ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 27 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 በግብዝነት ኀጢአትን የሚሠሩአት ብዙዎች ናቸው፤ ገንዘቡ ይበዛለት ዘንድ የሚወድድ ሰው ግን ዐይኑን ይመልሳል። 2 ችንካር በድንጋይ ግንብ መካከል እንደሚተከል፥ በመሸጥና በመግዛት መካከል ኀጢአት ትመጣለች። 3 እግዚአብሔርን በመፍራት ፈጥኖ ካልተጠበቀ፥ የቤቱ ውድቀት አይዘገይም። የሕይወት መመዘኛ 4 በወንጠፍት ዐሠር ይከማቻል፤ እንዲሁም ሁሉ ሰውን ኀጢአቱ ታገኘዋለች። 5 የሸክላ ዕቃን እሳት ይፈትነዋል፤ ሰውንም የልቡናው ዐሳብ ይፈትነዋል። 6 ተክል የሚጠብቅ ሰው ፍሬውን ያያል፤ እንዲሁም የሰው ነገሩ የልቡናውን ፈቃድ ይገልጥበታል። 7 ሰውን ሳትረዳው አታድንቀው፤ ሰውን ከሥራው የተነሣ ይፈትኑታልና። 8 ጽድቅን ብትከተላት ታገኛታለህ፥ እንደ ከበረ ግምጃም ትለብሳታለህ። 9 ወፍ ከዘመዱ ጋር ይኖራል፤ ጽድቅም በሚሠሯት ሰዎች ዘንድ ትኖራለች። 10 አንበሳ የሚበላውን ያድናል፤ እንዲሁም ኀጢአት የሚሠሯትን ሰዎች ታድናቸዋለች። 11 ጻድቅ ሰው ሁልጊዜ ጥበብን ያስተምራል፤ የሰነፍ ሰው ግን ዕውቀቱ እያደረ እንደ ጨረቃ ይጐድላል። 12 በሰነፎች ዘንድ ጊዜውን ተጠበቅ፤ በብልሆች ሰዎች ዘንድ ግን ሁልጊዜ ተረዳ። 13 የሰነፎች ነገር ያበሳጫል፤ ሣቃቸውም የኀጢአት ደስታ ነው። 14 ብዙ መሐላን የሚምል ሰው ነገር ፀጕርን ያቆማል፤ የትዕቢተኛ ሰው ክርክርም ዦሮ ያደነቍራል። 15 የትዕቢተኞች ጠብ ደም ያፋስሳል፤ ክርክራቸውም ለሚሰማቸው ሰው ድካም ነው። የባልንጀራን ምሥጢር ማውጣት እንደማይገባ 16 የባልንጀራውን ምሥጢር የሚያወጣ ሰው መታመኑን ያጠፋል፤ ከዚህም በኋላ እንደ ልቡ የሚሆን ወዳጅን አያገኝም። 17 ወዳጅህን ጠብቅ፤ ከእርሱም ጋራ ተማመን፤ ምሥጢሩን ብታወጣበት ግን በኋላው አትከተለውም። 18 ሰው ጠላቱን እንደሚያጠፋ፥ አንተም የወዳጅህን ወንድምነት ታጠፋለህ። 19 ወፍ ከእጅህ እንደምታመልጥ፥ እንዲሁ ወዳጅህ ከአንተ ያመልጣል። 20 ምዳቋ ከወጥመድ እንደምታመልጥ፥ ከአንተ አምልጦ ርቋልና ከዚህ በኋላ አትከተለውም። 21 ቍስል ቢሆን ባዳኑት ነበር፤ የተሰደበንም ሰው ባስካሱት ነበር፤ የባልንጀራውን ምሥጢር የሚያወጣውን ሰው ግን ተስፋ ይቈርጡበታል። ስለ ግብዝነት 22 ክፋቱን ማስተው የሚችል የለምና፤ በዐይኑ የሚጠቅስ ሰው ልቡናው ያማረ አይሆንም። 23 ለዐይንህ ግን ከንፈሩን ይመጥጥልሃል፤ በተናገርኸውም ሁሉ ያመሰግንሃል፤ ኋላ ግን በቃሉ ይወነጅልሃል፤ በተናገርኸው ቃልህም ያጠምድሃል። 24 የጠላኋቸው ብዙዎች ናቸው፤ ነገር ግን እንደ እርሱ አይደሉም፤ እግዚአብሔርም እርሱን ይጠላል። 25 ድንጋይን ወደ ላይ የሚወረውር ሰው በራሱ ላይ ትወርዳለች፤ የበደል ግርፋትም ቍስሉ ይታወቃል። 26 ለባልንጀራው ጕድጓድ የቈፈረ ሰው፥ እርሱ በውስጡ ይወድቃል፤ ወጥመድም ያዘጋጀ ሰው ራሱ ይያዝበታል። 27 ሰው ኀጢአትን ቢሠራ በእርሱ ላይ ትመለሳለች፤ ከየትም እንደምትመጣ አያውቅም። 28 የትዕቢተኞች ስድባቸውና ሣቃቸው እንደ አንበሳ ያድኑአቸዋል፤ ይበቀሉአቸዋልም። 29 በጻድቅ ሰው መውደቅ ደስ የሚላቸው ሰዎች በወጥመድ ይያዛሉ፤ የሚሞቱበትም ጊዜ ሳይደርስ መቅሠፍት ያጠፋቸዋል። 30 ቍጣና መዓትም የሚያስጸይፉ ናቸው፤ በኀጢአተኛ ሰውም ዘንድ ጸንተው ይኖራሉ። |