ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 38 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ባለ መድኀኒትና መድኀኒት 1 ባለ መድኀኒትን አክብረው፥ እንደ እጁ እንዲሁ ክብሩ ነውና። እርሱንም እግዚአብሔር ፈጥሮታልና። 2 ማዳን ከእግዚአብሔር የሚገኝ ሲሆን፥ ክብርን ግን ከንጉሥ ይቀበላል። 3 ሰው ሁሉ ባለ መድኀኒትን በጥበቡ ያከብረዋል፤ በመኳንንትም ዘንድ ይመሰገናል። 4 እግዚአብሔር መድኀኒትን ከምድር ፈጠረ፤ ጠቢብ ሰውም ይህን አይንቀውም። 5 ኀይሉን ያውቁ ዘንድ፥ ውኃ በእንጨት የጣፈጠ አይደለምን? 6 በጌትነቱ ይከብሩ ዘንድ፥ እግዚአብሔር ለሰዎች ጥበብን ሰጣቸው። 7 በመድኀኒቱ ያድናቸዋል፤ በሽታቸውንም ያርቅላቸዋል። 8 ያድኑ ዘንድ ከእነርሱ መድኀኒትን ያደርጋሉ፤ እርሱም ለሀገር ሰላምን ያመጣል። 9 ልጄ ሆይ፥ በሽታህን ቸል አትበል፤ ወደ እግዚአብሔርም ጸልይ፤ እርሱም ይፈውስሃል። 10 ኀጢአትን ተዋት፤ እጅህን አቅና፤ ልቡናህንም ከኀጢአት ሁሉ አንጻ። 11 መባእህን አግባ፤ የመታሰቢያውንም የስንዴ ዱቄት ስጥ፤ የሰባ መሥዋዕትህንም የተቻለህን ያህል አብዝተህ አቅርብ፤ 12 እግዚአብሔር እርሱን ፈጥሮታልና፤ ለባለ መድኀኒት መንገድን አብጅለት፥ እርሱንም ትሻዋለህና ከአንተ አታርቀው። 13 በእጃቸው ፈውስ የሚደረግበት ጊዜ አለና። 14 ይረዳቸው ዘንድ፥ ዕረፍትንም ይሰጣቸው ዘንድ፥ ሁልጊዜም ይፈውሳቸው ዘንድ እነርሱ ወደ እግዚአብሔር ይለምናሉ። 15 ፈጣሪውን የሚበድል በባለ መድኀኒት እጅ ይወድቃል። ለሞተ ሰው መታሰቢያ ስለ ማድረግ 16 ልጄ ሆይ፥ ለሞተ ሰው አልቅስለት፥ እዘንለትም፤ ራስህንም አሳዝን፤ እንደ ሥርዐቱም መታሰቢያ አድርግለት። ያገለገለህን ሰው ሞት ቸል አትበል። 17 እንደ ልማዱ መራራ ልቅሶ አልቅስለት፤ ጥልቅ ኀዘንም እዘንለት፥ የኀዘን መዝሙርም ዘምርለት፤ እንደ ሕጉም አንድ ቀን ቢሆን ሁለት ቀን ቢሆን አልቅስለት። 18 ከዚህ በኋላ ልቅሶህን ተው። ኀዘንም አይግባህ፤ በኀዘን የሞቱ ብዙዎች ናቸውና፥ የልብ ኀዘንም ኀይልን ይሰብራልና። 19 ኀዘንና ትካዜ ለሞት ያደርሳል፤ የድሃም ዘመኑ ሁሉ በኀዘን ያልቃል። 20 ኀዘንን ወደ ልቡናህ አታግባ፤ ኀዘንን ከአንተ አርቃት። 