ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 42 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ነገር ግን ስለዚህ ነገር አትፈር፤ ስለ እግዚአብሔርም ሕግ በደል እንዳይሆንብህ የሰው ፊት አይተህ አታዳላ፤ 2 ስለ ልዑል ሕግና ስለ ቃል ኪዳኑ አትፈር፤ በደለኛውንም እንዳታነጻው ስለ ፍርድ አትፈር። 3 ከጓደኛህ ጋር ገንዘብህን በተሳሰብህ ጊዜ አትፈር፤ ስለ ዋጋህና ስለ ርስትህ አትፈር። 4 ስለ ሚዛንና ስለ ላዳንም ጥቂት ቢሆን፥ ብዙም ቢሆን ስለ ገንዘብህ አትፈር። 5 ስለሚረባህና ስለሚጠቅምህም ሁሉ አትፈር፤ ልጆችህንም ስለ ማስተማር አትፈር፤ ክፉ ባሪያንም ጎን ጎኑን ግረፈው። 6 በክፉ ሴት ላይ ቍልፍ መያዝ መልካም ነው፤ ብዙ እጆች ካሉበት ዘንድም በቍልፍ አኑር። 7 የምትሠራውን ሁሉ በቍጥር፥ በመስፈሪያና በሚዛን አድርግ፤ ያገባኸውና ያወጣኸው፥ የሰጠኸውና የተቀበልኸው ሁሉ በጽሑፍ ይሁንህ። 8 ሰነፍን ሰው፥ አእምሮ የሌለውንም ሰው፥ በእርጅናውም ወደ ዝሙት የሚሄድ ሽማግሌን ስለ መምከር አትፈር፤ ስለዚህ በሰው ሁሉ ዘንድ በእውነት ብልህና ዐዋቂ ትሆናለህ። 9 ሴት ልጅ ለአባትዋ ስውር የእንቅልፍ ዕጦት ናት፤ የወጣትነት ዕድሜዋ እንዳያልፍባት፥ ከተዳረችም በኋላ እንዳትጠላ፥ ስለ እርስዋ ማሰብ ዕንቅልፍን ያሳጣዋል፤ 10 በድንግልናዋ እንዳትደፈር፥ በአባቷም ቤት ፀንሳ እንዳትገኝ፥ ምንአልባትም ከባልዋ ጋር ሳለች እንዳትበድል፥ ካገባችም በኋላ መካን እንዳትሆን፥ 11 የጠላት መዘባበቻ፥ በከተማም መነጋገሪያ፥ በሕዝቡም መካከል መሰደቢያ እንዳታደርግህ፥ በብዙ ሰዎች ፊትም እንዳታሳፍርህ የማታፍር ልጅን አጽንተህ ጠብቃት። 12 ለሰው ሁሉ ስለ መልኩ አታድላለት፤ በሴቶችም መካከል አትግባ፤ 13 ከልብስ ብል ይገኛል፤ ክፋትም ሁሉ ከሴቶች ይገኛል። 14 ኀፍረትንና ቅንዐትን ከምታመጣ ሴት ደግነት፤ የወንድ ክፋት ይሻላል። የእግዚአብሔር ክብር በፍጥረቱ 15 እንግዲህ ወዲህ ግን የእግዚአብሔርን ሥራ አስባለሁ፤ ያየሁትንም እናገራለሁ፤ ፍጥረት ሁሉ በእግዚአብሔር ቃል ተፈጥሯልና። 16 ፀሐይ ያበራል፤ ሁሉንም ያሳያል፤ የእግዚአብሔርም ጌትነት በሥራው ሁሉ ላይ ምሉእ ነው። 17 ሁሉ በክብሩ ይጸና ዘንድ፥ ሁሉን ቻይ እግዚአብሔር ያጸናውን አላደረገምን? 18 ጥልቅንና ልብን መርምሮ ያውቃቸዋል፤ ምክራቸውንም ሁሉ ያውቃል፤ እግዚአብሔር የልቡና አሳብን ሁሉ ያውቃል፤ የዓለምንም ምልክት ያያል። 19 ያለፈውንም፥ የሚመጣውንም እርሱ ይናገራል፤ የተሰወረውንም ፍለጋ ይገልጣል። 20 ከምክርም ሁሉ የሚያመልጠው የለም፤ ከነገሩ ሁሉ አንድ ቃል ስንኳ የሚሰወረው የለም። 21 የጥበቡን ገናናነት አስጌጠ። ይህቺም ዓለም ሳይፈጠር የነበረች ናት፥ ለዘለዓለሙም ትኖራለች፤ አትጨምርም፤ አትጐድልምም፤ አንድ መካርን ስንኳ አይፈልግም። 22 ሥራው ሁሉ ያማረ ነው፤ ለማየትም እንደ ብርሃን ነው፤ 23 ይህ ሁሉ ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ ይኖራል፤ ለጥቅም በሚፈልጉት ጊዜ ይሰማል። 24 ሁሉም አንዱ የሌላው ተቃራኒ በመሆን ሁለት ሁለት ናቸው፤ ምንም ነጠላ አድርጎ የፈጠረው የለም። 25 ለመልካም ነገር አንዱን ከሁለተኛው ጋር አጸናው፤ ክብሩን ከማየት ማን ይጠግባል? |