ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 47 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ናታንና ዳዊት 1 ከእርሱም በኋላ ናታን ተነሣ፤ በዳዊትም ዘመን ትንቢት ተናገረ። 2 ስቡን ከድኅነቱ መሥዋዕት እንደሚለዩ እንደዚሁ ዳዊት ከእስራኤል ልጆች ተለየ። 3 በእርሱም ዘንድ አንበሳ እንደ ፍየል ጠቦት፥ ግስላም እንደ በግ ጠቦት ነበር። 4 በወጣትነቱ አርበኛን የገደለ አይደለምን? እጁንስ አንሥቶ ድንጋይ በወነጨፈ ጊዜ ጎልያድን ግንባሩን የመታው፥ ናላውንም የበጠበጠው አይደለምን? የሕዝቡንስ ተግዳሮት ያስወገደ አይደለምን? 5 ልዑል እግዚአብሔርን ለምኖታልና በሰልፍ ኀይለኛውን ሰው ይገድል ዘንድ የወገኖቹንም ቀንድ ያጸና ዘንድ በቀኝ እጁ ኀይልን ሰጠው። 6 ዘፋኞቹም ዳዊትን ዐሥር ሺህ ገዳይ አሉት፤ በእግዚአብሔርም በረከት አመሰገኑት፤ የክብር ዘውድንም ተቀዳጀ። 7 በዙሪያው ያሉ ጠላቶቹንም ቀጠቀጣቸው፤ ጠላቶቹ ፍልስጥኤማውያንንም አዋረዳቸው፤ እስከ ዛሬም ድረስ ቀንዳቸውን ሰበረ። 8 በሚሠራው ሥራ ሁሉ ቅዱስና ልዑል እግዚአብሔርን በምስጋና ቃል አመሰገነ፤ በፍጹም ልቡም ፈጣሪውን አመሰገነው፤ ወደደውም። 9 በመሠዊያውም ፊት መዘምራንን መደበ፤ የቃላቸውም ዜማ ያማረና የጣፈጠ ነበር። 10 መልካም በዓልንም አደረገ፤ ዓመቱን ሁሉ ደስ አሰኘ፥ ቅዱስ ስሙንም አመሰገነው፤ ቅድስናውም ከነግህ ጀምሮ ይነገራል። 11 እግዚአብሔርም ኀጢአቱን አስተሰረየለት፤ ቀንዱንም ለዘለዓለሙ ከፍ ከፍ አደረገለት፤ የተባረከች መንግሥትን፥ የእስራኤልንም የክብር ዙፋን ሰጠው። ስለ ንጉሥ ሰሎሞን 12 ከእርሱም በኋላ ጠቢብ የሆነ ልጁ ተተካለት ስለ እርሱም በስፋት ኖረ። 13 ሰሎሞንም በሰላም ዘመን ነገሠ፥ እግዚአብሔርም በዙሪያው ካሉት ሁሉ አሳረፈው፤ በስሙ ቤትን ሠራ፤ የዘለዓለም መቅደሱንም አዘጋጀ። 14 ሰሎሞን ሆይ፥ ከሕፃንነትህ ጀምሮ ጥበብህ እንዴት በዛ፤ ማስተዋልህም እንደ ፈሳሽ ውኃ ሞላ። 15 ጥበብህ ምድርን ሸፈነቻት፥ ምሳሌህን፥ የነገርህንም ትርጓሜ አበዛህ። 16 ስምህም እስከ ሩቅ ደሴት ድረስ ተሰማ፤ ስለ ሰላምህም ተወደድህ። 17 ሀገሮችም ስለ መዝሙርህ፥ ስለ ምሳሌህ፥ ስለ እንቆቅልሾችህና ስለ ትርጓሜዎችህ አደነቁህ። 18 የእስራኤል አምላክ በተባለ በእግዚአብሔር ስም፥ ወርቁንም እንደ እርሳስ አደለብኸው፤ ብርንም እንደ ማዕድን ቅልቅል መላኸው። 19 ሴቶች ልቡናህን ለወጡት፤ በሥጋህም ሠለጠኑብህ። 20 ክብርህን አስነቀፍህ፤ ዘርህንም አሳደፍኽ፤ በልጆችህም ላይ መቅሠፍትንና ጥፋትን አመጣህ፤ ስንፍናህም አስደነገጠኝ። 21 መንግሥትህም ተከፈለ፤ ዐመፀኛ መንግሥትም ከኤፍሬም ወጣች። 22 እግዚአብሔር ግን ቸርነቱን አልተወም፤ ሥራውንም አላጠፋም፤ የጻድቃኑንም ልጆች አልደመሰሰም፤ የሚወዱትንም ሰዎች ዘር አላጠፋም፤ ለያዕቆብም ቅሬትን ሰጠው፥ ከእርሱም ለዳዊት ሥርን ሰጠው። ሮብአምና ኢዮርብአም 23 ሰሎሞንም እንደ አባቶቹ አረፈ ከእርሱም በኋላ አእምሮ የሌለው ልጁን ለእስራኤል ተወ። ይኸውም ሕዝቡን በምክሩ ያሳመፃቸው ሮብዓም ነው። እስራኤልን ያሳታቸው፥ ለኤፍሬምም የኀጢአት መንገድን ያሳየ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ነበረ። 24 ኀጢአታቸውም ፈጽሞ በዛ፥ ከሀገራቸውም አስወጥቶ ሰደዳቸው። 25 ፍዳቸውም እስክትደርስባቸው ድረስ ኀጢአትን ሁሉ ፈለጓት። |