ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 40 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የሰብአዊ ሕይወት ችግር 1 የሰው የተፈጥሮው መከራ ታላቅ ነው፤ ከእናታቸው ማኅፀን ከሚወጡበት ጀምሮ በሁሉ እናት ሆድ እስኪቀበሩ ድረስ በአዳም ልጆች ላይ ከባድ ሸክም አለ። 2 ዕለተ ሞትን ማሰብ በአዳም ልጆች ሁሉ ላይ የምታስደነግጥና ልብንም የምታስፈራ ናት። 3 በመንግሥት ዙፋን ከሚቀመጥ ንጉሥ ጀምሮ በዐመድና በትቢያ ላይ እስከሚተኛ ድሃ ድረስ፥ 4 ቀይ ግምጃ ከሚለብስና ዘውድ ከሚቀዳጅ ጀምሮ የተናቀ ልብስን እስከሚለብስ ድረስ፥ 5 ቍጣና ቅንዓት፥ ንዝንዝና ሁከት፥ ሞትን መፍራትና ክርክር፥ ሐሜትም አለ፤ በመኝታው በተኛ ጊዜ የሌሊት እንቅልፍ አሳቡን ይለውጠዋል። 6 ዕረፍቱ ጥቂት ወይም እንደ ኢምንት ነው፤ ይህ ሁሉ በመኝታው ይታወቃል፤ አንድ ጊዜ እንደ ሸንጎ ተከማችቶ ያገኘዋል፤ ከሰልፍ እንደሚሸሽ ሰውም የልቡናውን ምክር ያወላውላታል። 7 የሸሸው ሰው ግን ዕለቱን ያመልጣል፤ ፍርሀቱንም እርሱ ራሱ ያደንቃታል፤ 8 ይህ ሁሉ በሰው ላይ እስከ እንስሳ ድረስ አለ፤ ይህም በኀጢአተኞች ሰዎች ላይ ሰባት እጥፍ ይብሳል። 9 ሞትና መታበይ፥ ቸነፈርና ጦርነት፥ ቀጠናና የልብ ቍስል፥ መቅሠፍትም። 10 ይህ ሁሉ በኀጢአተኛ ስዎች ላይ ተፈጠረ፤ በእነርሱም ምክንያት የጥፋት ውኃ መጣ። 11 ሁሉ ከምድር ተፈጠረ፤ ሁሉም ወደ ምድር ይመለሳል፤ የወንዙ ውኃ ሁሉ ወደ ውቅያኖስ ይመለሳል። የክፋት ውጤት 12 መማለጃና ዐመፃ ሁሉ ይደመሰሳሉ፤ ሃይማኖት ግን ለዘለዓለሙ ትጸናለች። 13 የዐመፃ ገንዘብ እንደ ፈሳሽ ውኃ ይደርቃል፤ በዘነበም ጊዜ እንደ ታላቅ መብረቅ ጩሆ ይጠፋል። 14 እርሱ እጁን ከዘረጋ ደስ ያሰኛል፤ የሚክዱት ሰዎች ግን ፈጽመው ይጠፋሉ። 15 የኀጢአተኞች ልጆች ቅርንጫፎቻቸው አይበዙም፤ የርኩሳን ሰዎች ሥራቸው በሚያድጥ ዓለት ላይ እንደ ወደቀ ዘር ነው። 16 በውኃና በወንዝ ዳር የበቀለ አረምም ከሣሩ ሁሉ ቀድሞ ይነቀላል። 17 ጸጋ ግን በበረከት እንደ እግዚአብሔር ገነት ናት፥ ምጽዋትም ለዘለዓለሙ ጸንቶ ይኖራል። 18 የሚዘጋጅና የሚሠራ ሰው ሕይወቱ ጣፋጭ ነው፤ ከእነዚህም ከሁለቱ ይልቅ የተቀበረ ወርቅን ማግኘት ደስ ያሰኛል። 19 ልጆችና የሀገር ሕንጻ ስምን ያስጠራሉ፤ ከእነዚህ ከሁለቱ ይልቅ ምንም ነውር የሌለባት ሴት ደስ ታሰኛለች። 20 ወይንና ማሕሌት ልብን ደስ ያሰኛሉ፥ ከሁለቱም ይልቅ ጥበብን መውደድ ደስ ያሰኛል። 21 በገናና መሰንቆ ሰውነትን ደስ ያሰኙኣታል፤ ከሁለቱም ይልቅ ልዝብ አንደበት ደስ ያሰኛል። 22 ደም ግባትና ውበት ዐይንን ደስ ያሰኙኣታል። ከሁለቱም ይልቅ ቡቃያ ደስ ያሰኛል። 23 ወዳጅና ጓደኛ በዘመናቸው ይጠቅማሉ፤ ከሁለቱም ይልቅ ደግ ሴት ባሏን ትጠቅማለች። 24 ወንድሞችና ረዳት በመከራ ቀን ይጠቅማሉ፤ ከሁለቱም ይልቅ ለማዳን ምጽዋት ትበልጣለች። 25 ወርቅና ብር ሀገርን ያጸናሉ፤ ከሁለቱም ይልቅ በጎ ምክር ደስ ታሰኛለች። 26 ባለጸግነትና ገንዘብ ልቡናን ደስ ያሰኛሉ፤ ከሁለቱም ይልቅ እግዚአብሔርን መፍራት ደስ ያሰኛል፤ እግዚአብሔርን መፍራት የምታሳጣው የለም፤ አጋዥም አትሻም። 27 እግዚአብሔርን መፍራት በበረከትዋ እንደ እግዚአብሔር ገነት ናት፤ ክብርና ደስታም ሁሉ በእርስዋ አለ። 28 ልጄ ሆይ! በጉልበትህ ሳለህ ልመናን አትውደዳት፤ ከመለመን መሞት ይሻላል። 29 የሌላ ማዕድ ደጅ የሚጠናና ተስፋ የሚያደርግ ሰው፤ ኑሮው እንደ ሞተ ሰው ነው፤ የሰው እህል የሚወድ ሰው ከሐሜት አይድንም፤ የተመከረ ብልህ ሰው ግን ከሁሉ ይጠበቃል። 30 ለማያፍር ሰው አፍ ልመና ጣፋጭ ነው፤ በሆዱ ግን እሳት ትነድዳለች። |