ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 26 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የደግ ሴት ተግባር 1 ደግ ሴትን ባሏ ያመሰግናታል፤ የሕይወት ዘመኑም እጥፍ ይሆናል። 2 ቅን ሴት ባሏን ደስ ታሰኘዋለች፤ ዘመኑንም በሰላም ይጨርሳል። 3 የደግ ሴት ዕድሏ ያማረ ነው፤ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰውንም ወደ ዕድሉ ታደርሰዋለች። 4 የባለጸጋውም የድሃውም ልቡ የቀና ይሁን፤ ሁልጊዜም ፊቱ የበራ ይሁን። ስለ ክፉ ሴት 5 በእነዚህ በሦስቱ ነገሮች ልቡናዬ ደነገጠብኝ፤ አራተኛውም ፊቴን አስፈራኝ፤ ይኸውም የከተማ ሁከት፥ የአሕዛብ መዶለት፥ የሐሰት ምስክር፤ እነዚህ ሁሉ ሰውን ለሞት ያደርሳሉ። 6 ባሏን የምታስቀና ሴት የልብ ቍስል ናት፤ የሰውነትም ኀዘን ናት፤ በክፉ ሁሉ የምትስተካከል የምላስ ጅራፍ ናት። 7 ክፉ ሴት ውልቅ ውልቅ እንደሚል፥ እንደ በሬ ቀንበር ናት፤ እርስዋንም የሚይዝ ሰው ጊንጥ እንደሚጨብጥ ሰው ነው። 8 ሰካራም ሴት ታላቅ ጥፋት ናት። ኀፍረትዋንም አትሸፍንም፤ 9 የሴት ዝሙትዋ በዐይኗ ይታወቃል፤ በቅንድቧም ይታወቃል። 10 ስታ ራሷን እንዳታጠፋ፥ ልጅህን አጽንተህ ጠብቃት። 11 ከአመንዝራ ዐይን ጠብቃት፤ ብትበድልህም አትደነቅ። 12 እርስዋ የተጠማ ሰው ከቀረበው ውኃ ሁሉ እየላሰ እንደሚጠጣ፥ በዛፍም ሁሉ ሥር እንደሚያርፍ፥ 13 ፍላጻውንም ከሰገባው እንደሚያወጣ ናትና። የደግ ሴት በረከት 14 የሴት ሞገስዋ ባሏን ደስ ያሰኛል። 15 ጥበቧም አጥንቱን ያለመልመዋል። 16 የዋህ ሴት የእግዚአብሔር ስጦታ ናት። 17 ለብልህ ሴት ለውጥ የላትም። 18 የምታፍር ሴት በበረከት ላይ በረከት ናት። 19 ለትዕግሥተኛ ሴት ለውጥ የላትም። 20 ፀሐይ በእግዚአብሔር ሰማይ እንደሚያበራ፥ እንደዚሁ የደግ ሴት ውበቷ ባማረ በቤቷ ውስጥ ነው። 21 የተቀደሰችው መብራት በመቅረዟ ላይ እንደምታበራ፥ እንዲሁ የብልህ ሰው የመልኩ ውበት በጠባዩ ውበት ነው። 22 በብር ስክተት ላይ እንደቆሙ የወርቅ ምሰሶዎች፥ በበጎ ሥራ የቆመ የደግ ሰው እግር አገባብም እንዲሁ ነው። 23 በእነዚህ በሦስቱ ነገሮች ልቡናዬ አዘነብኝ። 24 ዐራተኛው ግን ብስጭትን አመጣብኝ። 25 እነዚህም አርበኛና ደፋር ሰው አጥቶ ሲቸገር፥ 26 ጠቢባን ሰዎች ሲስቱ፥ 27 ጽድቅን ትቶ ወደ ኀጢአት የሚመለስ ሰው ናቸው። 28 እንዲህ ያለውን እግዚአብሔር በጦር ያጠፋዋል። 29 አጣሪ ከኀጢአቱ በጭንቅ ይድናል፤ መሸተኛም ከበደል ተመልሶ አይጸድቅም። |