥ በመስኮቶች ሲጐበኝ፥ በዐይነ ርግብም ሲመለከት፥ እርሱ ከቅጥራችን በኋላ ቆሞአል። 10 ልጅ ወንድሜ እንዲህ ብሎ መለሰልኝ፦ ወዳጄ ሆይ፥ ተነሺ፥ መልካምዋ ርግቤ ሆይ፥ ነዪ። 11 እነሆ፥ ክረምቱ ዐለፈ፥ ዝናሙም አልፎ ሄደ፤ 12 አበባ በምድር ላይ ታየ፥ የመከርም ጊዜ ደረሰ፥ የቍርዬውም ቃል በምድራችን ተሰማ። 13 በለሱ ጐመራ፥ ወይኖችም አበቡ፥ መዓዛቸውንም ሰጡ፤ ወዳጄ ሆይ፥ ተነሺ፤ መልካምዋ ርግቤ ሆይ፥ ነዪ። በዐለት ንቃቃትና በገደል መሸሸጊያ ወዳለው ጥላ ነዪ። 14 ፊትህን አሳየኝ፥ ቃልህንም አሰማኝ፤ ቃልህ ያማረ፥ ፊትህም የተዋበ ነውና። 15 የወይን ቦታችን ያብብ ዘንድ፥ የወይናችንን ቦታ የሚያጠፉትን ጥቃቅኑን ቀበሮች አጥምዳችሁ ያዙልን። 16 ልጅ ወንድሜ የእኔ ነው፥ እኔም የእርሱ ነኝ፤ በሱፍ አበባዎች መካከልም መንጋውን ያሰማራል። 17 ልጅ ወንድሜ ሆይ፥ ቀኑ እስኪነፍስ፥ ጥላውም እስኪሸሽ ድረስ ተመለስ፤ በቅመም ተራራ ላይ ሚዳቋውን ወይም የዋላውን እንቦሳ ምሰል። |