ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 32 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ሕጉን የሚጠብቅ ሰው መባ ያገባል። 2 ትእዛዙን የሚሰማ ሰውም ለድኅነቱ መሥዋዕትን ይሠዋል። 3 ስንዴ የሚያገባ ሰው ዋጋውን ይመልሳል። 4 ምጽዋትን የሚመጸውት ሰውም የምስጋና መሥዋዕትን ሠዋ። 5 የእግዚአብሔር ፈቃዱ ክፉ እንዳትሠራ ነው፤ ፈቃዱም ከበደል ትርቅ ዘንድ ነው። 6 ወደ እግዚአብሔር ፊት ባዶህን አትግባ። 7 ይህን ሁሉ ስለ ትእዛዙ አድርግ። 8 የጻድቅ ሰው መሥዋዕት ምሠዊያውን ያለመልመዋል፤ መዓዛውም ወደ ልዑል ፊት ይደርሳል። 9 የጻድቅ ሰው መሥዋዕት ቅዱስ ነው፤ ስም አጠራሩም ሁሉ አይዘነጋበትም። 10 በደስታ ዐይን እግዚአብሔርን አመስግነው፤ ከመጀመሪያ አዝመራህም ዐሥራት ማግባትን አትተው። 11 የሰጠህን ሁሉ ፊትህን ደስ እያለው ስጠው፤ ደስ እያለህም የአዝመራህን ዐሥራት አግባ። 12 እንደ ክብሩ ብዛት መጠን ለእግዚአብሔር መባእህን አግባ፤ በእጅህ ከአገኘኸውም በመልካም ዐይን አግባለት። 13 እግዚአብሔር ዋጋህን ይመልስልሃልና፤ ሰባት እጥፍ አድርጎም ይሰጥሃልና፤ 14 አይቀበልልህምና መማለጃን አታግባለት። 15 እግዚአብሔር የእውነት ዳኛ ነውና፥ ፊትን አይቶም አያዳላምና የዐመፃ መሥዋዕትን የሚቀበል አይምሰልህ። 16 ድሃውን ስለ ችግሩ አይለየውም፤ የተበደለ ሰውንም ጩኸት ይሰማል። 17 የሙት ልጅ ልመናን ቸል አይልም፤ ባልቴት ሴትንም የሚያስለቅሳት ሰው ቢኖር፥ 18 እንባንም በፊትዋ ላይ ብታወርድ፥ 19 እንደዚሁ ባስለቀሳት ሰው ላይ እንባ ይወርዳል። 20 በእውነት የሚያገለግለውን ሰው ይቀበለዋል፤ ጸሎቱም እስከ ደመና ትደርሳለች። 21 የትሑት ጸሎት ከደመና ታልፋለች፥ ወደ እርሱ እስክትደርስ አትመለስም፥ እግዚአብሔርም እስከሚያያት ድረስ አትመለስም። 22 ለጻድቃን ይፈርድላቸዋል፤ ይበቀልላቸዋልም፤ እግዚአብሔር ለእነርሱ አይዘገይም፤ ክፉዎችን ወገባቸውን እስኪቀጠቅጥ ድረስ ስለ እነርሱ ፈጽሞ አይታገሥም። 23 አሕዛብን ይበቀላቸዋል፤ ዐመፀኞችንም ሁሉ ያጠፋቸዋል፤ የኀጢአተኞችንም በትር ይሰብራል። 24 ለሰው ሁሉ እንደ ሥራው ይከፍለዋል። 25 ስለ ሰዎችም ሁሉ እንደ ሥራቸውና እንደ አካሄዳቸው ፍዳውን ይከፍላቸዋል። የወገኖቹን በቀል ይመልሳልና፥ በቸርነቱም ደስ ያሰኛቸዋልና። 26 በመከራ ጊዜ የሚገኝ ምሕረት በቃጠሎ ጊዜ ዝናም እንደ ያዘ ደመና ነው። |