ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 35 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 አለቃም አድርገው ቢሾሙህ ራስህን አታኵራ፤ ከእነርሱ እንደ አንዱ ሁን፤ ኀዘናቸውንም እዘን፤ ተቀምጠህም ፍረድላቸው። 2 ሥራህን ጨርሰህ ዕረፍ፤ መልእክትህን ጨርሰህ የክብር ዘውድን ታገኝ ዘንድ ከእነርሱ ጋራ ደስ ይበልህ። 3 ሽማግሌ ሆይ፥ ተናገር፤ ይገባሃልም፥ ለበጎ ነገርም ቸል አትበል፤ የጥበብህንም ነገር ተናገር። 4 ለመረመረህ ሰው ሁሉ ቃልህን አትናገር፤ እንዳገኘህም አትራቀቅ። 5 በወርቅ ጌጥ ክቡር ዕንቍ ደስ እንደሚያሰኝ፥ ዘፈንም ወይን በሚጠጡ ሰዎች ዘንድ እንዲሁ ነው። 6 በወርቅ ዝርግፍ ላይ ዕንቍ እንደሚያምር፤ ዘፈንና መሰንቆ በመጠጥ ቤት እንዲሁ ያማረ ነው። 7 ጎልማሳ! ከተፈቀደልህ ተናገር፤ ዳግመኛም ቢጠይቁህ በጭንቅ ተናገር። 8 አንድ ጊዜ ተናግረህ፥ ወዲያውኑ ነገርህን ጨርስ፤ እያወቅህም በአንደበትህ ዝም በል። 9 በታላላቆች መካከል አትቀመጥ፤ ሌላ ሰውም ሲናገር ነገርህን አትናገር። 10 መብረቅ ከነጐድጓድ በፊት እንደሚሮጥ፥ እንዲሁ የሚያፍር ሰው መከበሩ በፊቱ ነው። 11 ወደ ቤትህ ገብተህ ሁሉን በጊዜው መጥነህ አድርግ፤ በዚያም ደስ ይበልህ ተጫወትም። 12 የሚገባውንና የሚወደደውንም ሁሉ አድርግ፤ የትዕቢትን ነገር እንዳትናገር ዕወቅ፤ በቃልህም አትበድል። 13 ከዚህ ሁሉ ጋራ ፈጣሪህን አመስግነው፤ እርሱም ከበረከቱ ሁሉ ያጠግብሃል። ሕግን መተርጐም 14 እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ለሕጉ ይገዛል፤ ወደ እርሱም ፈጥነው የሚሄዱ ሰዎች መፍቅዳቸውን ያገኛሉ። 15 ሕጉንም የሚፈልገው ከእርሱ ይጠግባል፤ በእርሱ የሚጠራጠር ግን ይወድቃል፤ ይበድላልም። 16 እግዚአብሔርን የሚፈሩት ሰዎች ፍርድን ያገኛሉ፤ በእኩለ ቀንም ተበቅሎ ጠላቶቻቸውን ያጠፋላቸዋል። 17 ኀጢአተኛ ሰው ግን የሚመክሩትን አይሰማም፤ ሁሉም እንደ እርሱ ይመስለዋል። 18 ብልህ ሰው ያለ ምክር የሚሠራው ሥራ የለም፤ የሚሠራውም ሥራ የበጀ ይሆንለታል፤ ፍርሀትን የማያስብ ትዕቢተኛ ጠላት ግን ያለ ምክር ይሠራል። 19 ልጄ ሆይ፥ አንተ ግን ያለ ምክር የምትሠራው ሥራ አይኑር፤ የሠራኸውንም ሥራ አታጥፋ። 20 በጥፋት ድንጋይ እንዳትሰነካከል፥ መንገድ በሌለበት በምድረ በዳ አትሂድ። 21 ጠላትህን በምድረ በዳ አትመነው። 22 በፈቃድህ የማይሄድ ልጅህን ስንኳ አትመነው። 23 በሠራኸው ሥራ ሁሉ ሰውነትህን ደስ አሰኛት፥ በሁሉም ትእዛዙን ጠብቅ። 24 ሕጉን የሚጠብቅ ሰው የመጽሓፉን ትእዛዝ ይሰማል፤ በእግዚአብሔርም የሚያምን ሰው የሚያጣው ነገር የለም። |