ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 29 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ማበደርና መበደር 1 ምጽዋትን የሚመጸውት ሰው ለእግዚአብሔር ያበድራል፤ በእጁም የሚበቃ ያለው ትእዛዙን ይፈጽማል። 2 በደስታው ጊዜ ከእርሱ ጋር ደስ ይልህ ዘንድ፥ በተቸገረ ጊዜ ለባልንጀራህ አበድረው። 3 ቃልህን ጠብቅ፤ ከእርሱም ጋራ ተማመን፤ በጊዜውም የሚያስፈልግህን ነገር ታገኛለህ። 4 የብድርን ገንዘብ በምድር ላይ ወድቆ ያገኙት የሚመስላቸው ብዙዎች ናቸው፤ የረዷቸውንና ያበደሩአቸውንም ችግር ይፈጥሩባቸዋል። 5 እስኪበደርህ ድረስ ራስህን ይስምሃል፤ ቃሉንም ያለሰልሳል፤ ገንዘብህንም እስኪወስድ ድረስ ያባብልሃል፤ በሚከፍልበት ጊዜ ግን ቀጠሮህን ያረዝምብሃል፤ በገንዘብህም ጠብና ክርክርን ይከፍልሃል፤ ያደክምሃል፤ ቀጠሮህንም ያሳልፋል። 6 እኩሌታውን ቢከፍልህ በጭንቅ ነው፤ ዳግመኛም ያንኑ በምድር ላይ ወድቆ ያገኘኸው ይመስልሃል፤ ይህስ ካልሆነ ገንዘብህን ሁሉ ታጣለህ፤ ዳግመኛም ጠላት ይሆንሃል፤ ርግማንንና ስድብን ይከፍልሃል፤ ከሚያከብርህም ይልቅ ያዋርድሃል። 7 ገንዘባቸውን እንዳያጡና እንዳይጣሉ በመፍራትና ጠብን ባለመውደድ ገንዘባቸውን የማያበድሩ ሰዎች ብዙ ናቸው። ስለ ምጽዋት 8 ድሃዉን ግን ታገሠው፤ ምጽዋቱንም ስጠው፤ አልፈኸውም አትሂድ። 9 ችግረኛ ነውና በሕግ እንደ ታዘዘው ድኃዉን በምጽዋት ተቀበለው፤ ባዶውንም አትመልሰው። 10 ባልንጀራህንና ወዳጅህን ከምታጣ፥ ተቀብሮ ከሚዝግና በድንጋይም ሥር ከሚጠፋ ወርቅህን እጣ። 11 ስለ ልዑል ትእዛዝ በወርቅህ አስተዋፅኦ አድርግ፤ ከወርቅ ድልብ የበለጠም ያተርፍልሃል። 12 ምጽዋትን በቤቶችህ አድልባት፤ እርስዋም ትሻላለች፤ ከመከራህም ሁሉ አንተን ማዳን ትችላለች። ስለ ዋስትና 13 ከጦርና ጋሻ ትሻላለች፤ ጠላትህን ድል ትነሣልሃለች፤ ታጠፋልሃለችም። 14 ደግ ሰው ጎረቤቱን ይዋሰዋል፤ የማያፍር ሰው ግን ባልንጀራውን ቸል ይላል። 15 ስለ አንተ ፋንታ ሰውነቱን አሳልፎ ሰጥትዋልና የተዋሰህን ሰው ውለታ አትርሳ። 16 ጠብን ለማጥፋት መዋስ ደግ ነገር ነው። 17 ኀጢአተኛ ሰው ግን ያዳነውን ሰው ውለታ ይዘነጋል። 18 መዋስ ብዙ ደጋግ ሰዎችን አሳዘነ፤ እንደ ባሕር ማዕበልም አወካቸው፤ አርበኞች ሰዎችንም አሳታቸው፤ ወደ ባዕድ ሕዝብም አሳደዳቸው። 19 ኀጢአተኛ ሰው ግን በመዋስ ይጠፋል፤ ለትርፍም የሚሳሳ ሰው በመከራ ይወድቃል። 20 በተቻለህ መጠን ባልንጀራህን ርዳው፤ ነገር ግን እንዳያስትህ ራስህን ጠብቅ። 21 የሕይወትህ መጀመሪያ እህልና ውኃ፥ ልብስም ነው፤ ቤትህ ግን ኀፍረትህን የምትሰውርበት ነው። 22 በሌላ ሰው ገንዘብ በባዕድ ቤት ፈጽመህ ደስ ከሚልህ፥ በራስህ ጎጆ ብትቸገር ይሻልሃል። 23 ለታናሹም ለታላቁም ሥራህንና ቃልህን አሳምር። 24 ካንዱ ቤት ወደ ሌላው ቤት የሚዞር ሰው ኑሮው ክፉ ነው፤ ባደርህበት ቦታ ክፉ ነገር እንዳትናገር ተጠንቀቅ። 25 ያም ባይሆን ታበላለህ፤ ታጠጣለህም፤ ምስጋና ግን አይኖርህም፥ ከዚህም ሁሉ ጋር መራራ ነገርን ይመልሱልሃል። 26 በተዘጋጀህ ጊዜ ግን እንዲህ ይሉሃል፥ “እንግዳችን ገብተህ ማዕድን ሥራ፤ ያለህንም አብላን።” 27 ብትቸገር ግን፥ “እንግዳችን ውጣ፤ አማቻችን ደረሰ፤ ቤታችንን እንፈልገዋለን” ይሉሃል። 28 ይህ ነገር በብልህ ሰው ዘንድ ጭንቅ ነው፤ ያሳደርኸው ሰው ያዋርድሃል፤ ያበደርኸውም ሰው ይሰድብሃል። |