ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 37 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ወዳጅ ያበጀ ሰው ሁሉ እኔም ወዳጁ ነኝ ይላል፤ ነገር ግን በከንቱ ለስም ወዳጅ የሚሆን ሰው አለ። 2 በልቡናው ግን እስከሚሞትበት ቀን ድረስ ኀዘን ይኖራል፤ ጠላት የሚሆን ወዳጅም አለ። 3 ክፉ ምኞት ሆይ! ከወዴት ተገኘሽ፤ በምድሩ ሁሉ ኀጢአትን መላሽ። 4 በደስታህ ጊዜ የሚቀርብህ ወዳጅ አለ፤ ብትቸገር ግን እርሱ ጠላት ይሆንሃል። 5 በበሽታህ ጊዜ ስለ ሆዱ የሚያዝንልህ ወዳጅ አለ፤ የሚከዳህ ሰው ቢኖር ግን ይገድልህ ዘንድ እርሱ ይቀድማል። 6 በተመቸህ ጊዜ ወዳጅህን አትርሳ፤ ገንዘብም ብታገኝ አትተወው። 7 መካር ሁሉ ምክርን ይመክራል፤ ነገር ግን ራሱን ይጠቅም ዘንድ የሚመክር ሰው አለ። 8 ከሚመክርህ ሰው ልቡናህን ጠብቅ፤ ስለ ራሱ ይመክርሃልና፤ ይወድድህም ዘንድ አስቀድመህ ፍላጎቱን ዕወቅበት። 9 ገንዘብህን የሚያጠፋብህን ነገር ያመጣብሃል በጎ ነገር አደረግህ ይልሃል፤ በተቸገርህም ጊዜ አይቶ ይስቅብሃል። 10 ከሚጠባበቅህ ሰው ጋራ አትማከር፤ ከሚመቀኝህም ሰው ነገርህን ሰውር። 11 ከሴት ጋር ስለሚያስቀናት ነገር አትናገር፤ ስለ ጦርነትም ከፈሪ ሰው ጋር አትማከር። ስለ ትርፍም ከሻጭ ጋር አትማከር፤ ስለ ንግድ ነገርም ከነጋዴ ጋር አትማከር። ስለ ምጽዋትም ከንፉግ ሰው ጋር አትማከር። ዋጋን ስለ መመለስም ከከዳተኛ ጋር አትማከር፤ ስለ ሥራም ከሰነፍ ሰው ጋራ አትማከር፤ ሥራ ስለሚፈጸምበት ዓመትም ከምንደኛ ጋር አትማከር። ስለ ጥበብም ከአላዋቂ ሰው ጋር አትማከር፤ ከዚህም ሁሉ ጋር ስለዚህ ነገር የምትማከረው አይኑር። 12 ሃይማኖት እንዳለው ከምታውቀው፥ እግዚአብሔርንም ከሚፈራ፥ ልቡናውም እንደ ልብህ ከሆነ ጻድቅ ሰው ጋር ምክርህን ተናገር፤ ብታዝንም ከአንተ ጋር ያዝናል። 13 እርስዋ ከሁሉ ይልቅ ታማኝህ ናትና፤ የልቡናህን ምክር አጽና። 14 የሰው ልቡና ከሰባት ጠባቂዎች ይልቅ የሚደርስበትን ነገር ፈጽማ ታስታውቀዋለችና። 15 ከዚህ ሁሉ ጋር መንገድህን በእውነት ያቀናልህ ዘንድ፥ ወደ ልዑል እግዚአብሔር ለምን። 16 የመፍቅድ ሁሉ መጀመሪያ ቃል ነው፤ የሥራም ሁሉ መጀመሪያ ምክር ነው። 17 የሰው የልቡ ምልክት በአራቱ ወገን ይታያል። 18 እነዚህም ኀዘንና ደስታ ሞትና ሕይወት ናቸው። እነዚህንም ሁሉ አንደበት ያመጣቸዋል። 19 ሁሉን የሚማር፥ ብዙም የሚያውቅ ሰው አለ፤ ነገር ግን ሰውነቱን መጥቀም አይችልም። 20 በነገር የሚራቀቅ፥ ነገር ግን ራሱን የሚያስጠላ ሰው አለ። እንደዚህ ያለውን ሰው ጥቅሙ ሁሉ ያልፈዋል። 21 እግዚአብሔር ሞገስን አይሰጠውምና ከጥበቡም ሁሉ ወጥትዋልና። 22 በራሱ የሚራቀቅ፥ በቃሉም የዋህ የሚሆን ሰው አለ። 23 ብልህ ሰው ወገኖቹን ይመክራቸዋል፤ ለዘመዶቹም ጥበብን ያስተምራቸዋል። 24 ብልህ ሰው በበረከት ይጠግባል፤ ያዩትም ሰዎች ሁሉ ብፁዕ ይሉታል። 25 የሰው ዘመኑ በቍጥር ነው፤ የእስራኤል ዘመን ግን የማይቈጠር ነው። 26 ለወገኖቹ ጥበበኛ የሆነ ሰው ዋጋውን ያገኛል፤ ስሙም ለዘለዓለም ይኖራል። 27 ልጄ ሆይ፥ በሕይወት ሳለህ ሰውነትህን ፈትናት፥ የሚጎዳትንም ዐውቀህ አትስጣት፤ 28 ሁሉ ለሰውነት የሚገባት አይደለምና፥ ሁሉም ደስ የሚያሰኛት አይደለምና፤ 29 ለመብል ሁሉ አትሰስት፤ ላየኸውም እህል ሁሉ አትሳሳ። 30 ብዙ መብላት ደዌ ይሆናልና፤ ስስትም ጓታን ያበዛዋልና። 31 ስስት የገደላቸው ሰዎች ብዙ ናቸው፥ መጥኖ የሚበላ ሰው ግን ሰውነቱ ጤነኛ ነው። |