ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 8 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 በእጃቸው እንዳትወድቅ ከታላላቆች ሰዎች ጋር አትከራከር። 2 በብልጽግናው ድል እንዳያደርግህ ከባለጸጋ ጋር አትጣላ፥ ብዙዎች ስለ ወርቅ ጠፍተዋልና፤ የነገሥታትም ልቡና ድል ሆኖአልና። 3 ከተናጋሪ ሰውም ጋር አትከራከር፤ ያለዚያ በእሳት ላይ እንጨት መከመርህ ነው። 4 እናትና አባትህን እንዳታዋርድ፥ ከአላዋቂ ሰው ጋር አትሣቅ። 5 ከኀጢአቱ የተመለሰውን ሰው አትንቀፈው፤ እኛ ሁላችንም ኀጢአተኞች እንደሆን ዐስብ። 6 በርጅናው ጊዜ ሰውን አታቅልለው፥ ከእኛ የማያረጅ የለምና። 7 በሞተ ሰው ደስ አይበልህ፤ ሁላችንም እንደምንሞት ዐስብ። 8 የብልሆችን ነገር አታቃልል፤ ጥበብን በእነርሱ ዘንድ ታገኛለህና፥ ምሳሌያቸውን ተማር። መምህራንንም አገልግል። 9 የሽማግሎችን ምክራቸውን ጠብቅ፤ እነርሱ ከአባቶቻቸው ተምረዋልና አንተም ከእነርሱ ተማር፤ በኀዘንህም ጊዜ የምትናገረውን ታገኛለህ የምትመልሰውንም ታውቃለህ። 10 በእሳታቸው እንዳትቃጠል፥ የኀጢአተኞች ሰዎችን እሳት አትጫር። 11 በአንደበቱ ነገር እንዳያስትህ፥ በተሳዳቢና በጠላት ዘንድ አትከራከር። 12 ከአንተ ለሚበለጽገው አታበድረው፤ ብታበድረው ግን ገንዘብህን እንዳጣህ ዕወቅ። 13 ከአንተ ለሚበረታውም አቷሰው፤ ብቷሰው ግን አንተ ራስህ እንደምትከፍል ዐስብ። 14 ከዳኛ ጋር አትከራከር፥ እንደ ክብሩ መጠን ፍርድን ይለውጡለታልና፤ 15 እንዳይደፍርህ ከደፋር ሰው ጋራ መንገድን አትሂድ፤ እርሱ ልቡ እንደ ወደደ ያደርጋልና አንተም በእርሱ ስንፍና ትሞታለህ። 16 ከቍጡ ሰው ጋር አትከራከር፤ በእርሱ ዘንድ ደም ማፍሰስ እንደ ኢምንት ነውና፥ ረዳት ወደሌለበት ቦታም ይወስድሃልና ከእርሱ ጋር ወደ ምድረ በዳ አትውጣ። 17 የሰማውን ነገር መጠበቅ አይችልምና፥ ከአላዋቂ ሰው ጋራ አትማከር። 18 እንዴት እንደሚደርስብህ አታውቅምና፥ ጉዳይህን በባዕድ ፊት አትናገር። 19 ዋጋህ እንዳይጠፋብህ፥ ለሰው ሁሉ የልብህን ምሥጢር አትግለጥ። |