ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 51 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የሲራክ ልጅ የኢያሱ ጸሎት 1 አቤቱ ንጉሥ ሆይ! እገዛልሃለሁ፤ አቤቱ! አምላኬና መድኀኒቴ አመሰግንሃለሁ፤ በስምህም እታመናለሁ፤ 2 ረድተኸኛልና፥ ሰውረኸኝማልና፥ ሰውነቴንም ከሞት አድነኸዋልና፥ ከአንደበት የነገር ሥራ ወጥመድም አድነኸኛልና፥ ሐሰትንም ከሚሠሩአት ከብዙ ሰዎች ምላስ አድነኸኛልና፥ በጠላትነትም ከተነሡብኝ ሰዎች ፊት የምትረዳኝና የምትሰውረኝ ሆነሃልና። 3 እንደ ቸርነትህ ብዛት መጠን፥ ስለ ስምህም አዳንኸኝ፥ ይበሉ ዘንድ ያዘጋጁትን እንደሚያመሰኩ እንደዚሁ ባገኘችኝ በመከራዬ ብዛት ሰውነቴን ፈለጓት። 4 ቋያ እንደ ከበበው፥ በእሳት መካከልም እንደማይቃጠል፥ 5 ከታችም ከመቃብር ሆድ፥ ከረከሰ አንደበትም፥ ከሐሰት ቃልም፥ አዳንኸኝ፤ 6 ወደ ንጉሥ በሚያጣላ ዐመፀኛ አንደበት፥ ሰውነቴ ወደ ሞት ደረሰች፤ ሕይወቴም ለመቃብር ደረሰች። 7 በዙሪያዬም ከበቡኝ፤ የሚረዳኝም አጣሁ፤ የሚያድነኝ ሰው እንዳለ ብዬ ተመለከትሁ፥ ግን ማንም አልነበረም። 8 አቤቱ ይቅርታህን ዐሰብሁ፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የነበረ ሥራህን ዐሰብሁ፤ አንተን ተስፋ የሚያደርጉ ሰዎች፥ ከጠላታቸውም የምታድናቸው ብፁዓን ናቸውና። 9 ልመናዬንም ከምድር ወደ ላይ ከፍ ከፍ አደረግሁ፤ ከሞትም እድን ዘንድ ጸለይሁ። 10 አባቴና ጌታዬ እግዚአብሔርንም፥ ረዳት በሌለበት፥ ትዕቢተኞች በተነሡበት ወራት በመከራዬ ጊዜ አትለየኝ አልሁት። 11 ስምህንም ለዘለዓለም አመሰግናለሁ፤ እገዛልሃለሁ፤ ምስጋናህንም እናገራለሁ፤ ልመናዬንም ሰማኸኝ። 12 ከሞትም አዳንኸኝ፤ መከራ ከሚመጣበት ቀንም አዳንኸኝ፥ ስለዚህ ነገር እገዛልሃለሁ፥ አመሰግንሃለሁም። አቤቱ ስምህንም አመሰግናለሁ። 13 እኔ ሕፃን ሳለሁ ሳልሳሳት ጥበብን መረመርኋት፤ በጸሎቴም መረጥኋት። 14 በቤተ መቅደስም ስለ እርስዋ ለመንሁ፤ ለዘለዓለምም እመረምራታለሁ። 15 ፍሬዋም እንደ ተክል ፍሬ በዛ፤ ልቡናዬም በእርስዋ ደስ አለው፤ እግሬም በእውነት ቆመች፤ ከሕፃንነቴም ጀምሬ ፍለጋዋን ተከተልሁ። 16 በጆሮዬም ፈጽሜ አደመጥኋት፤ መረጥኋትም፤ እኔም ብዙ ጥበብን አገኘሁ። 17 በእርሷም ከፍ ከፍ አልሁ፤ ጥበብን የሰጠኝን እግዚአብሔርንም አመሰግነዋለሁ። 18 አደርጋትም ዘንድ ዐሰብሁ፤ ለበጎ ነገርም ቀናሁ፤ አላፍርምም። 19 ሰውነቴም በእርሷ ተበረታታች፤ በሥራዬም ተራቀቅሁ፤ እጆችንም ወደ ላይ አነሣሁ፤ ለድንቁርናዬም አለቀስሁላት። 20 ሰውነቴንም ወደ እርሷ አቀናሁ፤ በንጽሕናም አገኘኋት፤ ልቡናዬንም ከመጀመሪያ ጀምሮ ከእርስዋ ጋራ አጸናሁ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር አልጣለኝም። 21 ሰውነቴም ለእርስዋ ታወከች፤ መረመረቻትም፤ ስለዚህም መልካም ሀብትን ገንዘብ አደረግሁ። 22 እግዚአብሔርም አንደበትን ዋጋ አድርጎ ሰጠኝ፤ በእርስዋም አመሰግነዋለሁ። 23 እናንት አላዋቂዎች፥ ወደ እኔ ቅረቡ፤ በጥበብ ቤትም ትኖራላችሁ። 24 እንዴት አጣችኋት? እስኪ ንገሩኝ! ሰውነታችሁስ ፈጽማ እንደ ምን ተጠማች? 25 አፌን ከፍቼ፥ “ያለ ዋጋ ገንዘብ አድርጓት” ብዬ ተናገርሁ። 26 አንገታችሁን ዝቅ አድርጉ፤ ቀንበሯንም ተሸከሙ፤ ሰውነታችሁም ጥበብን ትቀበል፤ እርስዋን ማግኘት ቅርብ ነውና። 27 እነሆ፥ ጥቂት ደክሜ በእርሷ ብዙ ዕረፍትን እንዳገኘሁ፥ በዐይናችሁ ተመልከቱ። 28 ከብዙ ብር ይልቅ ጥበብን ምረጧት፤ ቍጥር ከሌለው ከወርቅም ይልቅ ገንዘብ አድርጓት። 29 ሰውነታችሁም በቸርነቱ ደስ ይበላት፤ እርሱንም ማመስገንን አትፈሩ። 30 በጊዜው ዋጋችሁን ይሰጣችሁ ዘንድ፥ ጊዜው ሳይደርስ ሥራችሁን ሥሩ። የሲራክ ጥበብ ተፈጸመ። |