21 ድኅነት እንደሌለባት ዕወቅ፤ ራስህንም ትጎዳለህ፥ ታሳዝናለህ፥ የምትጠቅመውም ነገር የለም። 22 እኔ የተቀበልሁትን ፍዳ አስተውል፤ አንተም እንደዚሁ ፍዳን እንደምትቀበል ዕወቅ። እኔ ዛሬ አንተም ነገ። 23 የሞተ ሰውስ ዐረፈ፤ ነገር ግን መታሰቢያውን አድርግለት፤ ከዚህ በኋላ ነፍሱ ታርፍ ዘንድ ልቅሶህን ተው። 24 የጸሓፊ ጥበቡ በተሾመበት ወራት ነው፤ ሥራውን የማያበዛ ሰው አይራቀቅም። 25 ዕርፉን የሚያጸና ሰው በምንም አይራቀቅም፥ በእርሻው ይታበያል፥ በሬውንም ይገርፋል፤ በሥራውም ይመላለሳል፤ ነገሩም ሁሉ ስለ በሬና ወይፈን ነው። 26 አሳቡ እርሻውን እንዲያርስ ነው፤ ትጋቱም በሬውን ገለባ ያበላ ዘንድ ነው፤ ወይፈኑንም እስኪያቀና ድረስ ይደክማል። 27 ሌሊቱ ቀን የሚሆንባቸው ጠራቢና የጠራቢዎች አለቃ፥ የማኅተም ቅርጽ የሚቀርጹና የሚያለዝቡ ሰዎች እንደ እርሱ ናቸው፤ እነዚህም አሳባቸው ሁሉ በየመልኩ መስለው ይሠሩ ዘንድ ነው፤ ምክራቸውም ሁሉ ማኅተሙን ማለዘብን ይጠነቀቁ ዘንድ ነው፤ ትጋታቸውም ሥራቸውን ይፈጽሙ ዘንድ ነው። 28 በወናፍ አጠገብ የሚቀመጥ፥ የብረትንም ሥራ የሚማር አንጥረኛ እንደ እርሱ ነው። የወናፉም ጢስ ሰውነቱን ያሻክረዋል። እሳቱም ሰውነቱን ያቀልጣታል፤ የመዶሻውም ድምፅ ጆሮውን ያደነቍረዋል። ዐይኖቹም ወደ መሣሪያው ይመለከታሉ፤ በልቡም ሥራውን ይጨርስ ዘንድ ያስባል፤ ትጋቱም መሣሪያውንና ወናፉን ያሳምር ዘንድ ነው። 29 በሥራው የሚቀመጥ ሸክላ ሠሪም እንደ እርሱ ነው፥ በእግሩም መንኰራኵርን ያዞራል፤ ሥራውንም እንዴት እንደሚፈጽም ሁልጊዜ ያስባል። የሠራውንም ሁሉ ይቈጥራል። 30 በእጁም ጭቃውን መስሎ ይሠራል፤ በእግሩ ጭቃውን ሲረግጥ ኀይሉን ያደክማል፤ የልቡናውም አሳብ ሥራውን ይጨርስ ዘንድ ነው። ትጋቱም መወልወያውን ያዞር ዘንድ ነው። 31 እነዚህ ሁሉ የእጃቸውን ሥራ ተስፋ ያደርጋሉ፤ ሁሉም በሥራቸው ይራቀቃሉ። 32 ያለ እነርሱም ሀገር መኖር አትችልም። 33 ነገር ግን በሸንጎ ምክርን አያስመክሯቸውም፤ በአደባባይም ከመኳንንት ጋራ አያስቀምጧቸውም፤ የቅጣት ፍርድንም አያስፈርዷቸውም፤ አያስገዟቸውም፤ አያሠለጥኗቸውምም። 34 ነገርን መስሎ በመናገር አይኖሩም፤ ነገር ግን ያገርን ፈቃድ ያጸናሉ፤ ጸሎታቸውም በሥራቸው ይራቀቁ ዘንድ ነው። 35 ዕውቀት ግን በልቡ ለሚተጋ ሰው ነው። የልዑልንም ሕግ ለሚያስብ ሰው ነው። |